ተቀናጅቶ መስራትን የሚጠይቀው የከበሩ ማዕድናት ልማት

ኢትዮጵያ ከሚገኙ ማእድናት መካከል የከበሩ ማዕድናት ይጠቀሳሉ። ማእድናቱ የከበሩ ለመባላቸው አንዱ ምክንያት የሚገኙበት ሁኔታ ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ማዕድናቱ በበቂ ሁኔታ እንደልብ የማይገኙ መሆናቸው የከበሩ ሊያሰኛቸው እንደቻለም ይናገራሉ።

ከእነዚህ ማእድናት መካከል ሳፋየር፣ ሩቢ፣ ኤምራልድ፣ ኦፓል፣ ጃስበር፣ ኦብሲዲያን፣ ጋርኔት፣ አሜቲስት እና ሲትሪን የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ማዕድናት በአብዛኛው ለመዋቢያ ጌጣጌጥነት የሚውሉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን የጌጣጌጥ ክፍል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘካሪያስ ፍቃድ ስለከበሩ ማዕድናት ሲገልጹ፤ ከሌሎች ማዕድናት አንጻር ሲታዩ የከበሩ የተሰኙበት ዋንኛ ምክንያት አገኛኘታቸው እንደሆነ ያስረዳሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ የከበሩት ማዕድናት እንደልብ በበቂ ሁኔታ አይገኙም። ይህም የከበሩ ተብለው እንዲለዩ አድርጓቸዋል። የከበሩ ማዕድናት ሁለት አይነት ናቸው፤ የከበሩ (precisions) እና በከፊል የከበሩ (semi precisions) ይባላሉ። በከፊል የከበሩ ማዕድናት ከሌሎች የከበሩ ማዕድናት አንጻር ሲታዩ በተሻለ መልኩ በብዛት ሊገኙ ይችላሉ። የከበሩ የሚባሉት ማእድናት ግን የመገኘት እድላቸው እጅግ አነስተኛ ነው።

በከፊል የከበሩ (semi precisions) ከሚባሉ ማዕድናት መካከል ጃስበር፣ ጥቁር ባልጭ /ኦብሲዲያን/፣ ጋርኔት፣ አሜቲስት፣ ሲትሪን ይገኙበታል። የከበሩ የሚባሉት ደግሞ በአንጻራዊነት የመገኘት እድላቸው እጅግ አነስተኛ የሆነው እንደ ሳፋየር፣ ኤምራልድ፣ ኦፓል አይነቶቹ ናቸው።

ኢትዮጵያ የተለያዩ አይነቶች የከበሩ ማዕድናት እንዳሏት ጠቅሰው፣ እነዚህም ማዕድናት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እንደሚገኙ አቶ ዘካርያስ ይናገራሉ። እስካሁን ባለው ግኝት በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በተለይ በኦሮሚያ ክልል፣ በአማራ ክልል እና በደቡብ ክልል እንዲሁም በሰሜን የአገሪቷ ክልል ላይ ይገኛሉ። ለአብነትም በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙት የከበሩ ማዕድናት ውስጥ አንዱ ኤምራልድ ነው። በክልሉ የሚገኘው ኤምራልድ ሌሎች ቦታ ላይ ከሚገኙ የተሻለ ጥራት አለው። ሩቢ እና ሳፋየር የሚባሉት የከበሩ ማዕድናት ደግሞ በሰሜን የአገሪቷ ክፍል በተለይ በትግራይ ክልል በስፋት ይገኛሉ። ኦፓል የተሰኘው ማዕድንም እንዲሁ በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ አካባቢ በስፋት እንደሚገኙ ይገልጻሉ።

አቶ ዘካርያስ እንዳብራሩት፤ እነዚህ ማዕድናት ከምንለይበት ዋና መንገድ አንዱ በአገኛኘታቸው ነው። ተገኝተውም ደግሞ የጥራት ደረጃቸው በራሱ የተለያዩ መሆኑ ሌላኛው ነው። ለአብነት ኦፓል የተሰኘውን ማዕድን ብንመለከት የሰሜን ሸዋ እና የደላንታ ኦፓል በመባል ይታወቃል። እነዚህ በሁለቱ የኦፓል አይነቶች መካከል ሰፊ ልዩነት ያለ ሲሆን፤ በተለይ የደላንታው ኦፓል በአውስትራሊያ ከሚገኘው ኦፓል እኩል ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው። አሁን ላይ እየወጡ ያሉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ደግሞ የጥራት ደረጃቸው ከአውስትራሊያው ኦፓልም የበለጠ መሆኑን ነው። በዚህ የተነሳ የደላንታው ኦፓል ዋጋ ከሌሎች አንጻር ከፍ ያለ ነው፡፡

ሌሎች አካባቢዎች የተወሰኑ የኦፓል አይነቶች አሉ። ለአብነትም ፋየር ኦፓል የተሰኘው በአፋር አካባቢ ይገኛል። ኦፓል በተለያዩ ቦታዎች የሚገኝ ሲሆን እንደ የኦፓሉ አይነት ደረጃውና የጥራቱም ይለያያል። እነ ሳፋየር፣ ሩቢ አይነት ማዕድናት ደግሞ ከኦፓል እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው መሆኑን አቶ ዘካርያስ አስገንዘበዋል።

አገሪቱ እነዚህ መሰል የከበሩ ማዕድናት ቢኖራትም ግን ማዕድናቱ አሁንም ድረስ እየተመረቱ ያለበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ የሚጠቆሙት አቶ ዘካርያስ፤ በባህላዊ መንገድ ስለሚመረትና ቴክኖሎጂን የመጠቀም እድሉ ውስን መሆኑንም ለዚህ እንደዳረጋቸው ያስረዳሉ። እስካሁን ድረስ ማዕድናቱን የሚመረቱ እንደዶማ፣ ዲጅኖ ያሉ የተለያዩ ባህላዊ መሳሪያዎች በመጠቀም እንደሆነ ይገልጻሉ። ባህላዊ የአመራረት ሂደት ተጠቅመን ሲመርቱ ደግሞ ማዕድኑ ሊመታ ስለሚችል የመሰባባርና የመሰነጣጠቅ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ይህ ሲሆን ደግሞ ማዕድኑ ያለው የጥራት ደረጃ እንዲወርድ ስለሚያደርገው በገበያ ላይ ያለው ተቀባይነት ዝቅተኛ እንዲሆን ያደርገዋል ሲሉ አስረድተዋል።

ማዕድናቱ ከማምረቱ በኋላ በጥሬው ለገበያ ከማቅረብ ይልቅ እሴት ማከል ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አጽኖት ሰጥተው ይናገራሉ። ቀደም ባሉት ጊዜያት አንድ ችግር የነበረው ማዕድኑ ምንም አይነት እሴት ሳይታከልበት በጥሬው መውጣት እንደነበር አንስተዋል። በሕገወጥ መንገድ ድንበር አልፈው የሚሄዱበት ሁኔታዎች መኖሩን ጠቅሰው፤ ማዕድኑ በጥሬ መላኩ እንዳለ ሆኖ በተጨማሪ ደግሞ በሕገወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጣ መደረጉ እንደሀገር ኪሳራ ሲያስከትል የቆየ መሆኑን ይገልጻሉ። አሁን ላይ መንግሥት አሰራር ሥርዓቱን በደንብ ስላስተካከለ ቁጥጥሩ በደንብ እየተጠናከረ መምጣቱ ይገልጻሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ የከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት ማከል ሲባል ለመዋቢያ ጌጥነት በሚውሉ መልኩ ማዘጋጀት ነው። በተለይ ለሰው ልጅ ውበት የሚውሉ ጌጣጌጦችን ለመስሪያነት ይወላሉ። የአንገት ጌጥ፣ የጆሮ ጌጥ፣ የእጅ አምባር፣ እና የጣት ቀለበት እና የመሳሰሉት አገልግሎት ላይ ውለው ውበትን ይሰጣሉ። ማዕድናቱ በዚህ መልኩ እሴት ታክሎባቸው አገልግሎት ላይ ከዋሉ የሚቀሩ ሌሎች ተረፈ ምርቶች ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚያ ተረፈ ምርቶች ውድ ስለሆኑ በአግባቡ በመጠቀም ለሌሎች ነገሮች ማስዋቢያነት ጥቅም ላይ ይውላሉ። ለምሳሌ ለተለያዩ ለዲኮር ሥራዎች፣ ለፈርኒቸር ውበት፣ ለሌዘር ፋብሪካዎች እና መስል አገልግሎቶች ሊውሉ ይችላሉ። የከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት በማከል መስራቱ እንደሀገር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይሰጣል ፡፡

