“የለሚ የሲሚንቶ ፋብሪካ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን በፍጥነት እና በብቃት አጠናቅቆ ዝግጁ የማድረግ ተምሳሌትም ነው” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- የለሚ ብሔራዊ የሲሚንቶ ፋብሪካ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን በፍጥነት እና በብቃት አጠናቅቆ ዝግጁ የማድረግ ተምሳሌትም ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ትናንት ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤በቀን 150 ሺህ ኩንታል የማምረት አቅም ያለውን የለሚ ብሔራዊ የሲሚንቶ ፋብሪካ መርቀን ሥራ አስጀምረናል። ይህ ሜጋ ፕሮጀክት የመንግሥታችን በፍጥነት፣ በግዝፈት እና በንፅህና የመገንባት ጽኑ አቋማችን ማሳያ ነው። እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን በፍጥነት እና በብቃት አጠናቅቆ ዝግጁ የማድረግ ተምሳሌትም ነው።

በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገራችን ያሉ ተመሳሳይ ፋብሪካዎች ተደምረው የሚያመርቱትን ሃምሳ ከመቶ የሚያመርት የሲሚንቶ ፋብሪካ እውን እንዲሆን የተሳተፋችሁ በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ፤እንደ ለሚ ያሉትን የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች በሀገራችን ካባዛን በሥራ ፈጠራ ላይ የሚኖረው የመባዛት ፍሬ አቻ የማይገኝለት ነው ብለዋል።

ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደዚህ ስፍራ ስመለስ የአመራር መርሆዎቻችን ማሳያ በሆነው በሥራው ፍጥነት ተደንቄያለሁ። ፕሮጀክቱ በመሰል ጠንካራ ሥራ መጪው ትውልድ ድህነትን እንደማይወርስ ይልቁንም ለእድገት እና ብልጽግና ጥሩ መደላድል እንደሚጠብቀው እንደሚያሳይም ገልጸዋል።

እንደ ለሚ ያሉትን የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች በመላው ሀገራችን ካባዛን በሥራ ፈጠራ እና በሀገራዊ እድገት ላይ የሚኖረው የመባዛት ፍሬ አቻ የማይገኝለት እንደሚሆን አመልክተው፤ በተለይም በብረት ምርት፣ በማዳበሪያ ምርት ብሎም በሰፊው የኢንዱስትሪ እና ግብርና ልማት አብዮት የሚኖረው ተፅዕኖ ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ትልቅ ሀገራትን የሚገዳደሩ ፈተናዎች ከፍ ያለ ደረጃ ያላቸው መፍትሔዎችን እንደሚሹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አመልክተው፤ በመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ የሚኖር የጋራ ትብብር እምቅ ሀብትና እድሎችን ለመጠቀም ብሎም ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ቁልፍ ነው። በመሰል ሥራዎች ላይ ኢንቬስት በማድረግ የብዙ ዜጎችን ሕይወት ማሻሻል እንዲሁም ክብር ያለው አኗኗር እንዲኖሩ ማድረግ እንደሚቻል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የለሚ ብሔራዊ የሲሚንቶ ፋብሪካ በ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በጀት ተይዞለት የተገነባ መሆኑ ታውቋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You