ልማቱ ነዋሪዎችን የዘመናዊ መኖሪያ ቤት ባለቤት ከማድረጉ ባሻገር በምቹ አካባቢዎች የመኖር ዕድልን ይፈጥራል

አዲስ አበባ፡- ልማቱ ነዋሪዎችን የዘመናዊ መኖሪያ ቤት ባለቤት ከማድረጉ ባሻገር ምቹ በሆኑ አካባቢዎች የመኖር ዕድልን የሚፈጥር ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የተገነቡ 75 መኖሪያ ቤቶችን መርቀው ለተጠቃሚዎች አስተላልፈዋል።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የዘመሙ ጎጆዎችን እያቃናን የሚፈሱ እንባዎች ሲታበሱ ማየት እጅግ ደስ ያሰኛል ብለዋል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዊንጌት እና ገብስ-ተራ አካባቢ ደሳሳ የሆኑ የቀበሌ ቤቶችን በማፍረስ ለመኖር ምቹ እና ለሰው ልጅ የሚመጥኑ 75 የመኖሪያ ቤቶች ያላቸው ባለ 5 ወለል(G+5) ሁለት ህንጻዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብተው ለነዋሪዎች በትናንትናው ዕለት መተላለፋቸውን ገልጸዋል።

የተላለፉት ምቹና ፅዱ የመኖሪያ ቤቶች በመሃል   ከተማ የተገነቡ፣ የመጸዳጃና የማብሰያ ቦታ እንዲሁም ሰፋፊ ክፍሎች ያላቸው ሆነው የተለወጡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ቤቶቹ ከዚህ ቀደም ለመኖር ቀርቶ በዚያ ለማለፍ እንኳን ይከብዱ የነበሩ መሆኑን ጠቁመው፤ የመኖሪያ ቤቶቹ ከቦታው ከተነሱ ነዋሪዎች በተጨማሪ ለልማት ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለሚነሱ ዜጎች የሚተርፉ ሆነው በጥሩ ሁኔታ ተገንብተዋል ነው ያሉት።

ልማቱ ነዋሪዎቻችንን የዘመናዊ መኖሪያ ቤት ባለቤት እና ምቹ በሆኑ አካባቢዎች የመኖር እድልን የሚፈጥርላቸው መሆኑንም ገልጸዋል ከንቲባዋ በመልዕክታቸው።

ከንቲባዋ አክለውም ራዕያችንን በመጋራት ቤቶቹን ለመገንባት የደገፋችሁንና ያስተባበራችሁ አካላትን በሙሉ በተለይም የብዙአየሁ ታደለ ፋውንዴሽን፣ መተባበር ለኢትዮጵያ አክሲዮን ማህበር፣ ተምሳሌት በሲዳሞ ተራ አክሲዮን ማህበር፣ ምዕራብ ገበያ ልማት አክሲዮን ማህበር፣ ጉሊት አክሲዮን ማህበር፣ ሸራ ተራ ብርሃን አክሲዮን ማህበር እንዲሁም ጎሽ ንግድና አክሲዮን ግንባታ ማህበርን በተጠቃሚ ነዋሪዎች እና በከተማ አስተዳደራችን ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ ብለዋል።

ስንተባበር የሰው ኑሮ እና አኗኗርን እያሻሻልን ሀገር እንገነባለንና ትብብራችንን አጠናክረን እንቀጥል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You