የአደባባይ በዓላት ለገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው

– በመዲናዋ በ2017 አንድ ሚሊዮን የውጭ ቱሪስቶችን ለመቀበል ታቅዷል

አዲስ አበባ፡- የአደባባይ በዓላት ለገጽታ ግንባታና የልማት ሥራዎችን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡ በ2017 በጀት ዓመት በመዲናዋ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ለመቀበል መታቀዱ ተመላክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃፍታይ ገብረእግዚአብሔር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ በመስከረም ወር በድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት መካከል የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት ይገኙበታል፡፡

የመስቀል ደመራ በዓልን ለመታደም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ብዙ እንግዶች ተገኝተዋል ያሉት አቶ ሃፍታይ፤ ኢሬቻን በዓል ለመታደም ደግሞ ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችና ከዓለም ሀገራት በርካታ ቁጥር ያላቸው እንግዶች ወደ ከተማዋ ይመጣሉ ብለዋል፡፡

ይህም የከተማዋን ገጽታ ለመገንባት፣ የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት እና አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችና የልማት ሥራዎችን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የመስቀል ደመራ በዓልን ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን የየራሳቸውን የባህል አልባሳትና ጌጣጌጥ ለብሰው እንዲሁም የተለያዩ የዓለም ሀገራት ቱሪስቶች የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እና የአንድነት ተምሳሌት ወደሆነችው አዲስ አበባ በመምጣት ማክበራቸውን አስታውሰዋል፡፡

የመስቀል ደመራ በዓል ለከተማዋ ገጽታ ግንባታና ኢኮኖሚያዊ እድገት ካበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባለፈ ሕብረ ቀለማችንን፣ ውበታችንንና አንድነታችንን በአደባባይ ለዓለም ሕዝብ አሳይተናል ነው ያሉት፡፡

የአደባባይ በዓላት ሲከበሩ ጫማ ከሚጠርጉ ዜጎች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ድረስ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከፍ የሚያደርጉበት ሁኔታ እንደሚፈጠር አስታውቀዋል፡፡

በመጪው ቅዳሜ የሚከበረው የኢሬቻ በዓልም በዓለም ከኢትዮጵያውያን አልፎ የዓለም ጸጋ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በዓሉን ለመታደም ከየትኛውም አቅጣጫ የሚገቡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል በመቀበል የከተማዋን ገጽታና ኢኮኖሚ ለማሳደግ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

የአደባባይ በዓላት በከተማዋ የተሠሩና እየተሠሩ ያሉ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎችን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ገልጸው፤ ኢሬቻን ለማክበር ለሚመጡ እንግዶች ሆቴሎች የምግብ፣ የመኝታ እና የሚጎበኙ ቦታ ጥቅሎችን ለማዘጋጀት እየሠሩ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ቢሮው ቱሪስቶች ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ድጋፍና ክትትል የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

ከተማ አስተዳድሩ ከሰላምና ጸጥታ፣ የበዓሉን እሴት ከማስተዋወቅና ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንጻር ከላይ እስከታች ባሉ አደረጃጀቶች በኩል በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች የአዲስ አበባን በአጭር ጊዜ የመልማት ውጤት አይተውና ተገንዝበው በሚመጡበት አካባቢ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ከተማዋን እንዲጎበኙ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለበዓሉ ተሳታፊዎች በህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦችን በማሳየትና በመሸጥ እንዲሁም ከተማዋን በማስጎብኘት ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢሬቻ በዓል ሲከበር የከተማው ነዋሪ በእኔነት ስሜት በዓሉን በጋራ እንዲያከብር፣ እንግዶችን በአግባቡ እንዲቀበል እና የከተማዋን ገጽታ ከፍ የሚያደርግ ሥራ እንዲሠራም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል በ2017 በጀት ዓመት በመዲናዋ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ለመቀበል ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You