ኢትዮጵያ በበረከቶቿ እንድትጠቀም ለሰላም ትልቅ ትኩረት እንስጥ!

አሁን ወቅቱ ቱሪዝማችን ነፍስ የሚዘራበት ወቅት ነው። ክረምቱ እየወጣ ሲመጣ የሚተካው ልምላሜ ምድሪቱን አረንጓዴ አልብሶና በአበቦች አስጊጦ ጎበዝ ሰአሊ በታላቅ ጥንቃቄ ከሳለው ስእል ያስበልጣታል። በሚገባ አልተጠቀምንበትም እንጂ ፈጣሪ ከማንም ሳያሳንስ ከብዙዎቹም አስበልጦ ይቺን ሀገር ሰጥቶናል። ተፈጥሮዋ፣ ታሪኳ፣ ባህሏ፣ ህዝቧ ከማንም በላይ የመጎብኘት እምቅ አቅም አለው። አሸንዳ፣ ሶለል፣ ሻደይ፣ ጎቤ፣ ሺኖዬ፣ ጳጉሜን፣ አዲስ ዓመት፣ መስቀል፣ ኢሬቻና ሌሎችም የነሐሴና የመስከረም በረከቶች ናቸው።

ቱሪዝም የገቢ ምንጭ ብቻ አይደለም። መልካም ገፅታ መገንቢያ፣ ማህበረሰብ ማነቃቂያ፣ እርስ በርስ መተዋወቂያ፣ የዓለም አንድ አካል መሆኛም ጭምር ነው። እርግጥ ነው የባህል መደበላለቅ፣ የባህል መበረዝና ሌሎችም ይፈሩ እንጂ የራስን አጥብቆ ይዞ መጎብኘት ከእነ ሕንድና ከእነ ቻይና ልንማር እንችላለን። ወደ ቱርክና ቻይና ሄዶ የሚመለስ ሰው ጠንካራ፣ ደረጃውን የጠበቀ፣ ራስን ያከበረ መስተንግዶ ስለሚጠብቀው ቱርካዊና ቻይናዊ ይሆናል እንጂ ባህልን በክሎ አይመለስም።

ቱሪዝም የብዙ ሀገራትን ቀዳዳ ደፍኗል። በተለይም እንደ እኛ ላሉ የግብርና ምርት ፈልገው ትልልቅ ማሽኖችን፣ መድኃኒቶችንና ነዳጅን የሚያስገቡ ሀገራት መቼም ቢሆን የንግድ ልውውጣቸው ተመጣጥኖላቸው አያውቅም። የግብርና ምርቶችም ገቢያቸው በራሳቸው የመወሰን ደረጃ ላይ ባለመድረሳቸው ገዢያቸው የሰጣቸውን ዋጋ ተቀብለው ነው የሚሄዱት። ይሄ የገቢና የወጪ ንግድ አለመመጣጠን ከሚስተካከልባቸው መንገዶች መካከል ዋናው ቱሪዝም ነው።

ቱሪዝም ተፈጥሮ የሰጠችንን ሀብት፣ እውቀትና ውበት ጨምረንበት የሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ እንዲሆን መስራትን የሚጠይቅ ዘርፍ ነው። የቡና ቱሪዝም ብቻ እንኳ ብንጀምር ቡና ሸጠን ከምናገኘው ገቢ ቡናን ለመጎብኘት ከሚመጡት እጥፍ ማግኘት እንችላለን። የቡና መገኛ መሆናችን ብቻ በየዓመቱ ሚሊዮኖችን መሳብ በቻለ ነበር። ለዚህም ዋናው ስራ ማስተዋወቅ ላይ መጠንከር ያስፈልጋል። ከተለመዱት ጎብኚዎች ባሻገር ሌሎች አፍሪካዊያን፣ አረቦች፣ ሕንዶች፣ ቻይናዎች፣ ሩሲያኖች እንዲመጡ ብናደርግ ቱሪዝሙን እናስፋፋዋለን።

መጥራት ብቻ ሳይሆን ስም ብቻ ሆኖ የቀረብን ኢትዮጵያዊ መስተንግዶን አስተካክለን ማረፊያና የሚታዩ ነገሮችን ሰርተን ብንጠብቃቸው ኢትዮጵያን አለመውደድ፣ አለመጎብኘት አይቻልም። በዚህ ረገድ ጠቀሜታቸው የገዘፈ የገበታ ለሀገር፣ የገበታ ለሸገርና ሌሎች ፕሮጀክቶች ግንባታ ለውጥ እያመጣ ነው። መንግስት ከለውጡ በኋላ በሰፊው ለቱሪዝም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው። በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የቱሪስት መዳረሻዎች ቱሪስቶችን በመሳብ የሀገሪቱን ገቢ ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው።

በእርግጥ አሁንም የሀገራችን ቱሪዝም ሊለማ በሚችልበት ልክ ያልለማና በዘርፉ ዜጎች ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዳልሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል። የኢትዮጵያ ቱሪዝም እንደዘርፍ ትኩረት ስቦ በተቋም መመራት ከጀመረ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም አሁንም ገና ያልተነካና በእምቅነት ደረጃ ያለ ነው። አሁን ላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሁሉም ዘርፍ ማሻሻያ ለማድረግ እቅድ ሲዘጋጅም ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው መስኮች መካከል አንዱ ቱሪዝም ነው።

ኢትዮጵያ ካላት እምቅ የቱሪዝም አቅምና መዳረሻዎች አንፃር እያገኘች ያለችው ጥቅም አነስተኛ መሆኑ የሚነሳበት ዘርፉን ለማዘመን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ሰፊ ዝግጅት እና ካፒታል የሚጠይቅ ነው። ኢትዮጵያ በቂ ሊባል የሚችል ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርስ አላት። እንደ ገበታ ለሀገር ያሉ ፕሮጀክቶች ደግሞ ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ በመሆን የቱሪስትን ፍሰት ይጨምራሉ። የፕሮጀክቶች መተግበር ሀገሪቱ በሀብት ላይ ሀብት ማካበት እንድትችል እድል ይሰጣታል።

እ.ኤ.አ በ2019 ከአጠቃላይ የዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ 10 በመቶ ድርሻ ያለው እንደሆነ የሚነገርለት ቱሪዝም ለ334 ሚሊዮን ሰዎችም ስራ መፍጠር ያስቻለ ነው። ኢትዮጵያም ነባራዊ ሁኔታን ለመቀየር እና ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ ተገቢውን ድርሻ እንዲይዝ እስቻይ ስራዎችን እያከናወነች ነው።

ኢትዮጵያ ተፈጥሮን፣ ታሪክንና ምጡቅ የአእምሮ ውጤቶችን በመጠቀም የቱሪስት መዳረሻዎችን እየገነባች ነው። ከነበሯት መዳረሻዎች በተጨማሪ አዳዲስ መዳረሻዎችን መገንባቷ ብዝሀነት ያለው የቱሪዝም ሀብት እንዲኖራት ያደርጋል። የመስህብ ቦታዎቹ /ወንጪ፣ ጎርጎራ፣ ኮይሻ፣ ጨበራ ጩርጩራ…/ የሀገርን ገፅታ ከመገንባት በተጨማሪም የቱሪዝም ዘርፉ ለዜጎች የስራ እድል ፈጠራና የውጭ ምንዛሬ ምንጭም እንዲሆን ያስችለዋል።

መሰል የቱሪዝም መዳረሻዎች በሰፉ ቁጥር እነሱን ተከትሎ ደግሞ የቱሪዝም ኢንቨስትመንቱ እያደገ ይመጣል። አንድ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻ ሲፈጠር ሌሎች ባለሀብቶች የስራ እድል ይፈጥርላቸዋል ወይም አዳዲስ የቢዝነስ ድርጅቶች ይፈጠራሉ። የቱሪዝም መዳረሻዎች አካባቢ የሚገኙ ዜጎች ጭምር ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን ከቱሪዝሙ በተገኘው ገቢ ደግሞ የመሰረተ ልማት አገልግሎትን ያገኛሉ። የተገነቡትም ሆኑ እየተገነቡ ያሉት የቱሪዝም መዳረሻዎች ቱሪስቶችን ወደ ሀገር ከመሳብ በተጨማሪ በሀገራችን የሚቆዩበትን ጊዜ ማራዘምና የማይረሳ ትዝታ ውስጥ አስገብቶ ደጋግመው እንዲመጡ በማድረግ ዋነኛው የገቢ ምንጭ ናቸው።

ይህንን በአግባቡ የተረዱት በቱሪዝም ፍሰታቸው የሚታወቁ ሀገራት ከዋናው ከሚጎበኘው መስህባቸው በተጨማሪ የተለያዩ የመዝናኛና የመገበያያ ስፍራዎችን ያዘጋጃሉ። ተራራ መውጣት፣ ጫካ ውስጥ ማደር፣ የተገደበ አደን፣ የሙዚቃ፣ የምግብና መጠጥ ፌስቲቫሎች እና መሰል ድርጊቶች ብዙ ቦታዎች ላይ ይዘወተራሉ።

በተቃራኒው ኢትዮጵያ እጅግ ብዙ የቱሪስት መስህቦች ቢኖሯትም የሚጎበኙላት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። እነሱም ቢሆን በቂ የሚባል መጓጓዣ እንኳ የሌላቸው ናቸው። የሚመጡትም ቱሪስቶች ያዩትን ካዩ በኋላ ወዲያውኑ ስለሚወጡ የያዙትን እውቀት፣ ገንዘብ፣ ልምድና ሀሳብ እንደያዙ ይወጣሉ። በዚህም ብዙ ነገር ስናጣ ቆይተናል።

የገበታ ለሀገር፣ የገበታ ለሸገር፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የኮሪደር ልማትና መሰል ፕሮጀክቶች መተግበር ከጀመሩ በኋላ የቱሪስቶች ቆይታ እየተራዘመ መጥቷል። በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሚደረጉ ጉብኝቶች ማረፊያ የሆነ ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። የተለመዱ ሆቴሎችና መስተንግዷቸው ያው የተደጋገመ ስለሚሆን የሚስብ ነገር ማግኘት አይቻልም ነበር።

ታዲያ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ታሪክን ከተፈጥሮ ጋር አጣምረው በመያዝ ሁነኛ መፍትሄ ሆነው አምረውና ደምቀው ብቅ ብለዋል። የተፈጥሮ ስጦታቸው ላይ ውበት የዘሩባቸው እጆች ስዕል እንጂ በእውኑ ዓለም የሌሉ እስኪመስሉ ድረስ አሳምረዋቸዋል። በውሀ ዳር ውበት ከተለየን ከሰላሳ ዓመታት በኋላ ባህርን፣ ውበትንና ታሪክን አጣምረው የሪዞርቶች ቁንጮዎች ሆነው በየአካባቢያቸው ተገማሽረዋል። ‹‹ኑ እዩን፣ ኑ ተፈጥሮና ጥበብ ሲጣመሩ የሚፈጥሩትን እፁብ ድንቅ ትዕይንት ተመልከቱ…›› እያሉ ነው።

ከዚህ በኋላ የትኛውም ቱሪስት እንደመጣ አይወጣም። የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ማግኔቶች ናቸው፤ ይስቡታልም፣ ያጣብቁታልም። በኮይሻ፣ በደንዲ ወንጪና በሌሎችም ያየነው የመዳረሻ ልማት እምቅ የውበት መጠናችንን ብቻ ሳይሆን የመወሰን እና የመቻል ብቃታችንን የሚያስመሰክር ነው። እነ ሀይቅ፣ አሸንጌ፣ አባያ፣ ጫሞ እና ሌሎችም ይቀጥላሉ።

አሁናዊው ቱሪዝም ታሪካዊ ወይም ባህላዊ አሊያም ሀይማኖታዊ ቅርሶች ብቻ የሚታዩበት አይደለም፤ እንዲያውም ዘመናዊው መዝናኛ የበዛበት እየሆነ ነው። ጥንታዊ ታሪኮች ከጥቂት ድግግሞሽ እና አድናቆት በኋላ ለራሱ ለታሪክ ተትተው፤ ተለዋዋጭና አዳጊው ዘመናዊው ቱሪዝም እየተፈለገ ይገኛል።

እነ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ አሜሪካ እና መሰል ሀገራት ሁልጊዜ የቱሪስቶችን ቀልብ የሚይዙት ከሕዝባቸው ቁጥርም በላይ አስተናግደው ቢሊዮን ዶላሮችን የሚዝቁት ጥንታዊ ወይም ታሪካዊ ብቻ ስለሆኑ አይደለም። ምናልባት ስፔንና ፈረንሳይ ከጥንቱ የሚወስዱት ቢኖራቸውም አሜሪካ ግን ዘመናዊ ነች። የእነ ፈረንሳይም ጥንታዊነት ከነቻይና፣ ግብፅ፣ ሕንድ፣ ኢትዮጵያ ጋር የሚወዳደር አይደለም። ነገር ግን ፈረንሳይ አሁንም በቱሪዝም መስክ መሪ ነች።

እንደ ዘመናዊ ቱሪዝም ምንጭ ከሚታዩት መካከል አንዱ የሆነው የኮንፍረንስ ቱሪዝም ጥሩ ጥሩ ሆቴሎችን፣ መጓጓዣዎችን፣ መሰብሰቢያዎችንና መዝናኛዎችን መገንባት ብቻ የሚፈልግ ነው። ለዚህ ነው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ቱሪስቶችን በመሳብ ግንባር ቀደም እየሆነች ያለችው። ሳውዲም ትሪሊዮን ዶላር እያወጣች ያለችው ራሷን እንደ አዲስ ለመገንባት ነው።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያም ጥሩ ጅምር ላይ ያለች ሀገር ነች። ከታሪካችን፣ ከልምዳችን፣ ከአፍሪካ ኅብረት መቀመጫነታችን የተነሳ ብዙ ኮንፍረንሶችን ብናስተናግድም የከተማችን ውበት፣ ሆቴል፣ መዝናኛና መሰብሰቢያ ምቹ ነበሩ ብለን መናገር አንችልም። ለዚህም ይመስላል አንዳንዶቹን እነ ኪጋሊ፣ ናይሮቢና ሌሎቹም ሲነጥቁን የነበሩት። አሁን አሁን እየሰራናቸው ያሉ ስራዎች በተጨባጭ የከተማዋን ውበት እና ፅዳት ከመጠበቅ አንፃር ትልቅ ለውጥን እያመጡ ነው።

ባለፈው ሳምንት ያስተናገድነው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም እንኳ የተካሄደው በአድዋ መታሰቢያ አዳራሽ ውስጥ መሆኑ ለእኛ ትልቅ ለውጥ ነው። ተሰብሳቢዎቹ ወጣ ሲሉ ወደ እንጦጦ አሊያም ወዳጅነት ፓርክ መሄድ ችለዋል። ነገ ከነገወዲያ ደግሞ እነ ወንጪ፣ ጎርጎራና ሌሎቹም እንደዚሁ አይነት ኮንፍረንሶችን ያስተናግዳሉ ማለት ነው። የቱሪዝሙ ገቢ በዚያው መጠን ይጨምራል፤ የሀገሪቱም ገፅታ ይ ስተካከላል።

የሀገራችን ትልቁ ችግር የሆነው የቤት ግንባታ ሲሟላ፣ የትራንስፖርት እጦቱ ሲቀረፍ፣ ድህነትና መፈናቀል ወደ ልመና የገፋው ኑሮ ተስተካክሎለት መመለስ ሲቻል፣ መልካም አስተዳደር ችግሮች ሲስተካከሉ ሀገራችን ለውስጥም ለውጪም የምትመች ተመራጭ በታደለችው ውብ ተፈጥሮ ላይ በዘመናዊነት የተሸለመች ገነት ትሆናለች።

ይሄ ግን የሁላችንንም ጥረትና ስራ የሚፈልግ ነውና በጋራ እንበርታ! ከሁሉም በላይ እምቅ የቱሪዝም አቅም እያላት ከዚህ ዘርፍ የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ የቆየችው ኢትዮጵያ አሁን በተገነቡት ገበታ ለሀገር በረከቶች ተጠቃሚ እንድትሆን ለሰላም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You