አዲስ አበባ፡- በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት ከ13 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አመራሮችና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለመስጠት ማቀዱን አዲስ አበባ አመራር አካዳሚ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ፕሬዚዳንት ጣሰው ገብሬ (ዶ/ር ) ለኢፕድ እንደገለጹት፤ አካዳሚው የከተማውን የአመራርና የባለሙያውን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ለማጎልበት እየሠራ ሲሆን በተያዘው ዓመትም ከ 13 ሺህ ስድስት መቶ በላይ ለሚሆኑ አመራሮችና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ይሰጣል፡፡
ሥልጠናውም የአመራር ልማትን ትኩረት ያደረገ የዳሰሳ ጥናትን በማዘጋጀት በከተማው ለሚገኙ 5 ሺህ አዳዲስ ተሿሚ አመራሮች፣ ለ2 ሺህ 8 መቶ በላይ ባለሙያዎች፣ ለ5 ሺህ 834 ዳይሬክተሮች የሚሰጥ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የአቅም ግንባታ ሥልጠናው አገልግሎት አሰጣጥ፣ በመልካም አስተዳደር፣ የችግር አፈታት፣ አዲስ አስተሳሰብና ዘመናዊ አሠራሮችን መከተል እንዲሁም የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ የሚያተኩር መሆኑን ጠቅሰዋል።
መሪዎች የሥራ አቅጣጫ የሚያስቀምጡና የሚያስተገብሩ ብሎም ውሳኔ የሚያሳልፉ በመሆናቸው ብቃት ያለው የአመራር ክህሎት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም አካዳሚው በሚሰጠው ሥልጠና የተሰጣቸውን የሕዝብ ተልእኮ በተሻለ እውቀትና ግንዛቤ ለመወጣት ያስችላል ብለዋል፡፡
ዶክተር ጣሰው እንደገለጹት፤ በአካዳሚው የሚሰጡ ሥልጠናዎች ሠልጣኞች መልካም የሥራ ሥነምግባር እና የአገልጋይነት መንፈስ እንዲኖራቸው በማድረግ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋለውን ችግር በመፍታት የከተማዋን ዘመናዊነትና እድገት የሚመጥን አመራር እና ባለሙያ ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡
እስካሁን ባለው ሂደትም አካዳሚው 77 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአመራርና ባለሙያዎች ሥልጠና ከመስጠቱ በተጨማሪ 46 ችግር ፊቺ የጥናትን ምርምር እና ከ7 በላይ የማማከር ሥራዎች የሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አንድ ተቋም ሊያድግ የሚችለው በአመራሩ ወይም በመሪው ልክ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለዚህም አካዳሚው የትግበራ ክፍተት በመድፈን እና የሥራ ግልጸኝነት በማስፈን በከተማው በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች በተሻለ እውቀትና የአቅም ማጎልበት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
እንዲሁም አካዳሚው በተያዘው በጀት ዓመት በከተማዋ ብቁ የሆነ አመራርና ባለሙያ ለመፍጠር እየሰጠ የሚገኘውን ሥልጠና ተደራሽነትና ጥራት ለማሳደግ በተጨማሪ ለከተማው ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር እንደሚሠራ ዶክተር ጣሰው አስታውቀዋል፡፡
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም