መድን ፈንድ በተያዘው ዓመት ሰባት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ዓረቦን ለመሰብሰብ አቅዷል

አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ በ2017 ዓ.ም ሰባት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ዓረቦን ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ 2016 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸምና የ2017 ዓ.ም የሥራ እቅድ አስመልክቶ በትናንትናው ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ደሳለኝ አምባው (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ፈንዱ በንግድ ባንኮችም ሆነ በአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ ለሚቆጥበው ማህበረሰብ ዋስትና የሚሰጥ ሲሆን፤ በባንኮች ላይ ወይም ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ላይ የመውደቅ አደጋ ቢያጋጥም አስቀማጮች እስከ 100 ሺህ ብር ካሳ የሚያገኙበት ሥርዓት ዘርግቷል።

ፈንዱ አባል ከሆኑ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት ካላቸው አማካይ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ ዜሮ ነጥብ ሦስት በመቶ ዓረቦን የሚሰበስብ ሲሆን በዚህም ፈንዱ በ2016 ዓ.ም ስድስት ነጥብ 51 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።

እንደ ዶ/ር ደሳለኝ ገለጻ፤ ተቋሙ በ2017 ዓ.ም ሰባት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ዓረቦን ለመሰብሰብና የተሰበሰበውን ዓረቦን በአግባቡ ኢንቨስት ለማድረግና ለማስተዳደር አቅዷል።

ከብር 100 ሺህ በላይ የተቀማጭ ገንዘብ ለአጣ ግለሰብ ወይም ድርጅት እስከ ብር 100 ሺህ ያለውን ገንዘብ ፈንዱ ተመላሽ የሚያደርግ ሲሆን ቀሪው ገንዘብ የወደቀው ፋይናንስ ተቋም ሂሳብ አጣርቶ ተመላሽ ሊያደርግ እንደሚችል ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ እስካሁን ባለው ሁኔታ ወደ 97 በመቶ የሚሆኑ ገንዘብ አስቀማጮች በባንክ ሂሳባቸው ውስጥ የያዙት ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከመቶ ሺህ ብር በታች በመሆኑ እነዚህ አስቀማጮች ከፈንዱ ሙሉ በሙሉ የመድን ሽፋን የሚያገኙ መሆኑ ተናግረዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ እንዳሉት፤ አንድ የፋይናንስ ተቋም ቢወድቅ ተቋሙን በመተካት ለገንዘብ አስቀማጮች ገንዘባቸውን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ከ90 ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ክፍያ ይፈጽማል።

ለዚህም አንድ የፋይናንስ ተቋም ቢወድቅ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፈንዱን በመወከል ለገንዘብ አስቀማጮች ገንዘባቸውን የሚመልስበት አሠራር ለመፍጠር የመግባቢያ ሰነድ ተዘጋጅቷል ብለዋል። ፈንዱ በአሁኑ ሰዓት 31 ባንኮችን እና 55 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን በአባልነት ይዟል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You