የግብጽ ያልተገባ እንቅስቃሴ መላ አፍሪካውያንን የሚያስቆጣ ነው

አዲስ አበባ፡– ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር በጎረቤት ሀገራት እያደረገችው ያለው የስህተት እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ አልፎ መላ አፍሪካውያንን የሚያስቆጣ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ታዋቂው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ሙሳ ሸኮ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ግብጽ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህ በመጣስና ኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ጫና ለመፍጠር እንደ ሶማሊያ፣ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን ባሉ ሀገራት የምታደርገው ያልተገባ እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ አልፎ መላ አፍሪካውያንን የሚያስቆጣ ነው፡፡

ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ የውጭ ጫና ለመፍጠር የምትሞክረው በተለይም እንደ ሶማሊያ፣ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን ባሉ ሀገራት የምታደርገው አሉታዊ እንቅስቃሴ የአፍሪካ መፍትሔዎችን መርህ የሚጻረር ነው ያሉት አቶ ሙሳ፤ እነዚህ ድርጊቶች ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ብሎም መላውን የአፍሪካ አህጉር ሕዝብ የሚያስቆጣ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

አቶ ሙሳ፤ ግብፅ የኢትዮጵያን እድገት ለማዳከም የረዥም ጊዜ ታሪክ እንዳላት ጠቁመው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ከዓባይ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ የተሳሳተ አቋም እየወሰደች መሆኗን ገልጸዋል፡፡ ግብፅ የግድቡ ግንባታ ለአካባቢው የሚያስገኘው ጥቅም ወደ ጎን በመተውና ዓባይ የእኔ ብቻ በሚል የተሳሳተ እሳቤ የተለያዩ ጫናዎችን ማድረጓንም አንስተዋል፡፡

ይህንኑ ጫናዋን በማጠናከር በቅርቡ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት ለማግለል ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ጥምረት በመፍጠር፣ ከኤርትራ ጋር ግንኙነት በመፍጠር እና “የሰላም መልዕክተኞች” በሚል ወደ ደቡብ ሱዳን ወታደሮችን ለመላክ በማቀድ በኢትዮጵያ ዙሪያ እየተሽከረከረች ትገኛለች ነው ያሉት፡፡

እነዚህ እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደርና በቀጣናው ውስጥ ያለውን አንድነት ለማዳከም የምትሠራው ስትራቴጂ አካል እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

በሶማሊያ የምታደርገው እንቅስቃሴ ምንም እንኳን ጥቂት ደጋፊዎቿን ቢያስደስትም የፖለቲካ ልኂቃንን ጨምሮ አብዛኛው የሶማሊያ ሕዝብና ሌሎች አፍሪካውያን ድርጊቷን እየተቃወሙ እንዳለም አስታውቀዋል።

አካሄዷ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ መላ አፍሪካውያንን የሚያስቆጣ ነው በማለት፤ በርካቶችም እንቅስቃሴዋን ለቀጣናውም ሆነ ለሰፊው አፍሪካዊ አንድነት መሸርሸር መንስዔ ሊሆን እንደሚችል እየተቹ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ወቅታዊው የግብፅ ድርጊት የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ሰላምና እድገትን ለማደፍረስ የተደረጉ ታሪካዊ ሙከራዎቿ ቀጣይነት አመላካች ነው ብለዋል፡፡ ሆኖም ይህ የግብጽ ታሪካዊ የሆነ የዲፕሎማሲ ስህተትና ጠላትነትን ይፋ የማድረግ አካሄድ ራሷን ግብጽን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ግብፅ ኢትዮጵያንና የምሥራቅ አፍሪካን ቀጣና ለማተራመስ የምታደርገው ጥረት የረዥም ጊዜ የጣልቃ ገብነት አካል ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ፅናት እንደሚያሳየው ግን አሁንም እነዚህ ፈተናዎችን መወጣት እንደምትችል ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You