አዲስ አበባ፡– ኢሬቻ በኢትዮጵያ የሚገኙ ብዝሃ ማንነቶች፣ አብሮነታቸውንና ወንድማማችነታቸውን የሚያጎለብቱበት በዓል ነው ሲሉ አባ ገዳዎችና ሀዳ ሲንቄዎች ገለጹ።
የኦሮሞ ቱለማ አባ ገዳ ጎበና ሆላ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የኦሮሞ ሕዝብ ክረምት አልፎ ፀደይ ሲመጣ፤ በክረምት ወራት ተራርቆ ሳይገናኝ የቆየ ዘመድ አዝማድ ሲገናኝ፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው።
ኢሬቻ ምስጋና ብቻ ሳይሆን የአንድነት፣ የወንድማማችነት፣ የእርቅና የሰላም በዓልም መሆኑን ገልጸው፤ የኢሬቻ ቀን ከመድረሱ በፊት የተቀያየመ፣ የተጣላ ሁሉ ታርቆ፣ ይቅር ተባብሎ ቂም በቀልን አስወግዶ፤ በኢሬቻ ቀን ፈጣሪ (ዋቃ)ን በማመስገን ከወዳጅ ዘመዶቹ ጋር በዓሉን ያከብራል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከ83 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች በሃይማኖት፣ በዘርና በቋንቋ ሳይለያዩ በራሳቸው መገለጫዎች በአንድነት ይኖራሉ ያሉት አባ ገዳ ጎበና፤ እነኚህ ብዝሃ ማንነቶች በራሳቸው የባህል አልባሳት አጊጠው አንዱ በሌላው ብሔር በዓል በመገኘትና በማክበር አብሮነታቸውን ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።
ከዚህ ውስጥ የኢሬቻ በዓል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የሕዝቦች ወንድማማችነት እንዲጠናከር፣ አብሮነት እንዲጎለብትና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ሲሉ ገልጸዋል።
ኢሬቻ ለሕዝቦች አብሮነት መጎልበት ዓይነተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ባህላዊ ዕሴቶቹ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል።
የሀዳ ሲንቄዎች ጉባኤ አባል ሳራ ዱቤ በበኩላቸው፤ ኢሬቻ የአንድ ሀገር ልጆች በአንድ ቦታ ተሰባስበው ሀገራዊ ዕሴታቸውን የሚያዳብሩበት የወንድማማችነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢሬቻ ዕለት ከተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች በተጨማሪ ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚሳተፉ የአንድ ሀገር ልጆች በአንድነት የሚሰባሰቡበት፤ በፍቅር የሚደምቁበትና የሚጠያየቁበት በዓል መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢሬቻ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚታደሙት ከመሆኑም በላይ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች እና ሃዳ ሲንቄዎች በውብ አለባበስ ደምቀው የሚያከብሩት የውበት በዓል በመሆኑ ከፍተኛ የቱሪዝም ሀብት እንደሆነም አስረድተዋል።
ኢሬቻ በአባ ገዳዎች እና ሃዳ ሲንቄዎች አደይ አበባ እና እርጥብ ሳር በመያዝ ‹‹መሬሆ›› በማለት ሲጫወቱ ወጣቶች ባህላዊ ጭፈራ እና ዘፈን የሚያሳዩበት ባህላዊ የጥበብ መድረክ ነው ያሉት ሀዳ ሲንቄ ሳራ፤ በዚህም ከሀገር ውስጥና ከውጭ በርካታ ቱሪስቶችን በመሳብ ለሀገር ኢኮኖሚ መነቃቃት ከፍተኛ ድርሻ ይጫወታል ብለዋል።
የኢሬቻ በዓል የቱሪዝም ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል ሥርዓቱን በጠበቀ መንገድ ማክበር ያስፈልጋል። የበዓሉ ዕሴት ሳይበረዝ እንዲቀጥል የበዓሉ ባለቤት የሆነው መላው ሕዝብ በፍቅር፣ በሰላምና በአንድነት እንዲያከብረው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም