የቱሪስት ቆይታን ለማራዘም- የአስጎብኚ ባለሙያዎች ሚና

ለቱሪዝም ዘርፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ ከሚታመንባቸው መካከል የአስጎብኚ ባለሙያዎች ይጠቀሳሉ። ባለሙያዎቹ በቀጥታ ከቱሪስቱ ጋር የሚሠሩና በቆይታው ወቅት አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፉ እንደመሆናቸው በበጎም ሆነ በአሉታዊ መንገድ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ከፍ ያለ ነው።

በተለይ ቱሪስቶች በመስሕብና በመዳረሻ ቦታዎች ላይ ለሚኖራቸው የተራዘመ ቆይታ የአስጎብኚዎች ምክረ ሀሳብ እና ሙያዊ ብቃት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። በመሆኑም ዘርፉን በመዳረሻ ልማት፣ በገበያና ማስተዋወቅ ከማደራጀት ባሻገር ብቁና ሙያዊ ሥነምግባር ያለው አስጎብኚም በብዛት ማፍራት ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ባሕላዊና ሌሎች የቱሪዝም መስሕቦች መገኛ ነች። በተለይ በያዝነው የመስከረም ወር የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቶች የቱሪስትን ቀልብ የሚስቡ፣ ሀገሪቱን በበጎ ገፅታ ከማስተዋወቅ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ እድገትን የሚያረጋግጡ ናቸው። ባሳለፍነው ሐሙስና ዓርብ የተከበረውና በዩኔስኮ የዓለም አቀፍ የማይዳሰስ የሰው ልጅ ወካይ ቅርስ ተብሎ እውቅና የተሰጠው የመስቀል ደመራ በዓል የዚሁ የሀገሪቱ ሀብት ውጤት ነው። በቀጣይ ሳምንት ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባና በቢሸፍቱ የሚከበረው የኢሬቻ በዓልም እንዲሁ የዚሁ አካል ነው።

እነዚህን ሀብቶች ለመመልከት በርካታ ቱሪስቶች ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እና ከሀገሪቱ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ይመጣሉ። በተለይ የውጪ አገር ጎብኚዎች የቱር ኦፕሬተሮችንና የጎብኚዎችን ምክረ ሀሳብ ተከተለው፤ ታሪክ፣ ባሕልና ሃይማኖት ነክ የሆኑ መስሕቦች ላይ ይታደማሉ፤ ጉብኝት ያደርጋሉ። በዚህ ወቅት አስጎብኚ ባለሙያዎች አንድ ቱሪስት በአግባቡ መስተንግዶ አግኝቶ፣ የኢትዮጵያን እሴቶች ተዋውቆ ወደ አገሩ እንዲመለስ ሙያዊ ድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል። በተለይ ጎብኚው ቆይታው እንዲያራዝምና ሌሎች መስሕቦችንም እንዲመለከት ለማድረግ አስጎብኚው በሚገባ መሥራት ይጠበቅበታል።

አቶ ክብሮም ተስፋይ የኢትዮጵያ አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው። ኢትዮጵያ አዲስ ዓመት (2017 ዓ.ም.) ከመግባቱ ከነሐሴ ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ በዓላት እንደሚከበሩ ይናገራሉ። በተለይ በመስከረም ወር የማኅበረሰቡን ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቶች አጉልተው የሚያሳዩ ክብረ በዓላት የሚዘጋጁበት ወቅት መሆኑን ይገልፃሉ።

ከእነዚህ መስሕቦች ውስጥ በቱሪዝም ዘርፍ ያስተዋወቅናቸውና ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች እንዲታዩ ያደረገናቸው የተወሰኑትን ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከሻደይ አሸንዳ የልጅ አገረዶች በዓል ጀምሮ፣ በደቡብ ክልል የሚከበሩትን የአዲስ ዓመት መግቢያ በዓላትን (የጌዲዮ፣ የሀድያ፣ የየም እና ሌሎችንም) ጨምሮ በርካታ ሀብቶች መኖራቸውንም ይገልፃሉ።

መስሕቦቹን በሰፊው ማስተዋወቅ ቢቻል በኢኮኖሚውም ከፍተኛ ጥቅም የሚፈጥሩ እንደሆኑም ይናገራሉ። ሰፊና የየራሳቸው ዓውድ ያላቸው ክብረ በዓላት ከመሆናቸው አንፃር በአጭር ጊዜ ውስጥ በቀላል ወጪ ሁሉንም ማስተዋወቅ እንደማይቻል የሚናገሩት ባለሙያው፣ ይህን መሰል አቅም ለመፍጠር ከፍተኛ በጀት፣ ብቁና የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት እንደሚገባም ይገልፃሉ።

‹‹በመስከረም ወቅት ያሉትን ባሕላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶችን ወደ ቱሪዝም መስሕብነት ቀይሮ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የሚያስችል አቅም መፍጠር ያስፈልጋል›› የሚሉት አቶ ክብሮም፤ ኢትዮጵያ ያላት የመስሕቦች ብዛት መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ቢሆንም ቱሪዝም ዘርፉ ይህንን ወደ አቅም ለመቀየር የሚያስችል ትከሻ መፍጠር አለበት ይላሉ። በዚህ ረገድ የአስጎብኚ ባለሙያዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ በመሠረተ ልማት፣ በትራንስፖርት፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በሠለጠነ የሰው ኃይል፣ አሠራርን ከማዘመን አንፃር ከመንግሥት ተቋማት ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።

የቱሪስት አስጎብኚዎች ማኅበር ከነሐሴ ወር ጀምሮ በመስከረም ወር የሚከበሩ የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቁና ጎብኚዎች መዳረሻ እንዲያደርጓቸው እየሠራ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ክብሮም፤ የመጀመሪያው የባለሙያዎቹ ሥራ ሀብቶቹን የመለየትና በየትኛው የኢትዮጵያ ክፍል እንዲሁም በምን መልኩ እንደሚከበሩ መገንዘብ መሆኑን ይገልፃሉ። ከዚህ አኳያ በዚህም የማኅበሩ አባላትና አስጎብኚዎች እነዚህን እሴቶች ለይተው እንዲያውቁ ሥልጠናና በግንዛቤ ማስጨበጫ መሰጠቱን ይናገራሉ።

እሳቸው አንዳስታወቁት፤ አስጎብኚ ባለሙያዎች እንደ መስቀል፣ ኢሬቻ እንዲሁም ሌሎች ክብረ በዓሎች ላይ ከደኅንነት አንፃር ሊወሰድ ስለሚገባ ጥንቃቄ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህንን ግንዛቤ ለማስጨበጥም የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚዎች ማኅበር አባላት ሥልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል። የመስቀል በዓል በተከበረበት ወቅትም ከሥልጠናው የተገኙ ልምዶች በአስጎብኚ ባለሙያዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ተደርጓል። በዓላቶች ላይ ለመታደምና በኢትዮጵያ የሚገኙ መስሕቦችን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስረቶች ደኅንነት መጠበቅ የአስጎብኚውም ኃላፊነት እንደሆነ የማስገንዘብ ሥራ ተሠርቷል። በጉብኝት ሰበብ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ አደናጋሪዎችን ከትክክለኛ ጎብኚዎች መለየትና ጥንቃቄ መውሰድም እንዲሁም የአስጎብኚው ደርሻ አንደሆነ የማስረዳት ሥራዎች በተከታታይ በማኅበሩ በኩል ተከናውነዋል።

እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ በአዲሱ ዓመት መስከረም ወር በኢትዮጵያ በርካታ የቱሪዝም ሁነቶች ይካሄዳሉ። በመሆኑም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ጎብኚዎች በአንድ ቦታና ሁነት ላይ ብቻ እንዳያተኩሩ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እሴቶች እውቀትና ልምድን ይዘው እንዲመለሱ የማድረግ ኃላፊነት የአስጎብኚ ባለሙያዎች ነው። በመሆኑም ማኅበረሰቡ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የተለያዩ የማኅበረሰብ እሴቶችን ለጎብኚዎች ከማሳየት፣ በአንድ አካባቢ ላይ ብቻ የቱሪስት መጨናነቅ እንዳይኖር ከማድረግ አንፃር ልዩ ልዩ ስልቶች ተቀርፀው ተግባራዊ ተደርገዋል።

በመስከረም ወቅት በአደባባይ በዓላት ላይ ለመታደም ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ጎብኚዎች ስለ ክብረ በዓሎቹ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሲሄዱ በበጎ መልኩ እንዲያስተዋውቁ አስጎብኚዎች ድርሻቸውን እየተወጡ ነው። ስለ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ በዓሎቹ ምንነትና ትርጓሜም ትክክለኛው መረጃ እንዲኖራቸው በበዓሉ ወቅትም ሆኖ ከዚያ ቀደም ብሎ የማስገንዘብ ሥራ እየተሠራ ነው። ይህንን ኃላፊነት የማኅበሩ አባላት እንዲወስዱ ተደርጓል።

‹‹የአደባባይ በዓሎቹ የቱሪስቱን ቆይታ ሊያራዝም በሚችል አግባብ በትክክል ሊተዋወቁ ይገባል›› የሚሉት አቶ ክብሮም፤ በተጨማሪ ከፍተኛ ቱሪስት በሚገኝበት በዚህ ወቅት ከዚህ ቀደም ምንም ያልተዋወቁ አዳዲስ መስሕቦችን አጋጣሚውን ተጠቅሞ ለጎብኚዎቹ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ። ለምሳሌ ያህል የሸዋል ኢድ በዓል፣ የድሬ ሼክ ሁሴን፣ በደቡብ ኢትዮጵያ የሚከበሩ የአዲስ ዓመት በዓላትና ሌሎች የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ መስሕቦችን ማስተዋወቅ ይገባል። ይህንን ለማድረግ የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር አቅጣጫ በማስቀመጥ ተግባራዊ ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።

የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት አንደሚገልፁት፤ ቱሪስቶች በብዛት ከሚገኙባቸው ከተለመዱት የቱሪስት መዳረሻ መስሕቦች በተጨማሪ አዳዲስ ያልተዋወቁ ሀብቶች ላይ መሥራት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል በገና ወቅት ላሊበላ ልዩ ትኩረት አግኝቶ ቱሪስቶች ለጉብኝት ይሄዳሉ። ይሁን እንጂ የጊዮርጊስ በዓል በሚከበርበት ወቅት ለቱሪስቶች ልዩ ድምቀትና ልምድን የሚሰጥ ክብረ በዓል አለ። በትግራይ አክሱም ጽዮንም ከኅዳር ዓመታዊ ክብረ በዓል ባሻገር የዓብይ ፆም ሊፈታ ሲቃረብ በሆሳዕና በዓል የቱሪስቶችን ቀልብ ሊስብ የሚችል ክብረ በዓል አለ። ይህንን አይነቱን አዳዲስ ልምድ በማስተዋወቅ ጎብኚዎች ተጨማሪ አማራጭ እንዲያገኙና ኢትዮጵያን እንዲያውቁ ማድረግ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚዎች ማኅበርም አዳዲስ መስሕቦችና መዳረሻዎች የሚከበሩበትን ወቅት፣ ስፍራ እንዲሁም ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች የሚሰጥ ካላንደር ለማዘጋጀት እየሠራ ነው። ይህንን ካላንደር ከባለሙያዎች፣ ከባሕልና ሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም ከመንግሥት ባለድርሻ ጋር ማዘጋጀት ቢቻል በያዝነው መስከረም ወር ከሚከበሩት ደማቅ ክብረ በዓሎች ባሻገር አዲስ መዳረሻን በመፍጠር የቱሪስት ቁጥር ሽፋን ማሳደግ ይቻላል።

የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በዩኔስኮ እውቅና ያላቸውም ሆነ ገና በሂደት ላይ የሚገኙ መስሕቦችን ከማስጎብኘት ባሻገር ተጨማሪ የቱሪስቱን ቆይታና ተዝናኖት የሚጨምሩ ሁነቶችን ለመፍጠር እየሠራ መሆኑንም አቶ ክብሮም አስታውቀዋል፤ ከዚህ ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ያዘጋጀው አስጎብኚዎች በመስሕብ ስፍራዎቹ ሲንቀሳቀሱ በምስል (ፎቶ) ያስቀሯቸውን ማራኪ የጉብኝት ቦታዎች የሚያሳይ ዓውደ ርዕይ መሆኑን ይናገራሉ። ዘንድሮም የመስቀል፣ ኢሬቻና በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚያከብሯቸው በዓላትን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ሙዚየም ዓውደ ርዕይ መካሄዱን ይናገራሉ።

‹‹የፎቶ ዓውደ ርዕይው ሁለት ዓላማ ነው ያለው ነው›› የሚሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ የመጀመሪያው አጠቃላይ ማኅበረሰቡ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ስለሚገኙ የመስሕብ ሀብቶች (ስለሰሜኑ ደቡቡ፤ ምስራቁ ስለ ምዕራቡ) ግንዛቤ ኖሮት የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲያድግ ማድረግ መሆኑን ያነሳሉ። ሁለተኛው በኢትዮጵያ ኤምባሲ የከፈቱ ሀገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶችን በመጋበዝ በቀላል ወጪና በአጭር ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ሀብቶች ለየሀገሮቻቸው ዜጎች እንዲያስተዋውቁ ዕድል መክፈት መሆኑን ገልጸዋል።

የማኅበሩ የአስጎብኚ ባለሙያዎች አባላት እንደ ሌሎች የፎቶ ዓውደ ርዕይዎች የመስኅብ ሰፍራዎችን ብቻ በፎቶ በማስቀመጥ የሚያስተዋውቅበት መድረክ አይደለም ያሉት አቶ ክብሮም፤ ይልቁኑም አንድ ጎብኚ ወደ መዳረሻዎቹ ቢያቀና በቀላል ወጪ የሚያርፍበትን ሆቴል፣ ማግኘት ስለሚችለው ልዩ ልዩ አገልግሎት፣ ሊጎበኛቸው የሚችላቸው መዳረሻዎች ብዛት እንዲሁም ሌሎች ጠቃሚ ማስረጃዎችን ጭምር በዓውደ ርዕይው ማግኘት እንደሚቻል ያስረዳሉ። ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀው ዓውደ ርዕይም ይህንን ዓላማ ያሳካ እንደነበር ተናግረዋል።

‹‹መስከረም በኢትዮጵያ የቱሪዝም ወር እየሆነ ነው›› የሚሉት የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ በተለይ ለኢትዮጵያውያን የአዲስ ዓመት መጀመሪያ፣ የክረምት ወር መውጫ፣ በዩኔስኮ የተመዘገቡ የአደባባይ በዓላትና የዓለም የቱሪዝም ቀን የሚከበሩበት መሆኑን ይገልፃሉ። በዚህ ምክንያት የፎቶ ዓውደ ርዕይ በዚህ ወር ቢዘጋጅ ከውጪም ሆነ ከሀገር ውስጥ ሰፊ ቁጥር ያለው ጎብኚ ማግኘት እንደሚቻል በማመን በዚህ ወር መደረጉን ገልጸዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር ተባብሮ የኢትዮጵያን የመስሐብ ሀብቶች ለማስተዋወቅ፤ ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ መሥራት እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል። የአደባባይ በዓል የሆኑት መስቀል፣ ኢሬቻና ሌሎችም በዓላት አሁን ካሉበትም በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቁ ሰፊ ጥረት መደረግ ይኖርበታል ይላሉ።

ቱሪዝም ከዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ውስጥ አንዱ ተደርጎ ከመወሰዱ አንፃር ይህንን እድል ማስፋት የሚያስችል የቱሪዝም ሚኒስቴር መዋቅር ሊዘረጋ ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል። አሁን ያለው አደረጃጀት ኢትዮጵያ ካላት አቅም፣ ለዘርፉ ከተሰጠው ልዩ ትኩረት አንፃር ሲመዘን በቂ ነው ተብሎ እንደማይታመንም ያነሳሉ። በመሆኑም ጠንካራ የቱሪዝም ሚኒስቴር እና ሌሎች መንግሥታዊ አደረጃጀቶችን መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል ቱሪዝም ሠላም እንደሚፈልግ ተናግረው፤ ሠላም ለቱሪዝም ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን አፅንዕኖት ሰጥተው አመልክተዋል። ማኅበረሰቡ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ በዓላት በሚከበሩበትም ሆነ በየትኛውም ጊዜ የራሱን ሠላም እና ደኅንነት በማስጠበቅ የአገሪቱን መልካም ገፅታ ሊገነባና የቱሪስቶችን ደህንንት እንዲጠብቅም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You