ዜና ትንታኔ
ለኢኮኖሚ ስብራቱ ዋነኛ መንስኤ የባህር በር አለመኖሩ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ወደብ የሌላቸው ሀገራትም ብዙ ጊዜ የኢኮኖሚ እድገታቸው ውስን የሚሆነው አንዱ ምክንያት የባህር በር አለመኖራቸው እንደሆነ ይገለጻል። የዓለም ኃያላን ሀገራት በቀይ ባህርና በዙሪያዋ ቦታ ለማግኘት የሞት ሽረት ትግል ሲያደርጉም ይስተዋላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ፤ የባህር በር የአንድ ሀገር ጥቅል የምርት እድገትን ከ25 እስከ 30 በመቶ ከፍ እንደሚያደርገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናትን ጠቅሰው መናገራቸው ይታወሳል።
ከዚህ አኳያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የወጪና ገቢ ንግዷን በጂቡቲ በኩል የምታከናውነው ኢትዮጵያም የባህር በር በማጣቷ ምክንያት በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለወደብ ኪራይ ታወጣለች። ይሁን እንጂ የባህር በር አለመኖሩ በሎጂስቲክስ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩ የገሃዱ ዓለም እውነታ ነው።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ወቅታዊና የሎጂስቲክስ አቅምን ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ በብዙኃኑ ዘንድ ሲገለጽ ቆይቷል። የባህር በር አለመኖር በተለይ ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልካቸው ሆነ ወደ ሀገር የምታስገባቸውን ዕቃዎች ደህንነታቸውና ምስጢራዊነታቸው ተጠብቆ በፍጥነት ከመላክና ከማስገባት አንጻር ከፍተኛ ጫና የሚፈጥርም ነው።
በተጨማሪም እቃዎች በሚገቡና በሚወጡበት ወቅት በወደብ የሚኖራቸው ቆይታ ከፍተኛ ወጪ እንዳለው እና ይህም የዋጋ ንረት እንዲከሰት የሚያደርግ ነው። የባህር በር ያላቸው ሀገራት የባህር በር ከሌላቸው ሀገራት የበለጠ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሉዓላዊነታቸው የሚያረጋግጡባቸው ሰፋፊ እድሎች እንዳሏቸው የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ(ዶ/ር) ለኢፕድ በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ የባህር በር ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ የሆነ ዐቢይ ጉዳይ ነው ያላሉ። የባህር በር በበርካቶች ዘንድ ከውጭ ንግድ ጋር በተያያዘ የሚነሳ ቢሆንም በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ሰፋ ያለ ግምት የሚሰጠው ነውም ባይ ናቸው።
ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት ባለመሆኗ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ፣ ለወጪና ገቢ ንግድ መቀዛቀዝ እንዲሁም ለተለያዩ የደህንነት ስጋቶች ተጋልጣለች የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤በተጨማሪም በባህር አካባቢ የሚገኙ ጥቅሞች ማለትም የአሣ እና የተለያዩ የማዕድናት ምርት ማጣቷን ይናገራሉ።
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ የባህር በር ባለቤት አለመሆን ከኢኮኖሚው ጉዳት በተጨማሪ የሀገር ሉዓላዊነትና ደህንነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባበት ነው። በተለይ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ትልቁ የመርከብ ድርጅት ያላት ሀገር በመሆኗ እነዚህ መርከቦች በሰላም የእለት ተዕለት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸው ጠንካራ የባህር ኃይል ለመገንባት የባህር በር ያስፈልጋል።
በባህር በር አካባቢ ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ልማቶች፣ ኢኮኖሚክ ዞን እንዲገነቡ፣ የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲያድግ በማገዝ የሥራ እድል ፈጠራ፣ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም በሀገር የሚመረቱ ምርቶች እሴት ጨምሮ ለመላክ እድል እንደሚፈጥር ያብራራሉ። በባህር በር ችግር ምክንያት ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች 78 በመቶ በላይ የሚሆኑት በጥሬው የሚላኩት መሆናቸውን ያስረዳሉ።
የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ካላቸው ሀገራት በላይ በኢኮኖሚው የበለጠ ተጎጂ መሆናቸው እሙን ቢሆንም የተለያዩ ፖሊሲዎቻቸው በመሻሻላቸው ወደብ ሳይኖራቸው የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታቸውን ያረጋገጡ ሀገራት አሉ ያሉት ደግሞ የምጣኔ ሀብት ባለሙያና ፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ዋና ኃላፊ ክቡር ገና ናቸው።
በዓለም ከ40 በላይ የሚሆኑ ሀገራት ወደብ የላቸውም የሚሉት ክቡር ገና፤ ወደብ ሳይኖራቸው የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና እድገት በማምጣት ተጨባጭ ውጤት ያሳዩ ሀገራት እንዳሉ ይጠቁማሉ።
የተለያዩ እቃዎች፣ ሸቀጦች በመቀበልና በመላክ ሂደት ውስጥ ያለው የጉምሩክ፣ የታክስ፣ እንዲሁም በኬላዎች ላይ ያለው ቢሮክራሲ እንዲሁም የተጋነነ ቀረጥ ማቃለል ለነገ የማይባል ውሳኔ የሚፈልግ ነውም ባይ ናቸው።
እነዚህም በምርታማነትም ላይ ሆነ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የተወዳዳሪነት አቅም እንዳይጎለብት የሚያደርጉ መሆናቸውን ያመላክታሉ።
የባህር በር ሳይኖራቸው ኢኮኖሚ ልማታቸው ካሳደጉ ሀገራት ተሞክሮ መውሰድ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን፤ ሉክተንበርግ፣ካዛኪስታን፣ ሞንጎሊያ፣ ቦትስዋና የባህር በር ባይኖራቸውም ራሳቸውን አደራጅተው ባላቸው የተፈጥሮ ሀብት ወደብ ካላቸው ሀገራት እኩል መሆን ከቻሉ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
ይህ ማለት ግን የባህር በር መኖር የኢኮኖሚ ዕድገት አያመጣም ሳይሆን በባህር በር ብቻ ላይ ማተኮር ተገቢ አለመሆኑን ለመግለጽ መሆኑን ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ የባህር በር ሳይኖራት 10 በመቶ ያደገችበት ወቅት አለ የሚሉት ክቡር ገና፤ የባህር በር ፍላጎቱ እንዳለ ሆኖ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ስብራት ለመጠገን አሁን በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው ግጭት ማቆም፣ በየዘርፉ ውስንነት ያለባቸው ፖሊሲዎችና የአሠራር ክፍተቶችን በማስወገድ ወደ አንድ አቅጣጫ የሚወስድ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ መጠቀም፣ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ማሳደግ እንዲሁም ቱሪስትን በብዛት መሳብም ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ከባህር በር በተጨማሪ ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን ነው የጠቀሱት።
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም