የኢሬቻ በዓል የገዳ ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል

– የዘንድሮው ኢሬቻ መስከረም 25 እና 26 ይከበራል

አዲስ አበባ፡- የ2017 ዓ.ም ኢሬቻ በዓል የገዳ ሥርዓትና ዕሴትን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የአባገዳዎች ሕብረት አስታወቀ፡፡

የኦሮሞ አባ ገዳዎች ኅብረት የኢሬቻ በዓል አከባበርን አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ በዓሉ የገዳ ሥርዓትና ዕሴትን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ የአባ ገዳዎች ኅብረት ሰብሳቢና የመጫ ኦሮሞ አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል አንድነትንና ሕብረትን በሚያጠናክር እንዲሁም የገዳ ሥርዓት እሴትን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል፡፡

እንደ አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ ገለጻ፤ በዓሉ መስከረም 25 ቀን በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ፣ መስከረም 26 ቀን ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ ሃርሰዴ ይከበራል።

የኦሮሞ ሕዝብ ከሚያከብራቸው የእርቅና የሰላም ክብረ በዓላት መካከል ኢሬቻ አንዱ ነው። ኢሬቻ የይቅርታና የአብሮነት በዓል በመሆኑ ሰላማዊነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር በትብብር መሥራት እንደሚገባ የገለጹት አባ ገዳ ወርቅነህ፤ የበዓሉ ታዳሚያን የእርቅ፣ የፍቅርና የአንድነት ተምሳሌት በመሆን በዓሉን ሊያከብሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢሬቻ በዓል የሰላም በዓል በመሆኑ የኦሮሞን ባህልና ሥርዓት በተከተለ መልኩ መከበር እንዳለበት ገልጸው፤ በዓሉ ባህልና እሴትን ተከትሎ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

የኦሮሞ ቱለማ አባ ገዳና የህብረቱ ምክትል ሰብሳቢ አባ ገዳ ጎበና ሆላ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ላይ የሚታደም ማንኛውም አካል በይቅርታና በፍቅር መሆን አለበት ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ በገዳ ሥርዓት መተዳደር ከጀመረ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል ያሉት አባገዳ ጎበና፤ የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በሆረ ፊንፊኔና ሆራ ሀርሰዴ በድምቀት ይከበራል ብለዋል።

የኦሮሞ ቄሮዎች፣ ቀሬዎችና ፎሌዎች የበዓሉ ባለቤት መሆናቸውን በመግለጽ፤ ኢሬቻ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ማስቻል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ኢሬቻ የይቅርታ፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተለያዩ የሚገናኙበትና ፈጣሪ የሚመሰገንበት በዓል መሆኑን ተናግረዋል።

የአፈንቀሎ አባ ገዳና የህብረቱ ጸሃፊ አባ ገዳ አብዱረዛቅ መሐመድ በበኩላቸው፤ ኢሬቻ እርቅና ሰላም በመሆኑ የዘንድሮው ኢሬቻ በደስታ፣ በአንድነትና በፍቅር ሊከበር ይገባል ብለዋል።

በዓሉ ያለምንም እንከን እንዲከበር ሁሉም በጋራ መቆም እንዳለበት ገልጸው፤ በተለይም ወጣቱ ሚናውን በአግባቡ መወጣት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በዓሉን ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በመሆን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በዓሉን ለመታደም የሚገኙ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የባህል ልብሳቸውን በመልበስ፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በሰላም ማክበር እንደሚገባም ገልጸው፤ የኦሮሞ ቄሮዎች፣ ቀሬዎችና ፎሌዎች ኢሬቻ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር የበኩላቸውን እንዲወጡም ሕብረቱ ጥሪ አቅርበዋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You