አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል የገጠሩን ማህበረሰብ ፍትሐዊ የኢነርጂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ 190 ሺህ የተሻሻሉ ዘመናዊ ምድጃዎችን ለማሰራጨት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአማራ ክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጥላሁን ሽመልስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2017 ዓ.ም በአማራ ክልል የገጠሩን ማህበረሰብ ፍትሐዊ የኢነርጂ ተጠቃሚ በማድረግ ጤንነቱ የተጠበቀ እና በኢኮኖሚ ያደገ ዜጋ ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡
በተለይ የገጠሩ ማህበረሰብ ንፁህ ማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ማድረግ የእናቶችና የሕፃናትን ጤንነት ለመጠበቅ፣ ሴቶችን ከፆታዊ ጥቃት ለማዳን ከሚሰጠው ጥቅም በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማሳለጥ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡
ኢነርጂ የአንድ ሀገር ዕድገት ሞተር መሆኑን በመጥቀስ፤ ለሁለተናዊ ዕድገት ሞተር የሆነውን ኢነርጂ ለገጠሩ ማህበረሰብ በፍትሐዊ መንገድ ተደራሽ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በክልሉ ፍትሐዊ የኢነርጂ ተደራሽነትን በማስፈን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ማህበረሰብ ማገዶንና የእንስሳት ቅሪት አካልን ለማብሰያ እየተጠቀመ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነዋሪው ጤንነቱን ለመጠበቅና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱን ይበልጥ ለማሳደግ የተሻሻሉና ኃይል ቆጣቢ ንፁህ የማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት ለገጠሩ ማህበረሰብ የተሻሻሉ ንፁህ የማብሰያ ቴክኖሎጂዎችንና ሶላር ኢነርጂዎችን ተደራሽ ለማድረግ በክልሉ አልፎ አልፎ የሚከሰተው የፀጥታ ችግር ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው ገልጸው፤ 116 ሺህ የተለያዩ ዘመናዊ ምድጃዎችን ተደራሽ የማድረግ ሥራ ተግባራዊ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በመንግሥት አቅም ብቻ የገጠሩን ማህበረሰብ ፍትሐዊ የኢነርጂ ተጠቃሚ ማድረግ አይቻልም፤ ማህበረሰቡን በኢነርጂ ተጠቃሚ ለማድረግ የሶላር ቴክኖሎጂን ለህብረተሰቡ በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ማድረግ የሚችሉ ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሳተፉ፤ ብዛት ያላቸው ባለሙያዎች እንዲሰማሩ የማበረታታት ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ኃይል ቆጣቢ ንፁህ ማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን የሚያመርቱ ወደ 80 የሚጠጉ ሴቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ቴክኖሎጂዎች በስፋት እንዲያመርቱና ተደራሽ እንዲሆኑ ለአምራቾች የገበያ ትስስር የማመቻቸትና የመደገፍ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት 190 ሺህ የተለያዩ ንፁህ የማብሰያ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሁም 190 ሺህ ሶላሮችን ለማህበረሰቡ ለማሰራጨት ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ነው ያሉት አቶ ጥላሁን፤ እቅዱን ማሳካት ከተቻለ 190 ሺህ አባወራዎች ብቻ ሳይሆኑ በስራቸው የሚተዳደረው የቤተሰብ አባል ሁሉ ተጠቃሚ ይሆናል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም