የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

– በዓሉን የሰላምና የአብሮነት ዕሴቶችን በማጠናከር ማክበር እንደሚገባ አመላክተዋል

አዲስ አበባ፡- የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ። በዓሉን የሠላምና የአብሮነት ዕሴቶችን በማጠናከር ማክበር እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልሰ አብዲሳ ለመስቀል በዓል ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ የደመራ እና መስቀል በዓል ያለንን ተጋርተን እርቅ በማውረድና ይቅርታ በማድረግ አንድነታችንን የምናጠናክርበት መሆን አለበት ብለዋል፡፡

በዓሉ ጎረቤት በአንድነት ሆኖ የሩቅና የቅርብ ወዳጅ ተሰብስቦ የሚያከብረው እንደሆነም ጠቅሰው፤ ሕዝቡ የደመራ እና የመስቀል በዓልን ሲያከብር ያለውን በመጋራት እርቅ በማውረድና ይቅርታ በማድረግ አንድነትን በማጠናከር መሆን አለበት ብለዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ለመስቀል በዓል ባሰተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ የመስቀል ደመራ በዓል በሃይማኖታዊም ሆነ በባህላዊ ትውፊቱ ትልቅ አስተምህሮት አለው። ከበረቱ፣ ከታገሉ እና ከጸኑ የማይሳካ ነገር እንደሌለ፤ የጸና የድል ባለቤት እንደሚሆን ከመስቀል ደመራ እንማራለን ብለዋል፡፡

እኛም በሚገጥሙን ፈተናዎች ሁሉ ሳንንበረከክ እንደ ደመራው በአንድነት ከቆምን አሁን ካሉብን ፈተናዎች ሁሉ አልፈን ከደመራው ብርሃን ማግስት የድካማችንን ውጤት ማየት እንደምንጀምር በማመን እንዲሁም የመስቀል ደመራ በዓልን ተሰባስበን ስናከብር ጠፍቶ የቆየውን አንድነት እና መሰባሰብን በማሰብ ብርሃኑ ጨለማውን እንደሚያጠፋው ሁሉ እኛም በፍቅር አንድ ሆነን እና ተሰባስበን ከሠራን ጠንካራ፣ የበለፀገች፣ ዘላቂ ሰላሟ እና አንድነቷ የፀና ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ማየታችን አይቀርም ሲሉ ገልጸዋል።

አንድነታችን ፍፁም በሆነ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ላይ በመገንባት እንደ ደመራችን ብርሃን ተስፋችንን እናድምቅ፤ በአንድነት ተሰባስበን የሚገጥሙንን ፈተናዎች በጽናት እንሻገር ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዋጋ የተከፈለበት መስቀል ምሳሌነት በዚህች ምድር ስንኖር እርሰበርሳችን ያለ ምንም ልዩነት በፍቅር፣ በምህረት እና በመተሳሰብ እንድንኖር ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ መላው የከተማችን ነዋሪዎች የከተማችን ሌላኛው ድምቀት የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል እንደ ምሳሌነቱ የሰው ልጆችን ሁሉ በመውድ፣ እርስበርስ በመተባበር፣ በመከባበርና በፍቅር የዓሉን እሴቶች በመጠበቅ ባማረና በደመቀ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የበኩላችሁን እንድትወጡ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የመስቀል በዓል የአብሮነትና የመተሳሰብ እሴቶች እንዲጠናከሩ በማገዝ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡

የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶችን በማጠናከር የአብሮነትና የመተሳሰብ እሴቶች እንዲጠናከሩ በማገዝ የበኩሉን ሚና እያበረከተ እንደሚገኝ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ገፅታ ያለው መሆኑን በማንሳት በዓሉ ተራርቀው የሠነበቱ ቤተሰቦች የሚገናኙበት፣ ቤተሰባዊና ማህበረሰባዊ ትስስሮች የሚታደሱበት ነው ብለዋል።

የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶችን በማጠናከር የአብሮነትና የመተሳሰብ እሴቶች እንዲጠናከሩ በማገዝ የበኩሉን ሚና እያበረከተ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የዘንድሮውን የመስቀል በዓል ስናከብር ለሠላምና ለአብሮነት መሠረት የሆኑ እሴቶችን በማጠናከር፣ ለጋራ ለውጥና ዕድገት በጋራ ለመትጋት ቃላችንን እያደስን መሆን ይኖርበታል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው፤ በዓሉ የአንድነት፣ የአብሮነት እና የመደመር፣ የኃያልነት የመድመቅ መሠረት መሆኑን ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

እኛ ኢትዮጵያውያን የቱንም ያህል ችግሮች፣ መከራዎች ቢፈትኑንም እነዚህን በጽናትና በትዕግስት በማለፍ እንደ ደመራው አንድ ሆነን ሀገራችን ከተስፋ ብርሃን ወደሚጨበጥ ብርሃን እያመራች ያለችውን መሰብሰባችን ታላቅ ሀገራዊ ብርሃንን እንድናበራ አይነተኛ ምሳሌያችን ነው ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰንም ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

 

በመልዕክታቸው፣ የመስቀል ደመራ በዓል ከኃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ ነው። በመሆኑም በዓሉን ስናከብር በአንድነት፣ በጋራና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዓሉን በማክበር ሂደትም የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት፣ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጎን መቆም ይገባል ያሉት አቶ አሻድሊ፣ በዓሉ በሠላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለደመራና መስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ የመስቀል ደመራ በዓል፤ ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው ዓለም የሰው ልጆች ቅርስነት የተመዘገበ፤ ሕዝቦችን ማስተሳሰር የቻለ ድንቅ ዕሴታችንና የሀገራችን ሀብት ነው ብለዋል፡፡

መስቀል የፍቅር፤ የአንድነትና የመተሳሰብ ተምሳሌት በመሆኑ፤ በዓሉን ስናከብር የመረዳዳትና የአብሮነት ዕሴታችንን በጠበቀ መልኩ በመጠያየቅ፤ በመተሳሰብ እና አብሮነታችንን በማጠናከር ሊሆን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ህዝበ ክርስትያኑ በዓሉን ሲያከብር ዕሴቱን ጠብቆ እንዲከበር በማድረግ የተቸገሩ ወገኖችን በማብላትና የተጠሙትን በማጠጣት ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ነው፡፡

ህብረተሰቡ የመተዛዘንና የመረዳዳት ባህሉን በመተግበር በዓሉን ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር እንዲያከብርም አሳስበዋል።

የተጀመረው የእድገትና የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን በየአካባቢያችን ሰላማችንን አጽንተን ያሉንን ጸጋዎች በመጠቀም ሙሉ አቅማችንን እና ትኩረታችንን በልማት ላይ ልናደርግ ይገባል ብለዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You