“አውስትራሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች” – ኢቫን ጄ ክሊፎርድ

አዲስ አበባ፡- አውስትራሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊና ሁለንተናዊ ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ የአውስትራሊያ ኤምባሲ ሰክንድ ሴክሬተሪ ኢቫን ጄ ክሊፎርድ ገለጹ::

ኢቫን ጄ ክሊፎርድ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አውስትራሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ እና ሁሉን አቀፍ አጋርነት ለማስቀጠል ቁርጠኛ ናት:: እንደ ኢቫን ጄ ክሊፎርድ ገለጻ፤ ሁለቱ ሀገራት በግብርና፣ በንግድ፣ ሠብዓዊ ሁኔታ፣ በአየር ንብረት ጉዳዮች እንዲሁም በተለያዩ መስኮች ጠንካራ ግንኙነት አላቸው።

የአውስትራሊያ መንግሥት በምስራቅ አፍሪካ አህጉር የግብርናውን ዘርፍ ለማሻሻል ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ 40 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ በዚህም አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል::

የአውስትራሊያ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በግብርና፣ በማዕድንና ቱሪዝም ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ኢቫን ጄ ክሊፎርድ ገልጸዋል:: በግብርናው ዘርፍ የሚደረገው ድጋፍ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት የሚደገፍ መሆኑን አስረድተዋል::

ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የግብርና መሠረተ ልማት በመገንባት እንዲሁም ሰላምና ደህንነትን በማስጠበቅ ረገድ ለምታደርገው ጥረት አውስትራሊያ እገዛ የምታደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለአብነትም ኦክስፋም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ የአውስትራሊያ ኩባንያ ሲሆን በምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ ሠብዓዊና መሰል ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ አመላክተዋል::

በተጨማሪም የአውስትራሊያ የልማት ተራድኦ ፕሮጀክት (ዳፕ) በኢትዮጵያ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ማህበረሰብ ክፍሎ ኑሯቸው እንዲሻሻል የዶሮ ዝርያዎችን በማሰራጨት እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ኢቫን ጄ ክሊፎርድ ተናግረዋል::

በተለይም የኢትዮጵያ ቡና በአውስትራሊያ ዜጎች ተመራጭ መሆኑን አውስተው፤ ይህም ከሀገሪቱ ጋር በንግድ ረገድ ያለውን ዕድል በስፋት ለመጠቀም ያግዛል ብለዋል::

ኢትዮጵያ ወደተሟላ እድገት ለመሻገር በቅርቡ ያደረገችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የአውስትራሊያ መንግሥት ይደግፋል ያሉት ኢቫን ጄ ክሊፎርድ፤ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የንግድ ሥራ ላይ እንዲሠማሩና የጋራ ተጠቃሚነት እንዲጠናከር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል::

አውስትራሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት አጋርነት ረጅም ዘመናትን አንዳስቆጠረ አውስተው፤ በቀጣይ በተለይ በኢኮኖሚ ዘርፉ ያላቸውን ትስስር ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚሠሩ ጠቁመዋል::

በተመሳሳይ የአውስትራሊያ ኩባንያዎች በኦሮሚያ ክልል በማዕድን ፍለጋ ሥራ ተሰማርተው ይገኛሉ ብለዋል:: ከዚህም ባሻገር ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር በመሥራት የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ኢቫን ጄ ክሊፎርድ አስረድተዋል::

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You