አዲስ አበባ፦ በኦሮሚያ ክልል ከ389 በላይ የቱሪስት መዳረሻ ዋሻዎች በጥናት እንደተለዩ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የቱሪዝም ልማትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ፋንታሁን ታደሰ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በኦሮሚያ ክልል በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡ ከክልሉ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ዋሻዎች በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው። በአሁኑ ጊዜም በክልሉ ከ389 በላይ የቱሪስት መዳረሻ ዋሻዎች በጥናት ተለይተዋል፡፡
የክልሉን እምቅ የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ በማስተዋወቅ እና በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ፋንታሁን፤ ለዚህም በክልሉ ከ389 በላይ የቱሪስት መዳረሻ ዋሻዎች በጥናት እንደተለዩ ገልጸዋል።
ለእነዚህ ካርታና ፕላን እንዲሁም ዋሻዎቹ እንዲጎበኙ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እየተሟሉ መሆኑን የተናገሩት አቶ ፋንታሁን፤ የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል። በተለይም በቱሪስት መዳረሻዎች አካባቢ የሚስተዋለውን የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር በመፍታት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
ከተለዩት ከ389 በላይ የቱሪስት መዳረሻ ዋሻዎች ውስጥ የናሲኦል ዋሻ አንዱ ነው። በአካባቢው እንደ መንገድ፣ ውሃ፣ መብራት፣ የቱሪስት ማረፊያና የእንግዳ መቀበያ መሠረተ-ልማቶች ለማሟላት እየተሠራ ነው። ዋሻውን በማልማትና በማስፋፋት የሀገራችን ብሎም የአህጉራችን ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ቢሮው ከምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ጋር በመተባበር ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህም በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ገልጸው፤ ዋሻውን ለመጎብኘት የሚመጡ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች እግረ-መንገዳቸውን ሌሎች የተፈጥሮ ዋሻዎችን፣ ደኖችን ጨምሮ አዕዋፋትና የዱር እንስሳትን እና መሰል የቱሪስት መስህቦችን ለመጎብኘት ልዩ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
ክልሉን በቱሪዝም ዘርፍ ተወዳዳሪ ማድረግ ለሥራ ፈጠራ፣ ለአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም ለሳይንሳዊና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የገለጹት አቶ ፋንታሁን፤ በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም ፀጋዎችን አልምቶ ውጤታማ የማድረግ ኃላፊነት የማህበረሰቡን ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም