ኦሮሚያ ክልል በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ነጥብ ላስመዘገቡ ተማሪዎች ሽልማትና ማበረታቻ ሰጠ

አዳማ፡- የኦሮሚያ ክልል በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ነጥብ ላስመዘገቡ ተማሪዎች ሽልማትና ማበረታቻ ሰጠ፡፡

የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች እና አስተዋፅኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት ያዘጋጀው የሽልማት መርሃግብር ትናንት ተካሂዷል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ሳዳት በሻር በወቅቱ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ትምህርት ቤቶችን ከማስፋፋት ባሻገር ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ መሥራት ያስፈልጋል።

በክልሉ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋትና ጥራት ያለው ትምህርት መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ በአዳሪና በልዩ ትምህርት ቤቶች የተገኙ ውጤቶችን ወደ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ማሸጋገር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ትምህርት ላይ መሥራት ካልተቻለ ተወዳዳሪ ትውልድና የበለጸገ ሀገር መገንባት አይቻልም ያሉት አቶ ሳዳት፤ የመምህራን አቅምንና ተነሳሽነትን በማሻሻል ተማሪዎችን ውጤታማ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ በበኩላቸው፤ በክልሉ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከተፈተኑ መካከል 305 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል።

በኦሮሚያ ስምንት ሺህ 520 ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ነጥብ አምጥተዋል ያሉት ኃላፊው፤ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ 13 ትምህርት ቤቶች ያስፈተኑትን ተማሪዎች በሙሉ አሳልፈዋል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ያስጀመራቸው የልዩና አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውጤት እያስገኙ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ተማሪዎች ለትምህርት አለመዘጋጀት፣ የመምህራን አቅም ማነስና ተነሳሽነት፣ የትምህርት ቤቶች ግብዓት እጥረትና የአመራሮችና ባለድርሻ አካላት የዘርፉ ችግሮች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You