ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ያልሰራነውና መስራት ያለብን ምንድ ነው?

የአፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካ የየሀገሪቱ መሪዎችና ፖለቲካ በሞቀና በቀዘቀዘ ወቅት የተለያየ አሰላለፍ እየያዘ በተለያዩ ጊዜያት ከወቅቱ ጋር ይዘቱንና ቅርፁን ይቀያይራል፡፡ በየጊዜው ቀጠናውን እንቅልፍ ለመንሳት የሚደራጁና የሴራ አስፈፃሚነቱን ሚና የሚረከቡና እሳት ለኩሰው ቤንዚን የሚያርከፈክፉ ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ቀጠናው ላይ የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖችም በትጥቅና በፋይናንስ የሚደግፋቸው አይቸገሩም፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ከመልካምድራዊ፣ ጆኦ-ፖለቲካዊ፣ ስትራቴጂካዊ ፋይዳው አንፃር የሃያላን አገራት ጣልቃ ገብነት ጎልቶ ይታይበታል፡፡ ተገዳዳሪዎቹን አሜሪካና ቻይናን ጨምሮ በርካታ የሩቅና የቅርብ ተዋንያን የጦር ሠፈሮቻቸውን ያደራጁበትም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጂኦግራፊካል መገኛም በዚሁ የተጨነቀ ቀጠና መሃል Nucleus ውስጥ ነው፡፡ የዚህ የፖለቲካ ድባብና ሁኔታም አገሪቱም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ይነካካታል፡፡ ቀጠናው ላይ የተለኮሰ እሳት ኢትዮጵያንም ይጠብሳታል፡፡ ከጥንት እስከ ዘመናዊ የዲፕሎማሲ መስተጋብር የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ማእከላዊ መሰረቶች ወይንም Determinant ዋነኛው ይህ ቀጠና ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ውጥረት ለአፍታም በማይለየው ቀጠና ውስጥ ጥበብ በተሞላበት መልኩ ብሔራዊ ጥቅምን አስጠብቃ ዘመናትን አሳልፋለች፡፡ ይሁንና አገሪቱ ቀጠናው ላይ አቅም እንዳትፈጥር አለን የሚሉትን ሁሉ ለማዋጣት የሚሽቀዳደሙ አገራትም በቅርብም ሆነ በሩቅ በርካቶች ናቸው፡፡

አገሪቱ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ካስጀመረች ጊዜ አንስቶ ባለፉት ዓመታት ያሳለፈችባቸው አባጣና ጎርባጣ የበዛባቸው መንገዶችና በግልጽም ይሁን በስውር የሚስተዋሉ ሴራዎች የነገ ሃያልነትዋን በመረዳት አስቀድሞ ከማስቆም ጋር በእጅጉ የተሳሰሩ ናቸው፡፡

በተለይ ወደ ካይሮ ቤተመንግስት የሚገቡ ሰዎች ሁሉ የወንዙን ውሃ ባልተፈለገ መንገድ የፖለቲካ አጀንዳ በማድረግ፤ በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ሊኖራቸው የሚችለውን ዘላቂ የጋራ ተጠቃሚነት ዕድል ትርጉም ወደሌለው የጠላትነት እና የግጭት መነሻ ለማድረግ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲንቀሳቀሱ ታዝበናል፡፡

በተለይም የለውጡ መንግስት እጅግ ጥበብ በተሞላበት አካሄድ ሕዳሴ ግድብን ከምዝበራ እንዲሁም ግንባታውን ከሞተበት እንዲያንሰራራና ከሞት ተነስቶ የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ማመንጨት እንዲሸጋገር ያተደረገበት ሂደት የካይሮውን መንግስት ከማስደንገጥ አልፎ ማመን ተቸግሮ እግሩ ወደ መራው እንዲሮጥ ሲያስገድደውም እየተመለከትን እንገኛለን፡፡

በቀጠናው በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ተፅእኖ ፈጣሪ መሆን ከሁሉ ቀድሞ የሚያንጨረጭራቸው የፈርኦን ልጆች፣ ኢትዮጵያን የእድገት በሮች እግር በእግር እየተከተሉ መዝጋት የዘወትር መሻታቸው ስለመሆኑ ከቃላቸው በላይ ተግባራቸውም ምስክር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሕዳሴ ግድብ ባሻገር የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት ጥያቄ ተከትሎ ያስነሱት አቧራ በቂ ማስረጃ ሆኖ መቅረብ ይችላል፡፡

እንደሚታወቀው፣ኢትዮጵያ በሁሉም መስፈርት ትልቅ ሀገር ነች፡፡ የሚያሳዝነው ግን ከዓለም የባሕር በር/ወደብ ከሌላቸው ሀገሮች በሕዝብ ብዛት አንደኛ ነች፡፡ አገሪቱን ከቀይ ባሕርና ከወደብ ባለቤትነት ለመግፋት ከውስጥም ከውጭም የተሰራው ደባና ሴራ ሁሌም ቢሆን ትውልድን የሚያስቆጭ ነው፡፡

ወደብ ለአንድ ሀገር ማሕበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካው እድገት ወሳኝ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለከፍተኛ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑ አገራት በሙሉ የወደብ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ከድህነት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት መተንፈሻን ማስፋት የግድ ነው፡፡

ኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት መሆን ባለመቻሏ ኢኮኖሚው ክፉኛ ታፍኖ ቆይታል፡፡ ችግሩ አገሪቱ በየጊዜው ለወደብ ኪራይ ቢሊዮን ዶላሮችን እንድትከፍል ከማድረግ ባሻገር የምትፈልገውን ገቢና ወጪ ምርት አስተማማኝና ቀልጣፍ በሆነ መልኩ እንዳታስተላልፍ ማነቆ ሆኖባታል፡፡

ቀጠናው ላይ በዝሆኖች መካከል ግጭት ሲነሳም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ እጅጉን ተጎጂ ናት፡፡ ይህ ደግሞ ባሕር በሩን ጥያቄ ከኢኮኖሚ ባሻገር ከሕልውና ከብሔራዊ ደህንነት ጋር በጥብቅ እንዲተሳሰር ያደርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ከሶማሊያ-ላንድ ጋር የተፈራረመችው የባሕር በር ስምምነትም ይህን እሳቤ መሰረት ያደረገ ነው።

ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበትን የመግባቢያ ሥምምነት የአገሪቱንን መጻኢ ዕድል የሚያሳምር ከመሆኑም በላይ ለዘመናት ወደብ አልባ ለሆነው ሕዝብ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ የተገኘው የባሕር በር የኢትዮጵያን ስብራት የጠገነና የትውልድን የዘመን ቁጭት የመለሰ ነው፡፡ ለሀገራዊ ምጣኔ ሃብት ጡንቻ መፈርጠም እንዲሁም ለብሔራዊ ደህንነታ ዋስትን ያለው አስተዋጽኦ ነጋሪ የሚያሻው አይደለም፡፡

አንድ መታወቅ ያለበት ሀቅ ቢኖር ኢትዮጵያ የባህር በር ብታገኝ የሚጎዳው አካል የለም፡፡ የኢትዮጵያ ፍላጎትም በጋራ ማደግ፣ በጋራ መበልፀግ፣ በጋራ ደህንነትን ማስጠበቅ መሆኑን መረዳት የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን በተለይም ግድቡም በሚመለከት የምታራምደው አቋም ከዚህ በተለየ መነፅር የሚታይ አይደለም፡፡

ይሁንና የመግባቢያ ስምምነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ እድገት የሚያርዳቸው አንዳንድ አገራት ከፍተኛ መደናገጥ ውስጥ የገቡ ሲሆን ‹‹እንዴት ተደርጎ›› በሚል አቧራ ለመስነሳት የቀደማቸው የለም፡፡ የመግባቢያ ስምምነት በአዲስ አበባ ሲፈረም ጩኸቷን የለቀቀችው ሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድም ኢትዮጵያ ላይ ተፅእኖ ለመፍጠር ከላይ እታች ሲሉ ከርመዋል፡፡

በሰኔ ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ (ዶ/ር) በፓርላማ ማብራሪያ ሲሰጡ የሶማሊያ መንግሥት አለመግባባቱን መፍታት ከፈለገ ከሞቃዲሾ ወደ አዲስ አበባ አንድ በረራ በማድረግ ብቻ በንግግር መፍታት እንደሚቻልና ከዚህ በተቃራኒ ከላይ እታች እያሉ የኢትዮጵያን ስም በማጥፋትም ሆነ የመንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር በመሞከር የሁለቱን አገሮች ችግር መፍታት እንደማይቻል አሳስበውም ነበር፡፡

ይሁንና አለመግባባቶችን በውይይት ከመፍታት ባለፈ የቬላ ሶማሊያ ሰዎች የዲፕሎማሲ ግንኙነትን እስከ ማቋረጥ የደረሰ እርምጃ መውሰዳቸውም ይታወሳል። አንዳንድ የሶማሊያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መደበኛም ሆነ ኢመደበኛ በሆኑ መንገዶች ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚሰጧቸው መግለጫዎች መስረተ ቢስ ተራ ውንጀላዎች ከመሆን ባሻገር የሚያስተዛዝቡም ጭምር ሆነው አይተናቸዋል፡፡

ከሁሉ በላይ ግን በሰሶማሊያ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል አገሪቱን ለቆ እንዲወጣ ከመግፋት ባለፈ ጦሩ በግብፅ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲተካ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ቅስቀሳ ሲያደርጉ መመልከት እጅጉን አሳዛኝ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያውያን ለጎረቤት ሀገራት ችግር ቀድሞ መድረስ፤ የሌሎችን ችግር የራስ አድርጎ መመልከት በታሪካቸው ከሚታወቁበት አንዱ መገለጫቸው ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ለሶማሊያ ሕዝብ ካለው ቅርበት /ወንድምነት/ የተነሳም ዓለም አቀፍ፤ አህጉራዊ እና አካባቢያዊ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎችን ወስዶ ሕዝቡ ከጽንፈኛ እና ሽብርተኛ ቡድኖች የሚደርስበት ፈተና ለማቅለል፤ የተሻለ የሠላም አየር እንዲተነፍስ ለማስቻል ብዙ መስዋዕትነት የጠየቁ ወታደራዊ ተልዕኮዎችን ወስዶ በስኬት ተወጥቷል።

ሶማሊያ ሰላምና እንደ ሀገር መቆም የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል የከፈለው የሕይወት፣ የአካልና የንብረት መስዋዕትነት እጅጉን ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ እውነት ቆም ብለው ቢያስቡ የሶማሊያ መንግሥት አመራሮችም በቀላሉ ሊያስታውሱት የሚችሉት ነው፡፡ ይሁንና በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ማስታወስን የመረጡ አይመስልም፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ሁሉ ዓመት ውድ ልጆቻን ስትገብር የት እንደነበሩ የማይታወቁት ፈርኦኖችም ዛሬ ብቅ ብለው ‹‹ሞታችንን ከሶማሊያ ጋር ያድርገው›› እያሉን ነው፡፡ ከአራት አስርት ዓመታት በኋላም ሞቃዲሾ ተገኝተዋል፡፡

ምንም እንኳን ማንም አገር ከማንም ጋር ወዳጅነትም ሆነ ወታደራዊ ትብብር የማድረግ መብት ቢኖረውም፣ በተለይም ይህ አካሄድ በኢትዮጵያ ሠራዊት መስዋዕትነት እንደ አገር ለመቆም ስትውተረተር የኖረችውን ሶማሊያን የበለጠ አዘቅት ውስጥ የሚከት፣ በተለያዩ ግዛቶች እየተነሳ ያለውን ተቃውሞ በማጋጋል ከድኅረ ዚያድ ባሬ የባሰ ትርምስ የሚፈጥርና አልሸባብ ለተባለው አሸባሪ ኃይል አሳልፎ የሚሠጥ ነው፡፡

ይህ ቀድሞ የገባቸው ሶማሊያውያንም ለግብፅ ጓዳቸውን የከፈቱ የቪላ ሶማሊያ ሰዎችን በመቃወም ላይ ናቸው፡፡ አንዳንድ የሶማሊያ ግዛቶች ከወዲሁ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ መከላከያ ጋር መሆናቸውንና የግብፅ ጦር በግዛታቸው ድርሽ እንዳይል፣ የኢትዮጵያ ጦርም እንደማይወጣ እንቅጩን ለሞቃዲሾ ኤርፖርት መሪዎች በይፋ አሳውቀዋል፡፡ ይህን ተከትሎም የግብፅም ሆነ የሞቃዲሾ ሚሊሻ ቀጣይ ሕልውና ቅርቃር ውስጥ ገብቷል፡፡

ሶማሊያ መክተም ብቻውን ኢትዮጵያን አደጋ ላይ ለመጣል በቂ አለመሆኑ የገባት ካይሮ የተባበሩት መንግስታት (ተመድ) ደጃፍ መቆምም አላቋረጠችም። ለድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም በኢትዮጵያ ላይ ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ እንደምትችል የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ጽፋለች፡፡

ይሁንና ምክር ቤት ካይሮ ‹‹ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ላይ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንድታቆም ጫና አድርጉልኝ›› ስትል ያስገባችውን የክስ ደብዳቤ አልቀበልም በማለት አሳፍሯታል። ምክር ቤቱ የሕዳሴ ግድብን ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ሰላማዊ ድርድርን ለማድረግ ፍቃደኛ ሆና ሳለች፤ ውጥረትን መፍጠር እንደማያስፈልግና ጉዳዩ ደግሞ በአፍሪካ ሕብረት በኩል ለመፍትሔው የተሰራበት በመሆኑ እኛን አይመለከተንም በማለት እንደለመደችው ሕፍረቷን ተቀብላ እንድትመለስ አድርጓታል።

ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የካይሮ ወታደራዊ ስምምነትና ከበባ፣ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የማቃቃር ሴራ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሃሰተኛ ክሶች እንደ ትላንቱ ሁሉ ነገም ቀጣይ መሆናቸው የማይቀር ነው፡፡

ዋናው ቁም ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ለአገራችን ብሔራዊ ጥቅም መከበር በአንድነት ለመቆም ምን ያህል ዝግጁ ነን፣ የአገራችን ፍላጎት በአንድነት መበልፀግ ስለመሆኑ በቅጡ ጉረቤቶቻችንም ሆነ ዓለም እንዲረዳው ምን ሰርተናል፣ ምንስ እየሰራን ነው? የሚለው ነው፡፡

አሁን ላይ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እንቅልፍ እንደሌላቸው እያየን ነው፡፡ በአንደበታቸው ጭምር አገራችንን ለማተራመስ እንቅልፍ አጥተው እየተራወጡ መሆናቸውን እየነገሩንም ነው፡፡ ይህ በሆነበት እኛስ ምን እያደረግን ነው፡፡ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ያልሰራነውና መስራት ያለብን ምንድ ነው? ለሚለው ጥያቄ የምንሰጠው ምላሽም እጅጉን ወሳኝ ነው፡፡

