“በአንድ ሳምንት ውስጥ ደብተሮች ለተማሪዎች ይሰራጫሉ” – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምገባ ኤጀንሲ
አዲስ አበባ፡- የ2017 ዓ.ም የትምህርት መርሐግብር መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም የተጀመረ ቢሆንም እስካሁን የደብተር አቅርቦት ስላልደረሳቸው በትምህርታቸው ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው በአዲስ አበባ ከተማ የሚማሩ ተማሪዎች ገለጹ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምገባ ኤጀንሲ በበኩሉ ከዛሬ ጀምሮ በአንድ ሳምንት ውስጥ 9 ሚሊዮን 125 ሺህ በላይ ደብተሮችን ለተማሪዎች አሰራጭቶ ለማጠናቀቅ መታቀዱን አስታውቋል።
የአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ተማሪ ሕሊና ደምሴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጸችው፤ የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መርሐግብር መስከረም 6 ቀን የተጀመረ ቢሆንም እስካሁን የመማሪያ ደብተር አልተሰጠንም።
በዚህም በየትምህርት አይነቱ በየቀኑ ስለሚጻፍ ደብተር ከሌለ ወደኋላ የሚያስቀር መሆኑን ተናግራ፤ ከማጥናት ይልቅ ያለፉትን ማስታወሻ በመገልበጥ ጊዜ ማባከኑ ትምህርቷ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥርባት መሆኑንም ጠቅሳለች።
ደብተር ስላልተሰጠን ካለፈው ዓመት በተረፈ ደብተር እየተማርኩ ነው የምትለው ሌላዋ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነጃት ጌድዮን፤ ዘንድሮ 12 የትምህርት አይነት እየተማረች ቢሆንም በአንድ ደብተር ላይ 3 የትምህርት አይነት ማስታወሻ ለመገልበጥ መገደዷን ተናግራለች።
በመንግሥት እየቀረበው ያለው የደብተር እና የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) አቅርቦት መግዛት ለማይችሉ ወላጆች ችግር የሚያቀል መሆኑን ጠቅሳ፤ በወቅቱ ተደራሽ አለመሆኑ ተማሪው ላይ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ ባለፈ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወላጆች ለድጋሚ ወጪ ይዳርጋል ስትል ተናግራለች።
የአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ እንዳልካቸው ደጀኔም፤ የ2017 የትምህርት ዘመን መርሐግብር መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም የተጀመረ ቢሆንም የተማሪዎች ግብዓት ከማሟላት አንጻር የተወሰኑ እጥረቶች አሉ ብለዋል።
ይህንንም ለመቅረፍ ትምህርት ቤቱ አምና ከተረፈው የደብተር ግብዓት ለተወሰኑ ተማሪዎች የተሰጠ ቢሆንም በቂ አይደለም። ተማሪዎች አዲስ ደብተር ባይገዙም አምና በተረፈው እንዲማሩ የተደረገ ሲሆን፤ በሂደት ይሟላል የሚል እምነት እንዳላቸው አብራርተዋል።
ደብተር አቅርቦት መዘግየት ተማሪዎች ማስታወሻ ለመያዝ ከመቸገራቸውም በላይ በዘገየ ቁጥር መማር ማስተማሩን በማወክ የተወሰነ እንቅፋት ስለሚፈጥር ቀደም ብሎ መቅረብ አለበት ብለዋል።
በመንግሥት የሚደረገው የትምህርት አቅርቦት ድጋፍ ለመማር ማስተማሩ ብቻ ሳይሆን ለወላጆች ኢኮኖሚያዊ ጫናም ለማቃለልና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ግብዓት ወሳኝ ነው ያሉት ርዕሰ መምህሩ፤ በተለይም በዝግጅት ምዕራፉ ላይ ቀደም ተብሎ የመማሪያ ግብዓትን ቢመጡ ዝግጅቱን ሙሉ ያደርገዋል ብለዋል።
የዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ በላይ ወልደጻዲቅ በበኩላቸው፤ ትምህርት በተጀመረበት ዕለት ለተገኙ ደብተር እና ዩኒፎርም የታደለ ቢሆንም ከግማሽ በላይ ተማሪዎች አላደረሳቸውም።
የተሰጣቸው ተማሪዎች በየክፍል ደረጃቸው በሚማሩት የትምህርት አይነት ልክ የተሰጣቸው ሲሆን ግብዓቱ ሲገባ አንድ ደርዘን ከአንድ ስኩየር ደብተር ለእያንዳንዱ ተማሪ የሚሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የትምህርት ግብዓት በተለይም ለተማሪዎች የትምህርት ክትትልና ማስታወሻ ለመያዝ ወሳኝ የሆነው ደብተር በትምህርታቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥርና በቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይሰናከሉ ትምህርቱ ከመግፋቱ በፊት መቅረብ አለበት ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምገባ ኤጀንሲ የግብዓት አቅርቦት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምነወር ኑረዲን ለኢፕድ በሰጡት ምላሽ፤ የተማሪዎች የትምህርት ግብዓት በተለይም የደብተር አቅርቦት የግዢ ሂደት ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም በአሠራር ሂደት ላይ በተፈጠሩ
ተግዳሮቶች ምክንያት የተወሰነ መዘግየት እንደነበር ገልጸዋል።
ኤጀንሲው በከተማዋ እና በከተማዋ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች የደንብ ልብስ እና የደብተር አቅርቦት የሚያካሄድ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘንድሮ የትምህርት ዘመንም በአጠቃላይ ለአንድ ሚሊዮን ሠላሳ አራት ሺህ በላይ ተማሪዎች የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) እና ደብተር የሚቀርብ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በመጀመሪያ ዙር ደብተር ስርጭት 739 ሺህ ደብተር የቀረበ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን አስታውቀው፤ ከዛሬ ጀምሮ በአንድ ሳምንት ውስጥ 9 ሚሊዮን 125 ሺህ በላይ ደብተሮችን ለተማሪዎች አሰራጭቶ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልጸዋል።
አቶ ምነወር እንደገለጹት፤ በዚህ የተማሪዎች የትምህርት ግብዓት ማሟላት ተግባርም ትልቅ በጀት የሚጠይቅና በጊዜ እና ግብዓት አቅርቦት ሂደት የመንግሥትን አሠራርና ሂደት በተከተለ መልኩ ይካሄዳል።
በሂደቱ ላይ የግብዓት አቅራቢ፣ የመንግሥት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች ብሎም ሰፊ ቁጥር ያለው የተማሪዎችን ጨምሮ በርካታ ተዋንያን የሚሳተፉበት በመሆኑ በርካታ ተግዳሮቶች ያጋጥማሉ ብለዋል።
በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የምርቶቹን ብዛትና ጥራት ለማረጋገጥ እና ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ የአሠራር ማሻሻያዎች እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ኤጀንሲው በዚህ ዓመት የታየውን ችግሮችና መልካም ጎኖች በትኩረት በመለየት በሚቀጥለው የተሻለ አሠራር በመፍጠር ትምህርት ግብዓት አቅርቦቱን ከትምህርቱ እኩል ለማቅረብ ይሠራል። በዚህ ትውልድን ለመገንባት ዋነኛ ዘርፍ በሆነው ትምህርት ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና እና ኃላፊነት መወጣት እንደሚገባ አቶ ምነወር ተናግረዋል።
ማሕሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም