የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለመግቢያ ፈተና የሚያዘጋጀው መተግበሪያ

ወጣት አማን በረከት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ትምህርት ዘርፍ ተመርቋል። የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለመግቢያ ፈተና (Entrance exam) የሚያዘጋጅ ፈተናዎችን የያዘ ‹‹ኢትዮ ማትሪክ (Ethio Matric)›› የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ሰርቶ ጥቅም ላይ አውሏል።

ወጣት አማን የ12ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት አጋጥሞት ያለፈና አሁንም አብዛኛው ተማሪ የሚያልፍበትን መንገድ አደላድሏል። ለፈተና ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት የሚያጋጠሙ ችግሮች በምን ዘዴ መፍታት ይቻላል የሚለውን አእምሮው ሲያሰላስል ቆይቷል። ዩኒቨርሲቲ ከገባም በኋላ ጊዜ ወስዶ ችግሩን እንዴት መፍታት እንደሚችል በማሰብ አውጥና አውርዶ ከተማረው ትምህርት ጋር በማዋሃድ የመፍትሔ ሀሳብ ማመንጭት ችሏል። በመፍትሔውም ኢትዮ ማትሪክስ የተሰኘ መተግበሪያ መስራት ችሏል።

ወጣት አማን ዩኒቨርሲቲ እያለ ጀምሮ ሲያስበው የቆየው ቢሆንም ሀሳቡን ወደመሬት ለማውረድ ሲያስብ ብዙ ጊዜ እንደፈጀበት ይናገራል። ‹‹መጽሐፍን አንብቦ አለመጨረስ የአብዛኛው ተማሪዎች ችግር መሆኑን ተማሪም ሆኜ ጀምሮ በቅርበት ስለማውቀው ይህን ችግር በመፍታት ተማሪዎች ሁሉንም መጽሐፍ አንብበው ከመጨረሳቸው በፊት እንዴት እንዲለማመዱ ማድረግ ይቻላል የሚለውን ሳስብ የተማርኩትን ትምህርት ተጠቅሜ በሙያዬ መፍትሔ ማምጣት እንደምችል ስለገባኝ ሥራውን ጀመርኩ›› ይላል።

‹‹ኢትዮ ማትሪክ (Ethio Matric)›› ያለፉት ዓመታት የማትሪክና የመግቢያ ፈተና ጥያቄዎች ለመስራት የሚጠቅምና ለአጠቃቀም በተመቸ መልኩ የተሰራ መተግበሪያ ነው። መተግበሪያው ተግባራዊ ከሆነ አምስት ዓመታት አስቆጥሯል። ይህ መተግበሪያ ተግባራዊ ከመደረጉ አምስት ዓመታት በፊት ባሉት ሌሎች መተግበሪያዎች ላይ በአብዛኛው የሚገኙትና እንዳሉ የሚታወቀው መጻሕፍት ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት ብዙ ስለሆኑ ተማሪዎች መጻሕፍቱን አንብበው እስካልጨረሱ ድረስ ጥያቄዎች ለመስራት ስለሚከብዳቸው አንዱ ጥያቄ ሰርተው ሲከብዳቸው ተጨማሪ ሌላ ጥያቄዎች መስራት ስለማይችሉ ብዙ ጥያቄዎች ሳይሰሩ ይተውታል። እንደገና ደግሞ ካላቸው ጊዜ አንጻር ሁሉንም መጻሕፍት አንብበው ለማዳረስ የማይችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።

አማን ‹‹ተማሪዎች የቱንም ያህል ተግተው ቢያነቡ በተለይ የመጨረሻዎቹን ሁለት እና ሦስት ምዕራፍ ሳይጨርሱ የመግቢያ ፈተና ይደርስባቸዋል። ስለዚህም የፈተናዎቹን ጥያቄዎች መስራት እያለባቸው ይህንን ምዕራፍ ጨርሼ ሰራዋለሁ እያሉ ሲዘናጉ የሚፈልጉትን ማዳረስ ሳይችሉ ጊዜው ስለሚያጥራቸው ፈተናውን ሳይሰሩት ይቀራሉ›› ይላል።

