በበጀት ዓመቱ ከባህር ትራንስፖርት አገልግሎት 104 ነጥብ 14 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዷል

አዲስ አበባ፦ በተያዘው በጀት ዓመት ከስምንት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቶን በላይ እቃ በማጓጓዝ 104 ነጥብ 14 ቢሊዮን ብር ለማግኘት መታቀዱን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮምኒዩኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምሰው በንቲ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ በበጀት ዓመቱ ከባህር ትራንስፖርት አገልግሎት 104 ነጥብ 14 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዷል።

በተያዘው በጀት ዓመት ስምንት ሚሊዮን 250 ሺህ ቶን የወጪና ገቢ ንግድ በማጓጓዝ 104 ነጥብ 14 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዷል ያሉት አቶ ደምሰው፣ በዚህም 14 ነጥብ 30 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ለማስመዝገብ ውጥን መያዙን ጠቁመዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ከባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት 51 ነጥብ 01 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ 57 ነጥብ 14 ቢሊዮን ብር በማግኘት ስምንት ነጥብ 86 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ መገኘቱንም ነው አቶ ደምሰው የገለጹት።

ዘንድሮ የታቀደው የጭነት የማጓጓዝ እቅድ በ2016 በጀት ዓመት የሀገሪቱን ወጪ ገቢ ንግድ ከማጓጓዝ አኳያ ከነበረበት ሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን ላይ አስር በመቶ ጨማሪ ያለው እንደሆነ ተናግረዋል።

አቶ ደምሰው አክለውም፣ አገልግሎቱ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል የተሳለጠ የሕዝብና የጭነት ትራንስፖርት እንዲሁም የወደብና ተርሚናል አገልግሎት መስጠት ነው ያሉ ሲሆን ከ94 በመቶ በላይ የሀገሪቱ የገቢና ወጪ ንግድ በአገልግሎቱ በኩል እየተሳለጠ ይገኛልም ብለዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት በቀይ ባህር አካባቢ ካጋጠሙ የደህንነት ችግሮች ጋር በተያያዘ በአገልግሎቱ ላይ ጫና አሳድሮ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ደምሰው፤ በቅንጅት በመሠራቱ ችግሩን ለመፍታት እንደተቻለ አብራርተዋል።

እንደ አቶ ደምሰው ገለጻ፣ በቀይ ባህር ላይ በተፈጠረው ችግር በተለይ ከቻይናና ከሩቅ ምስራቅ ሀገራት የተለያዩ ሸቀጦች ለማጓጓዝ በኪራይ የሚሠሩ መርከቦች ወደ ጅቡቲ ወደብ አንሄድም በማለታቸው ችግሩን ለመቅረፍ ሳውዲ አረቢያና ኦማን አካባቢ ያሉ ሁለት ወደቦች ድረስ አድርሰው በሀገር ውስጥ መርከቦች እንዲጓጓዝ ተደርጓል። ይህ ርምጃ ባይወሰድ በሀገሪቱ በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያሳድር ነበር።

አቶ ደምሰው ሀገሪቷ ካላት መርከበቦች በተጨማሪ መርከቦች በመከራየት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው በ2017 በጀት ዓመትም የስድስት አዳዲስ የመርከቦች ግዢ ለመፈጸም ቅድመ ሥራዎች መጀመራቸውን አስረድተዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ከጅቡቲ ወደብ በተጨማሪ የላሙ ወደብም መጠቀም ተችሏል ያሉ ሲሆን ሀገሪቷ ካላት ከፍተኛ የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ብዛት በርካታ ወደቦች ለመጠቀም መንግሥት እየሄደበት ካለው ጎን ለጎን የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ መርከቦች ከ346 በላይ በሚሆኑ ዓለም አቀፍ የወደብ መዳረሻዎች አገልግሎት በመስጠት ለሀገር ከሚያስገኙት ጠቀሜታ ባሻገር የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ ለሀገር አምባሳደር በመሆናቸው የተቋሙን አቅም ለማሳደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊተባበሩ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You