«ኢትዮጵያ ትላንትም ዛሬም ስደተኞችን በአግባቡ የምታስተናግድ ሀገር ናት» -አቶ ብሩህተስፋ ሙሉጌታ

አቶ ብሩህተስፋ ሙሉጌታ-በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር

ስደት የሰው ልጆችን ለመከራ የሚዳርግ የኖረ ያለና ምን አልባትም የሚቀጥል ክስተት ነው። ሰዎችን በተለያዩ ምክንያቶች የትውልድ ቀዬያቸውን ጥለው በብዙ መከራና ስቃይ ውስጥ ርቀው እንዲሄዱ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች በርካቶች ናቸው። የሰላም እጦት፤ ስራ አጥነት፤ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ የፖለቲካ አለመረጋጋት ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል። ያም ሆነ ይህ በተለያዩ ምክንያቶች ሀገራቸውን ለቀው የወጡ ሰዎች መጠኑ ቢለያይም ለዘርፈ ብዙ አካላዊ፤ ስነ ልቦናዊና ሰብአዊ ጉዳት መዳረጋቸው አይቀሬ ነው። ለመከራ የሚዳርጓቸው አካላት ደግሞ በዋናነት ስደተኞችን በሕገ ወጥ መንገድ የሚያንቀሳቅሱ አካላት ቢሆኑም በየተጠለሉባቸው ሀገራት የሚገጥሟቸውም ችግሮች መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የስደተኞቹ እጣ ፈንታ የሚወሰነው በየደረሱበት ወይንም ጥገኝነት በጠየቁበት ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ነው። የእነዚህ ሀገራት ያለበት የሰላም ሁኔታ፤ ስደተኞችን ተቀብሎ የሚያስተናግድበት ሕግና ትግበራ ነገሮችን በደግም ሆነ በክፉ የሚወስን ይሆናል። ለዚህም ነው አንዳንዶች ከሀገራቸው ብዙም ሳይርቁ በየጎረቤት ሀገራት የመከራ ጥግ የተባሉ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችን ለማስተናገድ ሲገደዱ የምናየው። ሌሎች ደግሞ ባሕር ተሻገረው ውቅያኖስ አቋርጠው የዓለም ዳርቻ የሚመስል ቦታ ደርሰው ስደት ከዘመድና ከወዳጅ ከመለየት ባለፈ እዚህ ግባ የሚባል ችግር ሳያደርስባቸው ይቀራል። ይልቁንም ያማረ የተሻለ ሕይወት መኖር ይጀምሩና በሀገራቸው ያሉ ወገኖቻቸውን ልብ ለስደት እስከ ማማለል ይደርሳሉ።

ኢትዮጵያ እንደሌላው ታሪኳ ሁሉ ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ ረገድም ዓለም የመሰከረው የረዥም ዘመን ታሪክ ያላት ሀገር ናት። ስሟ የሚነሳው ደግሞ ከነገስታቷም ሆኑ ከሕህዝቦቿ ለእንግዶች በሚሰጡት ፍቅር ነው። ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያ መንግስት የተለያያ ችግሮች ገጥመዋቸው ከጎረቤት ሀገራት የሚጎርፉትን ስደተኞች ስብእናቸውን ክብራቸውን ጠብቆ ለማስተናገድ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን ሀገሪቷ ስደተኞችን በመቀበል ብቻ ሳይሆን በመላክም ስሟ ሲነሳ ይስተዋላል። በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ መንገዶች ከሀገር ይወጣሉ።

የእነዚህም ኢትዮጵያውያን የመጨረሻ እድላቸው የሚወሰነው በየደረሰቡት ሀገር የእንግዳ ተቀባይነትና እነሱን የተመለከቱ ሕጎች ይሆናል። ባጭሩ ባሉበት ሀገር እንዲቆዩ አልያም ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል። በተመሳሳይ መንግስት በዚህ አይነት ከሀገራቸው የወጡ ኢትዮጵያውያንን ከስደት ተመላሾችንም ለማስተናገድ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል። እኛም ለዛሬው ዝግጅታችን በአሁኑ ወቅት በኢትይጵያ በዚህ ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የጥበቃና ከስደት ተመላሾች ዘርፍ መሪ አቶ ብሩህ ተስፋ ሙሉጌታ ጋር የነበረንን ቆይታ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከለላና ጥበቃ እየተሰጣቸው ያሉት ስደተኞች ከሀያ ሰባት ሀገራት የመጡ ሲሆን ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ከጎረቤት ሀገራት የመጡት ናቸው

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተቀባይነት ምን ይመስላል ?

አቶ ብሩህ ተስፋ፡ስደኞችና ተመላሾች አገልግሎት በዋናነት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍና በአህጉር አቀፍ መድረክ የተቀበለቻቸውንና የፈረመቻቸውን ስምምነቶች መሰረት በማድረግ የሚሰራ ነው። ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ በሀገር ውስጥ የተዘጋጁ ሕጎች አሉ። እነዚህን መሰረት በማድረግ ነው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ስደተኞች ይስተናገዳሉ። እነዚህ ስደተኞች በሀገራቸው ጥበቃና ከለላ ሊደረግላቸው ያልቻሉና የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን ለማግኘት የጠየቁ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከለላና ጥበቃ እየተሰጣቸው ያሉት ስደተኞች ከሀያ ሰባት ሀገራት የመጡ ሲሆን ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ከጎረቤት ሀገራት የመጡት ናቸው። ስደተኝነት የሚሰጣቸው በአብዛኛው በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶችን ጨምሮ በሀገራቸው መንግስት ከለላ ማግኘት ላልቻሉ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን የስደት ተመላሾችም የሚስተናገዱ ይሆናል። ኢትዮጵያዊ ከስደት ተመላሾች የሚባሉት በሌሎች ሀገራት በስደተኝነት ተመዝግበው ይኖሩ የነበሩ ናቸው። እነዚህን ስደተኞቸ በተመለከተ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የማድረግ በሀገር ውስጥ የሚኖራቸውን ቆይታና የማቋቋም ስራ ሁሉ የሚከናወነው በአገልግሎቱ በኩል ነው። አገልግሎቱ እነዚህን ስራዎች የሚያከናውነው ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ተቋማት ጋር በመቀናጀትም ነው።

አዲስ ዘመን፤ ኢትዮጵያ ለስደተኞች የምትሰጠው ከለላና ጥበቃ ምን ይመስላል ?

አቶ ብሩህ ተስፋ፡- ለስደተኞች ከለላና ጥበቃ ይሰጣል ሲባል በቀዳሚነት የሕግ ከለላን የአካል ጥበቃን ጨምሮ ለስደተኞች ተደራሽ ማድረግን ይመለከታል። ይህም የሚጀመረው ከምዝገባ ሲሆን ጥገኝነትም ሆነ ስደተኛ በሚለው የሚያገኙት መብት ተመሳሳይ ይሆናል። ከምዝገባው በኋላ በቀጥታ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ የሚከናወን ይሆናል። ከዚህም ውስጥ የመጀመሪያው አገልግሎት መሰረታዊ ፍላጎት ማለትም የጤና፤ የትምህርት፤ ስራ የማግኘትን ማሟላት ነው።

ስደተኞች ጥበቃ የሚደርጋላችው በሶስት አይነት መንገድ ነው። አንደኛው በካምፕ ለብቻቸው አንድ ቦታ ሰፍረው እንዲቆዩ በማድረግ የመጠለያ፤ የንጽህና የምግብ አካላዊ ጥበቃ ይደረጋል። በቅርብ ርቅት ማሕበረሰብ የሚኖር ቢሆንም እነሱ የሚኖሩት ግን በተለየ ቦታ ብቻ ይሆናል። ይህም ማለት ስደተኞቹ በአንድ ግዜ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሆነው ወደሀገር ቤት ስለሚገቡ በተለየ ቦታ አስፈላጊው ሁሉ መሰረተ ልማት እንዲሟላ ተደርጎ የሚስተናገዱበት ነው። ከመጠለያ ባለፈ የራሳቸው የጤና፤ የትምህርት መሰረተ ልማቶች ይሟሉላቸዋል። ይህ የሚደረገው በድንበር አካባቢ ብዙ ግዜ በቂ መሰረተ ልማት ባለመኖሩና የስደተኞቹም ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ በሳይት ወይንም እንደገና ማስፈር የሚባለው ነው። እነዚህም በቀጥታ እንደመጡ የሚያርፉት ከማሕበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ በመሆናቸው የሚሰጣቸው አገልግሎት ከማሕበረሰቡ ጋር ተዳምሮ ይሆናል። የተሰጣቸውን መታወቂያና ሌሎች ዶክመንቶች መሰረት በማድረግ ጥበቃና ከለላን ጨምሮ ከማሕበረሰቡ ጋር በአንድ ላይ ይሆናል ማለት ነው። ለኑሮ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችንም በተመለከተ እንደ አዲስ መስራት ሳይሆን ያሉትን የማሳደግ ስራ ብቻ የሚከናወን ይሆናል። ለምሳሌ ስደተኞቹ የተቀላቀሉት ማሕብረሰብ ውስጥ ያለ አንድ ትምህርት ቤት ሶስት ሺ ተማሪዎችን የሚያስተናግድ ይሆናል። ተጨማሪ የትምህርት አገልግሎት የሚፈልጉ ሁለት ሺ ስደተኞች ቢጨመሩ እነሱን የሚችል ማስፋፊያ ይገነባል፤ ሌሎች የትምህርት ቁሳቁስና የሰው ኃይልም ይሟላል ማለት ነው።

ሶስተኛው የስደተኞች አጠባበቅ ደግሞ ከካምፕ ውጪ እንዲኖሩ የሚደረግ ሲሆን በከተሞች የሚተገበር ነው። በአዲስ አበባና ከዚህ ቀደምም በትግራይ መቀሌና ሽረ ላይ ይኖሩ እንደነበሩት ያሉትን የሚያካትት ይሆናል። እነዚህ ስደተኞች ራሳቸውን ማስተዳደር የሚችሉ መሆናቸውና ሌላ እነሱን ሊደግፍ የሚችል አካል ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ሲኖር በጥገኝነት ለመኖር ጠይቀው እድሉ የሚሰጣቸው ናቸው። ነገር ግን እድሉ ራሳቸውን ማስተዳደር ስለቻሉ ወይንም የሚደግፋቸው አካል ስላለ ብቻ አይሰጣቸውም። የተለያዩ ተጨማሪ መስፈርቶች ያሉ ሲሆን የሚሰጠውም እድል ብዛት ውሱን ነው። ይህም ሆኖ የተለየ ከለላ ሊያስፈልጋቸው የሚሰጣቸው ሲሆን ሕክምና፤ የትምህርት እድል ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ሊያገኙ የሚችሉበትም ሁኔታ አለ። በዚህ አይነት በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ብቻ የሚገኙት ስደተኞች ሰማኒያ አንድ ሺ ይደርሳሉ።

አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተም የመጠለያ፤ የምግብ፤ የውሃ የንጽህና መጠበቂያ፤ የጤና የትምህርት አገልግሎቶች ተደራሽ የሚደረጉት ከዓለም አቀፍ ድጋፍ አድራጊ ተቋማት ጋር በመሆንም ነው። ከትምህርት ጋር በተያያዘም በካምፕ ለሚኖሩ እስከ ሁለተኛ ደረጃ በዛው በካምፑ ውስጥ የሚሰጥ ሲሆን ከካምፕ ውጪ የሚኖሩት ደግሞ ከማሕበረሰቡ ጋር በአንድ ላይ ሁኔታዎች እየተመቻቹላቸው እድሉን የሚያገኙ ይሆናል። ሁለተኛ ደረጃና ከዛ በላይ ማለትም ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ከሆነ ግን ከኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ጋር ተወዳድረውና ተፈትነው ካለፉ እንደማንኛውም ዜጋ የሚስተናገዱ ይሆናል። በተመሳሳይ የጤና ጣቢያዎች በየካምፖቹ የሚዘጋጁ ሲሆን እነዚህ ተቀባይ ማሕበረሰቡንም የሚያስተናግዱ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፤ ኢትዮጵያ ስደተኞችን የምታስተ ናግድበት መንገድ ከዓለም አቀፍ ሕጎች ጋር እንዴት ይታያል።

አቶ ብሩህ ተስፋ፡ በኢትዮጵያ ስደተኞች የሚስተናገዱት ጥሩ የሚባሉ የተዘጋጁ ሕግ መመሪያና ደንቦች አሉ። እነዚህ ሕግ መመሪያና ደንቦች ከዓለም አቀፍ ሕጎች ጋር የተናበቡና ዘመኑንም የሚዋጁ ናቸው። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ለስደተኞች ከለላ ስትሰጥ የምታደርገው ምዝገባ በዓለም አቀፉ ደረጃ ለሚንቀሳቀሱት አካላት ተደራሽ ስለሚሆን ከለላውም ዓለም አቀፍ ይሆናል ማለት ነው። ኢትዮጵያ በተባበሩት  መንግስታት ድርጅት ስር ያለውን ቻርተር ሙሉ ለሙሉ ተቀብላ ፈርማለች። በመሆኑም አንድ ስደተኛ ኢትዮጵያ በሕጋዊ መንገድ ከተቀበለችው ግዜ ጀምሮ የተሰጠው ከለላና ጥበቃ ወደ ሌሎች ሀገራት ሲንቀሳቀስም እንደተጠበቀ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ የሚካሄዱ መድረኮችን መሰረት አድርጎ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ የሚሰሩ ስራዎቸም ይኖራሉ ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ስደተኞችን የመቀበልና የማስተናገድ አካሄድ ከሌሎች ሀገራት አኳያ ሲታይ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል ?

አቶ ብሩህ ተስፋ፡– ከሌሎች ሀገራት ጋር በማነጻጻር ኢትዮጵያ ስደተኞችን የምታስተናግድበት መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተቀመጡ መብቶች አኳያ ተቀራራቢ ነው ለማለት ይቻላል። ይህ የሚሆነው ደግሞ መጀመሪያ ስደተኞች በተጠለሉበት ሀገር በሚኖራቸው ቆይታ አካላዊ ስነ ልቦናዊና ሰብአዊ መብቶች መጠበቅ። ከዚህ ውስጥ ስነ ልቦናዊ ጥበቃዎችን በተመለከተ በአጋጣሚ በኢትዮጵያ ከሚገኙት ስደተኞች አብዛኛዎቹ ቋንቋቸው በሀገር ውስጥም የሚነገር ነው። ይህም በማሕበረሰቡ ውስጥ የሚኖረውን ተመሳሳይና ተቀራራቢ ባሕልና ሀይማኖት ስለሚኖራቸው ግንኙነቱ የተስተካከለ እና ጠንካራ መስተጋብር ያለው ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ አለው። በዚህ መስፈርት አሁን ያለውን ሁኔታ ስንመለከት በሀገር ውስጥ ካሉት ስደተኞች ትልቁን ቁጥር የሚይዙት ማለትም ሀምሳ በመቶ የሚደርሱት ስደተኞች ከደቡብ ሱዳን የተፈናቀሉ ናቸው። የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ከጋምቤላ ጋር አኙዋክ እና ንዌር እንዲሁም ሙርሌ ጋር የሚመሳሰሉና አንድ አይነት ናቸው።

በሌሎቹም የሀገሪቱ ጠረፍ አካባቢዎች በሱማሌ ክልልና ሱማሊያ ሀገር በትግራይና በኤርትራ እንዲሁ ተመሳሳይ ነው። በመሆኑም አብዛኞቹ ስደተኞች በድንበር አካባቢ ከሀምሳ እስከ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ለይ በጥሩ ሁኔታ ሲኖሩ ይታያል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ መሆኑ ዓለም የመሰከረለት ሀቅ ነው። በሺዎች ዓመታት የሚቆጠረው የረዥም ዘመን ታሪኩም የሚያሳየው ይህንኑ ነው። በዚህም የተነሳ ዛሬም ድረስ ከየትም ሀገር መጥቶ ቢሆን ስደተኛ ሆኖ በየትኛውም የሀገሪቱ ክልል የሚንቀሳቀስ ሰው በማንነቱ የሚደርስበት ምንም አይነት መጥፎ ነገር ኖሮ አያውቅም። ለዚህም እንደ አንድ ጥሩ ማሳያ መጥቀስ የሚቻለው በኢትዮጵያ በስደት ወደ ሀገር ውስጥ በቅርብ ግዜ ከገቡትና እየገቡ ካሉት በተጨማሪ አርባ ዓመታት ድረስ የቆዩ እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በነጻነት የሚኖሩ ግለሰቦች ያሉ መሆናቸው አሉ።

አዲስ ዘመን፡- አገልግሎቱ ከስደት ተመላሾችን የሚያስተናግደው እንዴት ነው። ከስደት ተመላሾች የሚባሉት ኢትዮ ጵያውያንስ እነማን ናቸው።

አቶ ብሩህ ተስፋ፡- ከስደት ተመላሽ ተብለው የሚለዩት በሌሎች ሀገራት በስደተኝነት ተመዝግበው የነበሩና ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኙት ናቸው። እነዚህን ወደ ሀገር ቤት በመመለስም ሆነ ሀገር ውስጥ ከደረሱ በኋላ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸው የሚቆዩበትና በዘላቂነት መልሶ የማቋቋም ስራ የሚከናውንም ይሆናል። እነዚህ ስራዎች የሚከናወኑትም ከተለያዩ የባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን ነው። በዚህ ሂደት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀዳሚውን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን ኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በየደረጃው የስደት ተመላሾቹ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ቡድን አቋቁሞ የማረጋገጥ ስራ የሚያከናውኑ ይሆናል።

የስደት ተመላሾቹ በዚህ አካሄድ ኢትየጵያዊ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ሊሴ ፓሴ የይለፍ ፈቃድ ይሰጣቸዋል። ስደተኞቹ ወደ ሀገር ቤት ከገቡ በኋላ የመጀመሪያ ስራ የሚሆነው በግዜያዊነት የሚያርፉበት ቦታ ማመቻቸት ነው። ከዚህ በተጓዳኝ በግዜያዊነት በሚቆይበት ወቅት ኃይል ሰጪ ምግቦችን እንዲያገኙና የጤና አገልግሎትም እየተሰጣቸው ለአንድም ሆነ ለሁለት ወር ሁኔታዎች እንዲመቻቹላቸው የሚያደርግ ይሆናል።

ከዚህ በመቀጠልም ወደ ቀያቸው ተመልሰው በቋሚነት እንዲቋቋሙ ድጋፍ ከሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የሚሰሩ ስራዎች ይኖራሉ። ወደቀያቸው ከተመለሱ በኋላ ጥበቃና ከለላ ተደርጎላቸው እንዲቋቋሙ የሚሰሩ ስራዎች አሉ። ይህም የሚከናወነው በዋናነት በየአካባቢው ካሉ የስራና ክህሎት ቢሮዎች እና ከቴክኒክና ሞያ ተቋማት ጋር በመሆን ነው። በዚህም ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ የራሳቸውን ስራ እንዲሰሩ እንዲጀምሩ ሁኔታዎች የሚመቻቹላቸው ሲሆን በተጨማሪም በቆይታቸው ለእለት እለት እንቅስቃሴያቸው ቀጥተኛ ድጋፎችን በአይነትም ሆነ በገንዘብ እንዲያገኙ የሚደረግ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ያሉ ስተኞችን በተመለከተ በቂ መረጃ አይያዝም የሚል ሀሳብ ሲነሳ ይደመጣል። ይህንን እንዴት ያዩታል?

አቶ ብሩህ ተስፋ፡መረጃ አያያዝን በተመለከተ ስራው የሚጀመረው የትኞቹም ስደተኞች ከየትም ሀገር ቢመጡ ወደ ሀገር ውስጥ ከገቡበት ግዜ አንስቶ በሚደረግ ምዝገባ ይሆናል። ምዝገባው በተለያዩ ግዜያት እንደሁኔታው አራት ግዜ የሚከናወንም ይሆናል። የመጀመሪያው ምዝገባ እንደተከናወነ በኢትዮጵያ እንደ ስደተኛ መመዝገቡን የሚያረጋግጥለት ሰነድ ለስደተኛው ይሰጠዋል። እድሚያቸው ከአስራ አራት ዓመት በላይ ለሆኑትም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እስካሉ ድረስ ከላይ የተዘረዘሩትን አገልግሎቶች በሙሉ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው መታወቂያም ይሰጣቸዋል።

ምዝገባዎቹ ዳታዎችን ለማቀናጀት የሚጠቅሙ ሲሆን ይህንንም የሚሰጠውን አገልግሎት ፈጣንና ተደራሸ ለማድረግ ይረዳል። ከዚህ በተጨማሪ በእነዚህ ዳታዎች አማካኝነት ስደተኞቹ የልደት፤ የሞት፤ የጋብቻ፤ የፍቺና የመሳሰሉት የወሳኝ ኩነት ምዝገባዎች አገልግሎትም የሚያገኙ ይሆናል። ለተለያዩ ጉዳዮች ተፈልገው እነዚህ መረጃዎች ማረጋገጥ የሚፈልግ አካል ሲኖርም የማረጋገጥ ስራዎች የሚከናወኑ ይሆናል። እነዚህ አገልግሎቶች ተደራሽ የሚደረጉት ከኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትና ስደኞችና ተመላሾች አገልግሎት በሕግ በተሰጡት ስልጣንና ኃላፊነቶች መሰረት ነው። መረጃዎቹም እንደየ ሁኔታው በየወቅቱ የሚታደሱ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ለስደተኞችና የስደት ተመላሾች የስራ አድል ከመፍጠር አኳያ ምን ምን ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።

አቶ ብሩህ ተስፋ፡- ኢትዮጵያ የስደተኞችን ስራ የመስራት መብት በአዋጅ ያረጋገጠች ሀገር ናት። በዚህ ረገድ የሚፈጠሩ የስራ እድሎች በመሰረታዊነትን ስደተኞቹንም ተቀባዩንም ማሕበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ እንዲሆኑ ይጠበቃል። ይህ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው የስራና ክህሎት ሚኒስትርን ሲሆን ከዚህ ጋር እና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር አገልግሎቱ የመግባቢያ ሰነዶችን ተፈራርሟል። ይህንን መሰረት በማድረግ የስራ ፈቃድ የሚሰጥ ይሆናል። በሀገሪቱ ያለው የስራ እድል በቂ ባለመሆኑና ዜጎችንም ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉ ይታወቃል። በመሆኑም የሚፈጠረው የስራ እድል ስደተኞችን መሰረት አድርጎ ነገር ግን ተቀባይ ማሕበረሰብንም ተጠቃሚ የሚያደርግ እንዲሆን ይጠበቃል። እንደ ሁኔታው ለተቀባዩ ማሕበረሰብ የሚሰጠው የስራ እድል ሀምሳ በመቶ አርባ ወይንም ሰላሳ በመቶ ሊሆን ይችላል። በዚህ አይነት የስራ እድል እንዲፈጠር ከዓለም አቀፍ አጋር ደርጅቶች ጋር በመሆን እየተሰራ ይገኛል።

ከስራ እድል ጋር ተያይዞ ሌላው ለስደተኞች የሚኖረው ተጠቃሚነት ራሳቸውን ችለው በተለያየ መንገድ ንግድን ጨምሮ በቅጥርም ሊሰሩ የሚችሉም ይኖራሉ። ነገር ግን ሁሉም ስደተኞች የእነዚህ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ለመሆን በልዩ ሁኔታ የስራ እድሉን እንዲያገኙ ፈቃድ ሊኖራቸው ይገባል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ራሳቸውን ችለው ለሚንቀሳቀሱ የንግድ ፈቃድ እንዲኖራቸው ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የሚሰሩ ስራዎችም አሉ። በአጠቃላይ ባለፈው ዓመት ብቻ ሰላሳ ሶስት ሺ የስራ እድል ተፈጥሯል። ይህ ሲሆንም ለተቀባይ ማሕበረሰቡ በሚሰባሰቡ እርዳታዎች የኢትዮጵያ መንግስት ከመቶ ሚሊየን ዶላር በላይ በቀጥተኛ ድጋፍ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ከዓለም ባንክ አንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል።

አዲስ ዘመን፡- በሀገር ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን ተከትሎ ስደተኞች ለችግር እንዳይጋለጡ ምን ጥበቃ እየተደረገ ይገኛል። እስከ ቅርብ ግዜ በዚህ ረገድ በቂ ጥበቃና ከለላ እየተደረገ አይደለም በሚል ቅሬታ የሚያነሱ አሉ ለዚህ ጉዳይ ያለዎት ምለሽ ምንድን ነው?

አቶ ብሩህ ተስፋ፡በአንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እንደ አካባቢው ማሕበረሰብ ሁሉ ስደተኞችንም መመልከቱ አይቀርም። ነገር ግን በተለይ ከአካላዊ ጥበቃ ከማድረግ አንጻር በካምፕ ከሆኑ በልዩ ሁኔታ ጥበቃና ከለላ የሚደረግላቸው ይሆናል። ከካምፕ ውጪ ከሆኑ ግን ጥበቃ የሚደረግላቸው ከማሕበረሰቡ ጋር ይሆናል። ይህም የሚደረገው በዋናነት በፌደራል ፖሊስ ሲሆን የክልል ጸጥታ አካላትም እንደየአስፈላጊነቱ የሚሳተፉበት አጋጣሚ ይኖራል።

በተጨማሪ በየአንዳንዱ ካምፕ ባሉ ብሎኮች ከራሳቸው ከስደተኞች የተውጣጡ ሰላም ለማስጠበቅ የሚንቀሳቀሱ የጸጥታ አደረጃጀቶችም ይኖራሉ። እነዚህም የውሎም ሆነ የአዳር ሁኔታዎችን በየእለቱ ለሚመለከተው አካል ተደራሽ የሚያደርጉ ይሆናል። ይህንን መሰረት በማድረግ መስተካከል ያለበትም ነገር ካለ ከአካባቢው አስተዳደሮች ጋር በመምክር በየወቅቱ ተገቢው ጥበቃና ከለላ የሚሰጥ ይሆናል። በቅርቡም በሱዳን የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከኢትዮጵያ ከለላ ለማግኘት የመጡ ለሱዳንና ጥቂት የሌሎች ሀገራት ዜጎች የኢትዮጵያ መንግስት በልዩ ሁኔታ የሰጠውና እየሰጠ ያለው ጥበቃ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።

ይህ እንደ ተጠበቀ ሆኖ በኢትዮጵያ ለስደተኞች እየተደረጉ ያሉ ከለላንና ጥበቃዎችን በተመለከተ በአንዳንድ ሚድያዎች የሚነዙ ጕዳዮች እውነት አይደሉም። እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ስድተኞችን ዓላማ ያደረገ ጥቃት ተፈጽሞ አያውቅም። ከካምፕ ውጪ ሆነው በሚንቀሳቀሱበት ግዜ የሚፈጠር ነገር ቢኖር እንኳን ችግሩ ወይንም ጥቃቱ ስደተኞችን ብቻ የተመለከተ ሳይሆን ተቀባዩን ማሕበረሰብ የሚያካትት ይሆናል።

ይህም ሆኖ በአገልግሎቱ በኩል ስደተኞች ግጭቶችና አንዳንድ አስጊ ሁኔታዎች ሲኖሩ እንዳይንቀሳቀሱ ምክር ይሰጣል። በቅርብ ግዜያት በአንዳንድ ቦታዎች የነበሩ ግጭቶችን ተከትሎ ስደተኞችን ለመጠበቅ በተከናወኑ ስራዎች አስራ አንድ ፌዴራል ፖሊስ አባላት የሞቱ ሲሆን አስራ ሶስት ቆስለዋል። ከስደተኞች ወገን ግን አንድም ሰው ላይ ለጉዳት አልደረሰም ነበር።

ከዚሀ ጋር በተያያዘ ጥበቃና ከለላን በተመለከተ የሚነሱ ጉዳዮች የስደተኞችን ብዛት የሚመለከቱም ናቸው። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ተቀብላ እያስተናገደቻቸው ያሉ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥሩ በየቀኑ የሚጨምር ቢሆንም እስካሁን ተመዝግበው ያሉት ከአንድ ሚሊየን አንድ መቶ ስልሳ ሺ በላይ ደርሰዋል። እነዚህን ሁሉ ስደተኞች በአግባቡ መያዝና ማስተናገድ የተቻለው በመንግስት በኩል ጠንካራ መዋቅርና የክትትል ስራዎች ማድረግ በመቻሉ ነው። በተጨማሪ እንደ ሴቶች ፤ ሕጻናት አካል ጉዳተኞችና ሌሎች ልዩ ጥበቃና ድጋፍ የሚደረግላቸው ስተደኞችም አሉ። ይህ የሚደረገውም በተለየ መንገድ ከሌላው በተለየ ለችግር ተጋላጭ ሊሆኑ ስለሚችሉ ነው። ለእነዚህ ስደተኞች ከልዩ ጥበቃና ከለላ ባለፈ የመሰረታዊ አገልግሎት ተደራሽ ሲደረግም ቅድሚያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲሁም የምክርና የድጋፍ አገልግሎቶች እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም ስደተኞችን በአግባቡ የምታስተናግድ ሀገር መሆኗ በግልጽ የሚታይ ነው።

አዲስ ዘመን አመሰግናለሁ

አቶ ብሩህ ተስፋ፡እኔም አመሰግናለሁ

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You