ማዕድናቶቹ ከመመረት ጀምሮ ጥራታቸው የጠበቁ እንዲሆኑ የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። በተጨማሪም ከእነዚህ ማዕድናት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሕገወጥነት ሕጋዊ መንገድ እንዲከተል ለማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራትን ይጠይቃል የሚሉት አቶ ዘካሪያስ፤ ለአብነትም የአውስትራሊያን ተሞክሮ ያነሳሉ። አውስትራሊያዊያን በከበሩ ማዕድናት ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደአገር ትልቅ አጀንዳ አድርገው ብዙ ሥራዎች መስራታቸው ይናገራሉ፡፡

በተለይ ራሳቸው የሚያመርቱትን ኦፓልን የተሻለ ጥራት እንዳለው አድርገው በማስተዋወቅ በማቅረብ ብራንዱ ከፍ ብሎ እንዲታይ አድርገዋል። ሃቁን ስንመለከት ግን የኢትዮጵያ ኦፓል ከአውስትራሊያን የተሻለ ሆኖ ሳለ ማዕድናት የማስተዋወቅ ላይ ውስንነት ስላለ የተሻለ መሆንን ማሳየት አልቻልንም። ለዚህም በማዕድናቱ ዙሪያ ያለ የግንዛቤ ውስንና ፕላትፎርሙ አለመኖር በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።

በአገሪቷ ያሉ ማዕድናት ለዓለም የማስተዋወቅ ሥራ እምብዛም ያልተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንደሀገር ያሉት እንደ ኦፓል ያሉ የከበሩ ማዕድናት እሴት በማከል ለዓለም ማስተዋወቅ የሚመለከታቸው ሁሉ ሊሰሩበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እንደሀገር 40 በላይ የተለያዩ የከበሩ ማዕድናት ያሉ ቢሆንም ግን ምን ያህሉ ላይ በደንብ ተሰርቷል የሚለው በደንብ መታየት አለበት የሚሉት አቶ ዘካርያስ፤ አሁን ላይ ዋንኛ እሴት ከማከሉ ላይ መስራት ጎን ለጎን ማምረቱ ላይ ትኩረት በመስጠት የሚያመርቱ አምራቶች አቅም ማሳደግና ባለሙያው ማፍራት ላይ ሊሰራ ይገባል ይላሉ።

እንደ አቶ ዘካርያስ ገለጻ፤ እንደሀገር የከበሩ ማዕድናት ብዙ ትኩረት የተሰጣቸው ስላልሆነ እሴት ለማከል እንኳን ብዙም የሚባል የተማረ ሰው አልነበረበትም። እስካሁንም ድረስ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ደረጃ እንኳን ሙያዊ ስልጠናም ቢሆን እየተሰጠ ያለው አማራ ክልል ብቻ ነው። የእሴት ማከል (ላፒደሪ) ሥራ የከበሩ ማዕድናት የመቁረጥ፣ የማለስለስ እና የማስዋብ ሥራን የተለያዩ ድርጅቶች በግል በተወሰነ መልኩ እንቅስቃሴዎች እያደረጉ ነው። ‹‹መንግሥት ግን ትኩረት ሰጥቶት እየተሰራ ያለው በአማራ ክልል ብቻ ነው። በሌሎች ክልል የእሴት ማከል (ላፒደሪ) ባለሙያ ብንፈልግ ላናገኝ እንችላል። ይህም ዘርፉ ገና ያልተነካና ብዙ እንዳልተሰራበት በመሆኑ ብዙ ሥራን የሚጠይቅ የሚያሳይ ነው። በመሆኑም እሴት ከማከሉ ጀምሮ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት መስራት እንዳለበት አምናለሁ›› ይላሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ የከበሩ ማዕድናትን ጥራት ለማወቅ በማንኛውም ኬሚካል ላብራቶሪዎች የሚመረመሩ አይነት ስላልሆነ ማዕድን የጥራት ደረጃውን ለማወቅ የሚያስችሉ የራሳቸው መለኪያዎች አላቸው። ዝም ብሎ በማየት ብቻ ግን የጥራት ደረጃቸው ማወቅ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ አንድ ኤምራልድ ብንወስድ በጥሬ ከሚላክ ይልቅ እሴት ቢታከልበትና ቢቀርብ የሚያስገኘውም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። አሁን ላይ ትንሽ ከሚሰራ ሥራ አንጻር እንኳን ሲታይ ጥሩ የሚባል የገበያ እንቅስቃሴ በመኖሩ ታይታል። በደንብ ቢሰራበት ደግሞ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ሆኖ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ያስችላል። በዚያው ልክ ደግሞ የውጭ ገበያ ፍላጎት እየጨመረ ፈላጊዎች እየበዙ ይመጣሉ፡፡

የማዕድናት ምርመራ ላይ ከባለሙያዎች እጥረት ጋር ተያይዞ ውስነቶች አሉ ያሉት አቶ ዘካርያስ፤ አንዱ ከሰልጠና ጋር ተያይዞ ትምህርቱ የሚሰጡ ተቋማት አለመኖር መሆኑን ይገልጻሉ። እነዚህ ችግር በመፍታት ለብረትነክና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት ላይ በሰፊው ሲሰራ እንደነበር ይገልጻሉ። ማዕድናት ላይ እሴት የማከሉ፣ የመመርመሩ እና ጥራት እንዲጠብቁ የማድረግ ሥራ ትኩረት ሰጥቶ መስራትን ይጠይቃል። ለምሳሌ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ብንወስድ ግብዓት ሊውል የሚችል ማዕድን የኖራ ድንጋይ ነው። ይህ ድንጋይ ጥራቱ በሚገባ እስካልጠበቀ ድረስ፣ ማዕድኑ ትርጉም አይኖረውም። ለዚያም ነው ተመርምሮ የሚሰራው ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ዘካርያስ ገለጻ፤ የከበሩ ማዕድናት ምርመራ ከኬሚካል ላብራቶሪ የተለየ ነው። የተለያዩ መሳሪያዎች በመጠቀም በማረጋገጥ ይቻላል። እንደሌንሲ እና ሀርድነስ/ አይነት መሳሪያዎች መጠቀም የማዕድኑ የጥንካሬ ደረጃ መለየት ያስችላሉ። እንዲሁም ማዕድኑ ጥራት ያለው መሆኑን ወይም አለመሆኑን እና ተፈጥሮአዊ ነው ወይስ አርተፊሻል የሚለውንም ለመለየት ይረዳሉ። አሁን ላይ በአብዛኛው በገበያ ላይ የከበሩ ማዕድናት ተብለው የሚቀርቡ ጌጣጌጦች የተፈጥሮ እና አርተፊሻሉ ቀላቅሎ የመሸጥ ሁኔታ ይስተዋላል። ይህ ደግሞ እንደሀገር ገጽታ የሚያበላሽ ስለሆነ ሰዎች እነዚህ ማዕድናት ለመለየት በጣም ይቸገራሉ። እነዚህ ማዕድናት ለማወቅ የሚጠቅሙ የተለያዩ መሳሪያዎች ያሉ ቢሆንም ምርመራ በጣም ውስንነት ስላለው በአብዛኛው በባለሙያ እገዛ በመለየት የሚሰራበት ሁኔታ ነው ያለው። ሆኖም ግን በባለሙያ የሚሰጠው ድጋፍ ግን በቂ ስላልሆነ ደግሞ በመሳሪያ የታገዘ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።

በአገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከበሩ ማዕድናትን በመሳሪያ ተጠቅመን እየቆረጥን እያለሰለስን ለተለያዩ ጌጣጌጦች ማዋልን መማር እንፈልጋለን የሚሉ ጥያቄዎች ከሕብረተሰቡ እየቀረቡ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ይህም በዘርፉ ላይ ያለው ግንዛቤ እያደገ መምጣቱን ያሳያል ይላሉ። ስለዚህ በተለይ በዘርፉ ላይ ተሰማርተው እየሰሩ ያሉ ተቋማትም ሆኑ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በትብብርና በቅንጅት በመስራት የሚጠበቅባቸው መውጣት እንዳለባቸው አሳሰበዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You