– ከማዕድን የወጪ ንግድ 800 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል
አዲስ አበባ፡- ሦስት የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካዎች በግንባታ ላይ መሆናቸውን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ። ከማዕድን የወጪ ንግድ 800 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱም ተገልጿል።
የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የከበሩ ማዕድናት እና ግንባታ ግብዓት የሚሆኑ በርካታ ማዕድናት ያላት ሀገር ናት።እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶች አልምቶ ለመጠቀም ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።
ከማዕድን ዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ ሦስት የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካዎች በግንባታ ላይ ናቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ፕሮጀክቶቹ በአንድ ዓመት ከግማሽ ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ወደ ማምረት እንደሚገቡ ይጠበቃል ብለዋል።
አቶ ሚሊዮን፤ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካዎቹ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ በዓመት ከ10 ቶን በላይ ተጨማሪ የወርቅ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ወደ ውጪ የሚላከውን የማዕድን ምርት በመጠንም ሆነ በጥራት እንዲጨምር እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ፕሮጀክቶቹ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ በጋምቤላና በትግራይ ክልሎች እንደሚገነቡ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በቤኒሻንጉል ክልል በኮርሙክ ወረዳ የሚገነባው ፕሮጀክት ትልቅና በዓመት እስከ ዘጠኝ ቶን ወርቅ የማምረት አቅም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ሚሊዮን፤ ከሦስቱ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ጉጂ የሚገኘው ነባር የወርቅ ማምረቻ ኩባንያ የማስፋፊያ ሥራ እየተሠራለት መሆኑን ገልጸው፤ ከወርቅ ባለፈም የፖታሽ ማዕድንን በአግባቡ ማምረት የሚያስችል ፕሮጀክቶች በአፋር ክልል እንደሚገነቡ ጠቁመዋል።
መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ያሉት አቶ ሚሊዮን፤ ዘርፉ ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ ማልማት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
በ2016 በጀት ዓመት ወደ ውጪ ከተላኩ ማዕድናት 420 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በያዝነው አዲሱ በጀት ዓመትም 800 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል።
የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብቶች ዘርፉን እንዲያለሙ በሀገሪቱ ምቹ የሆነ አሠራር ተዘርግቷል። በዋናነት ከዘርፉ የውጭ ምንዛሬን በማግኘት የካፒታል ምንጭ እንዲሆን እየተሠራ ነው ብለዋል።
በተጨማሪ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ማምረትና ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠር በዘርፉ የሚሠሩ ሥራዎች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም