ሰመራ፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል ከዛሬ ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክከር ምዕራፍን እንደሚጀምር ገለፀ፡፡
የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባሳደር አይሮሪት መሐመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በአጀንዳ ሃሳቦቻቸው ላይ ውይይት የሚያደርጉ ሲሆን፣ በተጨማሪም ኮሚሽኑ በሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ የክልሉን ወኪሎች ያስመርጣል፡፡
ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም በክልሉ ከሚገኙ ወረዳዎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ተወካዮችን በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እንዲሳተፉ አስመርጦ ማዘጋጀቱን ያወሱት ኮሚሽነሯ፤ በመጪዎቹ ሁለት ቀናት እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍል ወኪሎች በአጀንዳ ሃሳቦቻቸው ላይ በየቡድናቸው ተወያይተው የተስማሙባቸው አጀንዳዎች ወደ ቀጣዩ የምክክር መድረከ ለሚያቀርቡላቸው ተወካዮቻቸው በአደራ ይሰጣሉ ብለዋል፡፡
ሂደቱ በሚከናወንባቸው ሶስተኛ፣ አራተኛ እና አምስተኛ ቀናት ከላይ የተጠቀሱትን የሕብረተሰብ ክፍል ወኪሎችን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በወኪሎቻቸው አማካኝነት የአጀንዳ ሃሳቦቻቸው ላይ በቡድን እንደሚወያዩና የተስማሙባቸውን አጀንዳዎችም በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸው አማካኝነት እንደሚያቀርቡ ነው ኮሚሽነሯ የገለፁት፡፡
ከነገ ማክሰኞ መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ቀናት በሚከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ መድረክ በአፋር ክልል ከሚገኙ ከ49 ወረዳዎች የተመረጡ ከ800 በላይ የሕብረተሰብ ክፍል ወኪሎች እንዲሁም ከ700 በላይ በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ የሶስቱ የመንግሥት አካላት ተወካዮች ተወካዮች፣ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም በክልሉ የሚኖሩ ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተሳታፊዎች እንደሚሆኑም አመላክተዋል፡፡
ይህ መርሃግብር የአፋር ክልል የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ይገባል የሚሏቸውን እጅግ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን የያዙ አጀንዳዎች በሕዝባዊ ውይይት የሚያዳብሩበት ብሎም ለኮሚሽኑ የሚያቀርቡበት ወሳኝ ምዕራፍ በመሆኑ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ በእጅጉ ወሳኝ መሆኑንም ኮሚሽነሯ ተናግረዋል፡፡
የባለድርሻ አካላት ተወካዮች በክልሉ ለተከታታይ ስድስት ቀናት የሚደገረውን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክከር ምዕራፍ ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳውን በመረዳት ንቁ ተሳትፎን ለማድረግ እንዲዘጋጁና በሂደቱም የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ኮሚሽነሯ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኮችን በተከታታይ እያካሄደ ይገኛል።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም