“ኢትዮጵያ በቀይ ባህርና በሕንድ ውቅያኖስ ያለውን የማሪታይም ደህንነት በቅርብ እየተከታተለች ነው” – አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያ በቀይ ባህርና በሕንድ ውቅያኖስ ያለውን የማሪታይም ደህንነት በቅርብ እየተከታተለች መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ አስታወቁ። የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ወደ ታሪካዊው የትግበራ ምዕራፍ ሊሸጋገር መቃረቡን ጠቁመዋል::

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ 79ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በኒውዮርክ ከተማ ሲካሄድ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ በቀይ ባህርና በሕንድ ውቅያኖስ ያለው የማሪታይም ደህንነት ስጋት እጅጉን እንደሚያሳስባት ገልጸዋል።

ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እና የማሪታይም ንግድን የምትጠቀመው ኢትዮጵያ በውቅያኖሶቹ ያለውን የማሪታይም ደህንነት በቅርብ እየተከታተለች መሆኑን ገልጸው፤ግጭቶች፣ የባህር ላይ ውንብድናና ሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራት በአካባቢው ያለውን የማሪታይም ደህንነት አደጋ ላይ መጣሉን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የማሪታይም ደህንነት ጥበቃ ሥራዎች ሁሉን አሳታፊ እንዲሆኑ ትፈልጋለች ያሉት አምባሳደር ታዬ ፤የባህር በር የማሰስና የመጠቀም ፍላጎቷ ሊከበር እንደሚገባም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው ስምምነት ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ መልማትና መበልፀግን መሠረት ባደረገ መልኩ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር የመሥራት ልምድ እንዳላት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኛነትን በመዋጋት ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ እየሠራች እንደምትገኝ ገልጸው፤ በሶማሊያ የሽብርተኛ ቡድን የሆነውን አልሸባብን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ በማዳከም ረገድ ከሌሎች ሀገራት ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ጋር ውጤታማ ተግባር ማከናወኗን አንስተዋል።

በሶማሊያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት የተገኙ ድሎችን ስጋት ላይ የሚጥሉ ጉዳዮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋሉ መምጣታቸውንም አመልክተው፤ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሶማሊያ የተገኙ ድሎችን ወደ ኋላ በመመለስ የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችን ሊያስቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።

አምባሳደር ታዬ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም የከፈለችውን መስዋዕትነትና ዋጋ እውቅና ልትሰጥና ልታከብር እንደሚገባም ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በተገናኘ የሚቀርቡባትን ክሶችና ወቀሳዎች በፍጹም አትቀበልም፡፡ ሽብርተኝነትን ከመዋጋት የሚያግዳት ምንም ነገር እንደሌለም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ እንዲሁም ለውጤታማ የባለብዙ ወገን የትብብር መድረክ በቁርጠኝነት ትሠራለች ነው ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቋሚ ውክልና ማግኘት እንደሚገባት ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ ጥልቅ ማሻሻያ በማድረግ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ፍትሐዊ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ የሚመለከታቸው ሁሉ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ወደ ታሪካዊው የትግበራ ምዕራፍ ሊሸጋገር መቃረቡን ገልጸው፤ ይህም በተፋሰሱ ሀገራት ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር ያደርጋል ነው ያሉት።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩንና ይህም የኢትዮጵያንና የጎረቤት ሀገራትን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በመመለስ ቀጣናዊ ትብብርን ለማጎልበት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ40 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን ጠቁመው፤አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያን የደን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉንም ገልጸዋል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You