ከኮሪደር ልማቱ ጋር በተያያዘ አዳዲስ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እየተስፋፉ መምጣታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ እነዚህ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከተማውን ከማስዋብና ከማዘመናቸውም ባለፈ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ በማድረጉ ረገድ አንዳንድ ለውጦች እንዳሉ የሚያሳዩ የመንገድ ዲዛይኖችና አንዳንድ ግንባታዎች እየታዩ ነው፡፡
ለመሆኑ እነዚህ ዲዛይኖች፣ የመንገድ ሥራዎች እና ሌሎች የሕንፃና የመሳሰሉት ግንባታዎች በታሰበላቸው ዓላማ ልክ ለአካል ጉዳተኞች ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ ነው?
የአዲስ አበባ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ገለታው ሙሉ፤ አካል ጉዳተኞችም በኮሪደር ልማቱ እንደ አንድ የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀው ትልቁ ጥያቄያቸው ተደራሽነት ከመሆኑ አኳያ በተለይ የመንገድ ልማቱ መልካም አጋጣሚ በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።
ይህ ማለት ግን ፍፁም ችግር የለበትም ማለት አይደለም የሚሉት ፕሬዚዳንቱ እስካሁን ከተማችን ላይ ከነበሩት ከፍተኛ የመሠረተ ልማትና የመረጃ አውታሮች ችግር አንፃር ኮሪደር ልማቱ ላይ እየታዩ ያሉ በጎ ነገሮች አሉ፤ ነገር ግን ደረጃውን ጠብቆ ከመሥራት አንፃር ችግር አለ ይላሉ፡፡
ለምሳሌ በእግረኛ መንገድ ላይ ለዓይነ ስውራን መንገድ መምሪያ ተብለው የተሠሩትን ቢጫ መስመሮች ስናይ አልፎ አልፎ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ደረጃቸውን ጠብቀው የተሠሩ እንዳሉ ብዙ ቦታዎች ላይ ደግሞ ደረጃቸውን ጠብቀው ባለመገንባታቸው ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ያብራራሉ። አንዳንዴም መስመሩ ላይ ሌላ ነገር የማስቀመጥ ሁኔታዎች እንዳሉ መታዘባቸውንም ይገልፃሉ፡፡
በተጨማሪም የእግረኛ ማቋረጫ ዜብራዎች ዳርና ዳር ባሉ የእግረኛ መንገዶች መሐል አንድ የዊልቸር ተጠቃሚ በቀጥታ ተሻግሮ ወደ እግረኛ መንገዱ ለመውጣት የሚያስችል ተደርጎ ከመሥራት አንፃርም አብዛኛው ቦታ ችግር መኖሩን የሚገልፁት ፕሬዚዳንቱ አንዳንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ሄዶ አገልግሎት ለማግኘትም ለአካል ጉዳተኞች አስቸጋሪ መሆኑን ያነሳሉ።
በተለይ ደረጃውን የጠበቀና አካል ጉዳተኞችን የሚያካትት ከመሆን አኳያ የሚቀር ነገር እንዳለ ጠቅሰው የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው በቀጣይ ሥራዎችም በተቻለ መጠን ሁሉን አቀፍ የሆነ እና አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ ያደረገ ሥራ እንዲከናወን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ኢንጅነር እያሱ ሰለሞን በበኩላቸው ከተማችን ገና እየለማች ከመሆኑ አንፃር ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ጠቅሰው በሂደት እየተስተካከሉ እንደሚሄዱ ይገልፃሉ፡፡ ባለሥልጣኑ አዳዲስ መንገዶችን በሚሠራበትና ነባር መንገዶች ላይ ማሻሻያ በሚያደርግበት ጊዜ አካልጉዳተኞችን ታሳቢ እንደሚያደርግም ይገልፃሉ።
በፊት ከነበረው አኳያ ለውጦች እንዳሉም አይካድም ይላሉ፡፡ ከዚህ ባሻገርም ለእነሱ በተሠሩ መንገዶች ላይ የቆሻሻ መጣያ በማስቀመጥ፣ ችግኝንና ሌሎችም ነገሮችን በመትከል ለታሰበለት ዓላማ እንዳይውል መደረጉን ከመከላከል አንፃር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
በ2016 ዓ.ም ኮሪደር ልማቱን ሳይጨምር ከ40 ኪሎሜትር በላይ የእግረኛ መንገድ ግንባታ ተከናውኗል። አሁን ላይ እንደበፊቱ ተሽከርካሪ ብቻ የሚተላለፍባቸው መንገዶች ላይ ትኩረት መስጠት ሳይሆን መንገድ ለሁሉም የሚል እሳቤ ተይዞ የከተማዋን መንገዶች በዛ ደረጃ መሥራት ከጀመርን ዓመታት አልፈዋልም የሚሉት ኃላፊው የኮሪደር ልማቱ ደግሞ የበለጠ ይህንን አጠናክሮ የሚሄድ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
ለዓይነስውራን መተላለፊያ የሚሆኑት መንገዶችም ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰው ባለሥልጣኑ ከዚህ በመነሳት ወደፊት የተሻሉ ሥራዎችን እንደሚሠራም ይገልፃሉ፡፡ ለ2017 ዓ.ም በተመሳሳይ ሁኔታ አዳዲስ በሚገነቡ እንዲሁም በነባር መንገዶች ማሻሻያ የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ ባለሥልጣኑ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም ይገልፃሉ፡፡
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር መቆያ ዓለማየሁ ከኮሪደር ልማቱ ጋር በተያያዘ አዳዲስ ሕንፃዎች ሲገነቡ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆኑ እየሠሩ እንዳለ ይገልፃሉ፡፡
የድሮ ሕንፃዎችን በማደሱ ረገድም ቢሮው አንዳንድ ለይስሙላ የተቀመጡ የአካል ጉዳተኛ መገልገያዎችን የማስተካከል ሥራዎችን እየሠራ እንዳለ ጠቅሰው የኮሪደር ልማቱ አንዱ ዓላማ ከተማውን ማዘመን ስለሆነ ሕንፃዎች የሚገነቡት ወይንም የሚታደሱት አካል ጉዳተኞችን ከግንዛቤ በማስገባት እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡
ነፃነት ዓለሙ
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2017 ዓ.ም