“መስቀሉ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መተሳሰብና መከባበር እንዲሰፍን መልዕክት የተላለፈበት ነው” – ዳንኤል ሰይፈሚካኤል የሥነመለኮት መምህር

አዲስ አበባ፡- መስቀሉ በሰው ልጆች መካከል ሁልጊዜም ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መተሳሰብ እና መከባበር እንዲሰፍን መልእክት የተላለፈበት መሆኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ጉባዔ አባልና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ገለጹ፡፡

መምህር ዳንኤል የመስቀል በዓልን በማስመልከት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የመስቀሉ መልእክት ሁልጊዜም ሰላም ፍቅር፣ አንድነት፣ መተሳሰብ፣ መከባበር የተላለፈበት ነው፡፡ ሰከን ብሎ በማሰብ የሚያጋጩንን ነገሮች በማረም፣ ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለአንድነት እና ለመተሳሰብ ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል፡፡

‹‹መንፈሳዊ እና ማሕበራዊ ልእልና ባለባቸው መንገዶች በመመካከር፣ በመወያየት፣ በመግባባት፣ የሚለያዩ ነገሮችን በመተው የሚያግባቡንን ማጥበቅ ይገባናል›› ብለዋል፡፡

መለያየትና መጋጨት ምንም ትርፍ የለውም፤ ሰላም እና ፍቅርንም አይወልድም፤ ከጠብ የሚገኘው ጥፋት፣ የንብረት፣ የሕይወት የአካልና የብዙ ነገሮች ማጣትን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የመስቀል ደመራ የክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ በዓል መሆኑን በመጠቆምም፤ በተግባር የተገኘውን እርቅና ሰላም የምናከብርበት ፍቅርንም የምንገልጽበት እርቅን፣ ሰላምን፣ አንድነት እና ትስስር ሰብስቦ የያዘ ነው ብለዋል፡፡ የሃይማኖታዊ በዓልነቱ መሠረትም የጌታችን የመድኃኒታችን የእየሱስ ክርስቶስ መስቀል ለረጅም ጊዜ ከተቀበረበት ቦታ መገኘቱና መውጣቱን ምክንያት በማድረግ የሚከበር መሆኑንም አንስተዋል፡፡

መስቀሉን ስናከብር የሰውን ልጅ የሚከፋፍሉ ነገሮች እንዳይኖሩ ማድረጉን በማሰብ ሊሆን ይገባል ብለውም፤ በዓሉ የእርቅ፣ የሰላም እና የአንድነት እና የትስስር በዓል መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ቤተክርስቲያን የሰው ልጆች በማህበራዊ ትስስራቸው እርስ በእርስ እንዲዋደዱ ታስተምራለች፡፡ የሚፈጠሩ ማንኛውም አይነት ችግሮችና ልዩነቶች በቅራኔ በብጥብጥና በተለያዩ መንገዶች ሳይሆን እርስ በእርስ በመከባበር እና በመተሳሰብ ሊፈታ እንደሚገባም ታምናለች፡፡ ለትወልድ ቀሪ የሆኑ ጠባሳ ታሪኮችን መተው የለብንም ብለዋል፡፡

ከመስቀሉም የምንማረውና ክርስቶስ ወደዚህች ምድር የመጣው በሰው ልጅ ያለውን ጠብና ክርክር፣ ጥላቻ እና መለያየት ያጠፋ ዘንድ ነው፡፡ በዓሉን መልካምን በማሰብ ማክበር እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

መልካም ስናደርግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ፣ መልካም ገጽታው፣ ውበቱ ይመጣል፡፡ መስቀል በአደባይ የሚከበር ሁሉም ሰው አንድ ሆኖ አይደለም፡፡ በጣም ብዙ አይነት ነን፡፡ ነገር ግን አልተለያየንም መብዛት ውበት ነው፡፡

በዓሉ ደማቅ ሆኖ መከበሩ ማህበረሰብን ያገናኛል፣ የመስቀሉን ታሪክ እና ከነገረ መስቀሉ ጋር መሠረታዊ ትምህርቶች ለማስተላለፍ የሚጠቅም አሳታፊ የአደባባይ በዓል ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

መስቀል የሰው ልጅ ሃጢያቱ የተሻረበት፣ የሰውን ልጅ የዘላለም ሕይወቱን ያቋረጡ ነገሮች ሁሉ የተሸነፉበት እና ከባርነት ወደ ነጻነት፣ ከሞት ወደ ዘላለማዊ ሕይወት፣ ጠብና ግጭት ከነበረባቸው ተጻራሪ ነገሮች ተላቅቆ የፍቅር፣ የሰላም፣ የአንድነት የመተሳሰብ ምልክት የሆነበት ነው፡፡

ነገረ መስቀል በቤተክርስቲያን የሰው ልጅ የድህነት ታሪክ የሚነገርበት፣ የሰው ልጅ ፍጹም ድህነትንና ሰማያዊ ርስትን ያገኘበትን የምንተርክበት በዓል ነውም ነው ያሉት፡፡

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You