ለባህራዊ ጥቅም መከበር ከሁሉ በላይ አንድነት ወሳኝ ነው፡፡ በአገር ጉዳይ ተቃራኒ አቋም መያዝ ለታሪካዊ ጠላት ያጋልጣል፡፡ ውስጣዊ ሰላሙን ያጣ አገር የውጭ ጥቃት መመከት አይቻለውም፡፡ አገርን ከሕልውና አደጋ መታደግ የሚቻለው ሕዝብና መንግሥት ሲናበቡ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ በሁሉም ጎራ ያሉ ኃይሎች ከእነሱ በላይ አገር እንዳለች ማወቅ አለባቸው፡፡ በውስጣዊ ጉዳዮች ስምምነቶች ባይኖሩም፣ በአገር ጉዳይ ግን አንድ መሆንና የውስጥ እንድነትን ማጠናከር ከሁሉም በላይ ለብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም በአንድነት መቆም የግድ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የተለያዩ የዲፕሎማሲ አማራጮችን በመጠቀም የአገርን ጥቅም ለማስጠበቅ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን፣ ውስጣዊ ሽኩቻን በመግታት አንድነትን ማጠናከር ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆን አለበት፡፡

‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ›› እንደሚባለው፣ መንግስትም የአገራዊ አንድነት መደላድሉን በማመቻቸት፣ ጠላትን መግቢያና መውጫ ቀዳዳ ለማሳጣት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በየትኛውም ዘርፍ አገራቸውን ማገዝ ከሚችሉና የዳበረ ዕውቀትና ልምድ ካላቸው ዜጎች ጋር በቅርበት መስራትም ይኖርበታል፡፡

በረቀቀ ዲፕሎማሲና በበሰለ ፖለቲካ ጉዳዩን በአንክሮ እየቃኙ መራመድ በተለይ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራቶች ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ቀድሞ ከነበረው በተሻለ ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ከሶማሊያ ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን በሰላማዊ የዲፕሎማሲ መንገድ መፍትሔ ለመስጠት የተጀመረውን ሥራ ዳር ማድረስም ተገቢ ነው፡፡

ሶማሊያ ሕዝብ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ የክፉ ጊዜ ወዳጅ እንጂ ጠላት እንዳልሆነች የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች መስራትና አሉታዊ ትርክቶችን የማስተካከል ስራ መስራትም ያስፈልጋል። ኢትዮጵያም ሆነች ሶማሊያ በአጠቃላይ የቀጣናው አገሮች ከመተባበር ውጪ መናቆር እንደማይበጃቸው አስረግጦ ማስገንዘብ ብሎም ድርድርና ንግግር መለመድ ያለበት የችግር መፍቻ ባህል እንዲሆን ማድረግም ይገባል፡፡

ከመሰል ቁልፍ ስራዎች ባሻገር የሕዝብ ግንኙነት ስራዎችን ያዝ ለቀቅ ሞቅ ደመቅ በሚል መልኩ ሳይሆን ወጥ በሆነና በተጠና መልኩ የኢትዮጵያን ሰላምና እድገት ፍላጎት እንዲሁም የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ከቀጠናዊ እድገት ጋር ባቆራኘ መልኩ ዘወትር መከወንም የግድ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ያልሰራነው አለና ትኩረት ሰጥተን ልንሰራበትም ይገባል፡፡ ሁሉም በየመስኩ በተለይ የኢትዮጵያ ፍላጎት በጋራ ማደግ፣ በጋራ መበልፀግ፣ በጋራ ደህንነትን ማስጠበቅ መሆኑን ደጋግሞ ማስገንዘብ ላይ የራሱን ጠጠር ሊወረውርም ይገባል፡፡

ሀገሪቷ በሕዝቦቿ ጥረትና ድጋፍ እየገነባች ያለችው የሕዳሴ ግድብ የሕልውናዋ መሰረትና የመሰረታዊ ፍላጎቷ ማሟያ በመሆኑ ግንባታን በፍጥነት ማጠናቀቅም የግድ ነው። ለዚህ ደግሞ መላው ኢትዮጵያዊ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You