– የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት ተከብሯል
አዲስ አበባ፡- የመስቀል ደመራ በዓል ሰዎችን የሚያቀራርብ የፍቅር፣ የሰላምና የአንድነት ተምሳሌት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
የ2017 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተለያዩ ኃይማኖታዊ ሥርዓቶች በትናንትናው ዕለት በድምቀት ተከብሯል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተቀብሮ የነበረው መስቀል የወጣበትን ቀን በውብ ኃይማኖታዊ ሥርዓት በማክበር የመስቀሉን መገኘትና ተቀብሮ አለመቅረትን በማብሰር ግማደ መስቀሉን ይዛና ጠብቃ በማኖሯ እንኮራባታለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ በበርካታ መዛግብታዊ ማስረጃ ከዓለም ቀዳሚ እና የገዘፈ የታሪክ ባለቤት ሀገር ናት መሆኗን ገልጸው፤ ለዚህ ማሳያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሚገኙ ዕንቁ እሴቶች መካከል የመስቀል ደመራ በዓል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
በሁሉም አካባቢዎች በድምቀት የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ባህላዊ ትዕይንትና ሕብረብሔራዊ አንድነትና አብሮነት ጎልተው የሚታዩበት የጋራ በዓል መሆኑን አስታውቀዋል።
መስቀል የአብሮነት የአንድነት፣ የሰላምና የፍቅር ምልክት በመሆኑ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በሙሉ ልብ መነሳሳትና ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ብርቅየና ባህላዊ እሴቶች እንዲለሙ፣ እንዲጠበቁና ለትውልድ እንዲሻገሩ ለማስቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
መስቀል የአብሮነትና የፍቅር ምልክት በመሆኑ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም ሚኒስትሯ ገልፀዋል።
በዚሁ መርሐግብር የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተወካያቸው በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) በኩል መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም የመስቀል ደመራ በዓል ከኃይማኖታዊ እሴቱም ባለፈ የሀገራችን በጎ ገጽታ ማሳያና የቱሪዝም ገቢን የሚያሳድግ በመሆኑን ኃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ ማሻገር ይገባል ብለዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል ሰዎችን የሚያቀራርብ የፍቅር፣ የሰላምና የአንድነት ተምሳሌት በመሆኑ ሁላችንም ልንጠብቀው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ ረጅም ዘመናትን ተሻግረው ላለንበት ዘመን የደረሱ በርካታ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ባለቤት ናት ያሉት ከንቲባዋ፤ እነዚህ ብርቅዬ እሴቶቿ ለሕዝቦቿ ኩራት ከመሆን አልፈው ለዓለም ሕዝብ ሀብት የሆኑ ናቸው። ከእነዚህም መካከል የመስቀል ደመራ በዓል ነው ብለዋል።
ይህ የፍቅርና የሰላም ተምሳሌት የሆነውን በዓል ሕዝቦች በአንድነት ከማክበር ባለፈም ፍቅራቸውንና መልካም ምኞታቸውን የሚለዋወጡበት ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
የመስቀል በዓል ሰዎችን የሚያቀራርብ የፍቅርና የመተባበር ተምሳሌት ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ይህንንም ቀልብ የሚሰብ በዓል ለማክበር በርካታ ቱሪስቶች ታድመዋል። ይህም ለሀገሪቱ ገፅታ ግንባታ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ሃላፊዋ ገልጸዋል።
አዲስ አበባን እንደስሟ አዲስና ውብ ለማድረግ የተሠሩት ሥራዎች ለሕዝባችን ኩራት ለቱሪስቶች ኩራት ነው ብለዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎች በሃይማኖታዊ አልባሳት በመድመቅ በዓሉን ለመታደም ለመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ባህላችንን ሊያስተዋውቁ ይገባልም ነው ያሉት።
በዓሉን ስናክብር የጥልና መለያየት መንፈስ በማስወገድ፣ እርስ በእርስ በመዋደድና በመተሳሰብ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው፤ ከተማ አስተዳደሩ የበዓላት እሴታቸውና ትውፊታቸው ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፉ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም