ከቱሪዝም አዝመራው ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት በትኩረት መሥራት የሚያስፈልግበት ወቅት!

በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የምጣኔ ሀብቱ ምሰሶ ተብለው ከተያዙት አምስቱ የምጣኔ ሀብቱ ዘርፎች መካከል አንዱ የቱሪዝም ዘርፍ መሆኑ ይታወቃል። ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ያለበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል።

ዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ በመሆን፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ኢኮኖሚውን በማንቀሳቀስና የሀገር ገጽታን በመገንባት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው እንደመሆኑ ከዘርፉ የሚጠበቁትን ለማግኘት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ይገኛሉ።

አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችንና መሠረተ ልማቶችን የመገንባት፣ ነባሮቹን ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ፣ መስሕቦችን የማስተዋወቅና ለገበያ የማቅረብ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። የመስሕብ ስፍራዎችን በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ ለማድረግ እየተሠራ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም በርካታ መስሕቦችን በዩኔስኮ ማስመዝገብ ተችሏል።

ለዘርፉ ፋይዳቸው ከፍተኛ ነው ተብለው የታመናባቸው ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቶች ትኩረት እንዲሰጣቸው፣ እንዲለሙ፣ እንዲተዋወቁና ለገበያ እንዲቀርቡ፣ የቱሪዝም ዘርፉ ተዋንያንንና መላው ሕዝብ የሚገናኙባቸውን ኤግዚቢሽኖች ማካሄድና ትስስሮች እንዲፈጥሩ ማድረግ ላይ ተሠርቷል፤ እየተሠራም ነው።

በተለይ ለዘርፉ ልማት እምቅ አቅም አላቸው በተባሉ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ወቅት የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ጉብኝት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። ከትራንስፖርት፣ ከፀጥታና ደኅንነት፣ ወዘተ ጋር ተያይዞ ችግሮች እንዳይገጥሙ ከሕዝቡ ጋር አስቀድሞ መሥራት ተለምዷል።

ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ አሟጣ ልትጠቀምባቸው የሚገባ ወቅቶች እንዳሏት ይታወቃል። በእነዚህ ወቅቶች በርካታ የውጭ ቱሪስቶች ወደ ሀገሪቱ እንደሚመጡም ይታወቃል፤ በሀገር ውስጥ ከፍተኛ የጉዞና የመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች የሚደረግባቸው በዓላትና የመሳሰሉት ሥነሥርዓቶች የሚካሄዱባቸው በርካታ ወቅቶች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ወቅቶች አንዱ ይህ የተያዘው የመስከረም ወር ነው።

ይህ ወር ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ብዙ ትርጉም አለው። ወሩ ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመታቸውን የሚጀምሩበት፣ ከጨለማው የክረምት ወቅት ወደ ብርሃናማው የበጋ ወቅት ሽግግር የሚያደርጉበት፣ ወንዞች የሚጎድሉበት፣ ዝናቡ ከአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢ መሸሽ የሚጀምርበት፣ ነፋሻማ አየር ስፍራውን የሚይዝበት፣ እሸት በስፋት መድረስ የሚጀምርበት፣ ሰውም ከብቱም ሰብሉም ምቹ የአየር ሁኔታ የሚያገኝበት ተወዳጅ ወር ነው።

በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል ደመራ በዓልን የክርስትና እምነት ተከታዮች በድምቀት የሚያከብሩበት፣ በርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች አዲስ ዓመታቸውን የሚያከብሩበት፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የኢሬቻ በዓል የሚከበርበት ወር ነው።

በኢትዮጵያ ለብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት እንዲሁም ለሃይማኖት እኩልነት የተሰጠው ትኩረት እነዚህ የኅብረተሰብ ከፍሎች፣ ባሕላዊ እሴቶቻቸውንና እምነታቸውን፣ ወዘተ በአደባባይ የሚከብሩበት ሁኔታ ይህን ወር በባሕላዊ ሥነሥርዓቶች ይበልጥ ደማቅ እንዲሆን አድርጎታል።

ወቅቱ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ እንዲሟሟቁ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በዓላቱን በየትውልድ ቀዬያቸው ለማክበር፣ የበዓል አከባበሮችን ለመጎብኘት፣ ክረምት የተራራቀውን ቤተሰብን ለመጠየቅ፣ ወዘተ. ሲሉ ሰዎች በብዛት ሰፊ የጉዞ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። ከትውልድ ሀገራቸው ርቀው የሚገኙትም ወደ ሀገራቸው ከሚመጡባቸው ወቅቶች አንዱ ይሄው ወቅት ነው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ደግሞ አያሌ ኢትዮጵያውያን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ቱሪስት ይሆናሉ። ይህም ለቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ አቅም እንደሆነ ይታመናል።

በዚህ ወቅት ደግሞ ለዘርፉ አስተዋፅዖ የሚያደርጉ በርካታ ክንውኖች የሚካሄዱበት የዓለም ቱሪዝም ቀን በኢትዮጵያ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፤ ይህን ቀን ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፏን ለማንቀሳቀስ ትልቅ አቅም አድርጋ ስትጠቀምበት እንደቆየች ሁሉ ዘንድሮም ይህንኑ ታደርግበታለች።

ይህን ታላቅ የቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚደረግበትን ወቅት ኢትዮጵያውያንና መንግሥታቸው በወሳኝ መልኩ ተጠቃሚ ለመሆን በሚገባ ሊሠሩበት ይገባል። ለዚህም የሚመለከታቸው መንግሥታዊና የግል ተቋማት፣ መላው ሕዝብ አበክረው መሥራት ይኖርባቸዋል። ለጎብኚዎች ምቹ ማረፊያዎችን በማመላከት፣ የሚጎበኙ ቦታዎችን በማሳየት፣ የቱሪስት ቁሳቁስን በማቅረብና በመሳሰሉት ሁሉ በስፋት መሥራት ይጠበቃል።

ገቢ ማግኘት አንድ ነገር ሆኖ ጎብኚዎችን በሚገባ ማስተናገድ መቻል በቀጣይም ሀገሪቱ የጎብኚዎች ፍላጎት እንድትሆን የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል። የዘንድሮ ጎብኚዎች ለመጪዎቹ ጎብኚዎች መረጃ ሰጪ እንደመሆናቸው ተገቢውን መረጃ ይዘው እንዲሄዱ ማድረግ ያስፈልጋል፤ እነሱም ተመላልሰው ሀገሪቱን እንዲጎበኙ በጥሩ ሁኔታ ማስተናገድ ይጠበቃል። ጎብኚዎች ዓላማ አድርገው የሚመጡት በዓላቱን ሊሆን ቢችልም፣ ከዚሁ ጎን ለጎን አዳዲሶቹን የቱሪስት መስሕቦችና ነባሮቹን ማስጎብኘት ላይም መሠራት ይኖርበታል።

ይህ ወር አርሶ አደሩ አዝመራ እንደሚሰበስብበት ወቅት ሊታይ ይገባዋል። አዝመራ በወቅቱና በአግባቡ ካልተሰበሰበ ብዙ ከተለፋበት የግብርና ሥራ የሚጠበቀውን ምርት ማግኘት አይቻልም። በቱሪዝም ዘርፉም እንደዚያው ነው። ሀገሪቱ፣ ኅብረተሰቡ፣ ሌሎች የቱሪዝም ዘርፉ ተዋንያን ዘርፉ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ሲሠሩ እንደቆዩ ሁሉ፣ ከእዚህ የቱሪዝም ታላቅ አዝመራ ምርታቸውን ለመሰብሰብ መረባረብ ይኖርባቸዋል።

የቱሪዝም ተዋንያኑ የቱሪስት እንቅስቃሴው እንዲሳለጥ በማድረግ፣ የሠላም ባለቤት የሆነው ሕዝብ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ሠላሙን በመጠበቅ የቱሪስቶች ቆይታ የሚራዘምበት፣ ሀገር ተገቢውን ጥቅም የምታገኝበት ሁኔታ እንዲፈጠር አበክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል!

አዲስ ዘመን መስከረም 14/2017 ዓ.ም

Recommended For You