በመዲናዋ የተሠሩ መጸዳጃ ቤቶች በተያዘው ወር መጨረሻ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ

አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ ኮሪደር ልማትን ተከትለው የተገነቡት የመጸዳጃ ቤቶች በተያዘው የመስከረም ወር መጨረሻ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ የከተማዋ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የዘላቂ ማረፊያና የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አጃይብ ኩምሳ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት በከተማዋ አምስቱም የኮሪደር ልማት አቅጣጫዎች የተሰሩ መጸዳጃ ቤቶች በተያዘው የመስከረም ወር መጨረሻ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ፡፡

በከተማዋ በአጠቃላይ ወደ አንድ መቶ የሚደርሱ መጸዳጃ ቤቶች ሁሉንም መስፈርት እንዲያሟሉ ተደርገው በፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የተገነቡ ሲሆን፤ አሁን ላይም አስፈላጊ መሠረተ ልማት የማሟላቱ ተግባር እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መጸዳጃ ቤቶቹ የወንድ፣ የሴት፣ የሕፃናት የዳይፐር መቀየሪያ እና የሴቶች የተፈጥሮ ንጽህና መጠበቂያና የእጅ መታጠቢያ ቦታዎችን ያሟሉ ብሎም ከመግቢያቸው ጀምሮ አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ እንዲሆኑ በትኩረት የተሠሩ ምቹ እና ሁሉንም ያካተተ አገልግሎት የሚሰጡ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አገልግሎቱን ለማግኘትም የትኬት መቁረጫ ቦታዎች በነባር የመጸዳጃ ቤቶች ክፍያ ተመን መሠረት እስከ 4 ብር ከፍሎ መገልገል የሚቻል መሆኑን አቶ አጃይብ ተናግረዋል፡፡

የተገነቡት መጸዳጃ ቤቶች ከተማውን ጽዱ የማድረግ ዓላማ በመያዝ ከዚህ በፊት ባልነበረ ሁኔታ የከተማውን ደረጃ፣ ውበት እና የነዋሪውን ክብር ጠብቀው የተገነቡ መሆናቸው የከተማው ለውጥ ነው ማለት ይቻላል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ይህ የከተማዋን ገጽታ የሚለውጥ መጸዳጃ ቤቶች ግንባታ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፤ በዚህ ዓመት የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ ቢያንስ 200 መጸዳጃ ቤቶች ለመገንባት የታቀደ መሆኑን አቶ አጃይብ አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም መጸዳጃ ቤቶች መገንባት የማይቻልባቸው እንደ መገናኛ፣ መርካቶ፣ ሳሪስ፣ አየር ጤና እና ሽሮሜዳ ያሉ ጠባብና ግርግር የሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ 60 ተንቀሳቃሽ መጸዳጃ ቤቶች ለመሥራት የታሰበ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን ባለው ሂደትም 40 የሚሆኑ ተንቀሳቃሽ መጸዳጃ ቤቶች ግዢ የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች የአካባቢን ንፅህና ከመጠበቅ ባለፈ ከተማዋ ካላት ተጽእኖ አንጻር እስካሁን የተገነቡትና ወደፊት የሚገነቡት መጸዳጃ ቤቶች ምቹ እና ለከተማው ውበት ሆነው ሁሉንም የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡

በመሆኑም የተገነቡ መጸዳጃ ቤቶች የከተማዋ አንዱ የውበት መገለጫዎች ስለሆኑ ሁሉም አገልግሎቱን በባለቤትነትና በኃላፊነት መገልገል እንደሚገባ አቶ አጃይብ አሳስበዋል፡፡

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You