ታዲያ ይህ መተግበሪያም ተማሪዎች የሚያጋጥማቸው ችግር ለመፍታት መጻሕፍቱን በየምዕራፍ በመከፋፈል በየእያንዳንዱ ምዕራፍ ያሉ ጥያቄዎችን በተደራጀ መልኩ በማቅረብ መስራት የሚችሉበት መንገድ ቀርቧል። ብዙ ተማሪዎች ሁሉንም መጻሕፍት የማዳረስ እድላቸው አነስተኛ ስለሆነ ካነበቡት መጻሕፍት ጎን ለጎን አንዱን ምዕራፍ ሲጨርሱ ጥያቄዎች እዚያ በመስራት ያሉበት ሁኔታ እየፈተሹ ማሻሻል የሚገባቸው እያሻሻሉ እንዲሄድ ይረዳቸዋል።

መተግበሪያው በሞባይል የሚሰራ ሲሆን በሞባይል እንዲሆን የተደረገበት ዋንኛ ምክንያት በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የትምህርት አሰጣጥ የዲጂታል አሠራር የተከተለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ነው። አብዛኛው ተማሪዎች ሞባይል ያላው በመሆኑ ሥራውን ቀላል ያደርገዋል። ሞባይል የሌላቸው ጥቂት ተማሪዎች ቢኖሩም ከወላጆች አልያም በቅርበት ካሉ ሰዎች ሊያገኝ ስለሚችሉ መተግበሪያውን አውርደው መጠቀም የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይችላሉ የሚል እምነት እንዳለው ይናገራል።

መተግበሪያው ባለፉት ስምንት ዓመታት የመግቢያ ፈተና ጥያቄዎችን፣ ከ2008 እስከ 2015 ዓ.ም የመግቢያ ፈተናዎች፣ ጥያቄዎች በየምዕራፉ ከፍፍሎ ያስቀመጠ እና ለጥያቄዎቹ ማብራሪያ ያካተተ ነው። መተግበሪያው ጥያቄዎች እና መልሶቻቸውን የያዘ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ለእያንዳንዱ ጥያቄ ማብራሪያ ይሰጣል። ለምሳሌ አንድ ጥያቄ ከጠየቀ በኋላ ለዚያ ጥያቄ የሚሆን የተሻለ ማብራሪያ የሚሰጥ በመሆኑ ተማሪ ጥያቄውን ከመመለስ ባሻገር ስለጥያቄ በደንብ እንዲያውቅ፣ እንዲረዳና እንዲገነዘብ ይረዳዋል።

ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከማትሪክ ጥያቄ ጎን ለጎን የመግቢያ ፈተና ጥያቄዎች መስራት ጠቃሚ መሆኑን ተማሪዎች በሚገባ ያውቃሉ የሚለው ወጣት አማን፤ ለዚህም ነው በመተግበሪያው ሁለቱን በአንድ ማካተት ያስፈለገው ይላል። አብዛኛው ትኩረት ያደረገባቸው ግን የባለፉት ዓመታት የመግቢያ ፈተና ጥያቄዎች ላይ ነው። ከዘንድሮ ዓመት ጀምሮ የተለያዩ አዳዲስ ነገሮችን ለማካተት ማሰቡንም አጫውቶናል።

ወጣት አማን እንደሚለው፤ ምንም እንኳን መተግበሪያ ተግባራዊ ከሆነ አምስት ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም በተለይ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ግን ትላልቅ የሚባሉ ማሻሻያዎች ተደርገውበታል። መተግበሪያው ይበልጥ እየታወቀ የመጣው ደግሞ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ነው ብሏል። እሱ እደሚለው እስካሁን ድረስ መተግበሪያውን እየተጠቀሙ ያሉ ተማሪዎች ቁጥር እጅግ በርካታ ሲሆን፤ አሁን ላይ ባለው መረጃ መሰረት ከ390 ሺ በላይ የሚሆን ተጠቃሚዎች መተግበሪያውን አውርደዋል። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ተማሪዎችም እንዲሁ የመተግበሪያው ተጠቃሚ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

መጀመሪያ ላይ መተግበሪያ ተግባራዊ እንደተደረገ ተማሪዎች ወዳሉበት አካባቢዎች በአካል በመሄድ ስለ መተግበሪያ ያላቸው አስተያየት እንዲሰጡት ይጠይቅ እንደነበር የሚያስታወሰው አማን፤ በወቅቱ የመተግበሪያው ተጠቃሚዎች በቁጥር አነስተኛ ቢሆኑም እነርሱ በሰጡት አስተያየት መሠረት የተለያዩ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደቻለ ተናግሯል። በማሻሻያው ቀደም ሲል ያልተካተቱ እንዲካተቱ ሆኖ መተግበሪያው አሁን የያዘውን ይዘት እንዲኖር ተደርጓል ሲል ያስረዳል።

‹‹አሁን ላይ የመተግበሪያው ብዙ ተጠቃሚዎች ተማሪዎች ስላሉ በቴሌግራም እና በስልክ ጭምር ግንኙነት እናደርጋለን። በመተግበሪያው ተጠቃሚ የሆኑ ተማሪዎችም በመተግበሪያ ላይ የብዙ ዓመታት ጥያቄዎችን ከነማብራሪያቸው ማግኘት እንደቻሉና ብዙ ለማወቅ እንደረዳቸው በመግለጽ ይህንን ቢጨምር ወይም ደግሞ በዚህ መልኩ ቢሻሻል የሚሉትን ሀሳብ እየሰጡን ነው። በዚህም መነሻነትም በሚቀጥሉት ጊዜያት በየጊዜው ብዙ ነገሮች በማሻሻል አዳዲስ ነገሮች በመጨመር ተመራጭ መተግበሪያ እንዲሆን በማድረግ ለተማሪዎች መተግበሪያ ተጠቅመውበት የተሻለ ውጤት የሚያመጡበት እንዲሆን እፈልጋለሁ›› ይላል።

መተግበሪያ ሲሰራ ሀሳብ አመንጭቶ የሰራው አማን ቢሆንም አሁን ላይ ግን በብዙ ባለሙያዎች በጥምረት እየተሰራ ይገኛል። ብዙ የሶፍትዌር ዲፕሎፐሮች፣ የእያንዳንዱ ትምህርት ዘርፍ መምህራን እና ሌሎች አጋር አባላትም በአንድ ላይ የሚሰሩበት ነው። በተጨማሪም የሚሰራው ሥራው እንደወቅቱ የሚለያይ ሲሆን ሥራው በሚኖርበት ወቅት እንደየአስፈላጊነቱ ብዙዎችን ያሳትፋል። ለአብነትም መግቢያ ፈተናዎችን መስራት ሲያስፈልግ ከየትምህርት ዘርፉ የተውጣጡ መምህራን እንዲሳተፉ ተደርጎ ይሰራል ሲል ያብራራል።

መተግበሪያውን ጭኖ ለመጠቀም የሚፈልግ ተጠቃሚ እስካሁን ባለው አሠራር ለአገልግሎቱ የተቀመጠውን ክፍያ እንዲከፍሉ ይጠይቃል የሚለው አማን፤ ይህም ክፍያውን በባንክ፣ በሞባይል ባንኪንግ እና በቴሌ ብር አማካኝነት ከፈጸሙ በኋላ መተግበሪያውን አውርደው መጠቀም የሚችሉበት አሠራር መዘርጋቱን ይገልጻል። በመቀጠልም የኢትዮ ማትሪክ መተግበሪያ አገልግሎቶችን ለማግኘት ተጠቃሚዎች ክፍያው ከከፈሉ በኋላ ያሉትን አገልግሎቶች ሁሉንም መጠቀም እንደሚችሉ አስገንዝቧል።

መተግበሪያው ተማሪዎችን ከመርዳት አንጻር የሚሰጠው ከፍተኛ ጠቀሜታ ሆኖ ሳለ የተቀመጠው ክፍያ በጣም አነስተኛና የተማሪዎችን የመክፈል አቅም ያገናዘበ መሆኑን ይጠቅሳል። ይሁን እንጂ መተግበሪያ እየሰጠ ካለው አገልግሎት አንጻርና አሁን ላይ እያስከፈለ ያለው ክፍያ አነስተኛ በመሆኑ በቀጣይም ከዚህ የበለጠ የተሻለ ሥራ ለመስራት ይረዳ ዘንድ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻል። በመሆኑም በዘንድሮ ዓመት በመጠኑም ቢሆን የዋጋ ጭማሪ እንደሚያደርግ አስታወቋል።

ወጣት አማን እንዳብራራው፤ አንድ ተማሪ መተግበሪያው ለመጠቀም መተግበሪያ/ አፕሌኬሽኑን/ ጎግል ፕሌይስቶር ላይ በመግባት በማውረድና መጠቀም ሲፈልግ ለአገልግሎቱ የሚጠይቀውን የአገልግሎት ክፍያ በመክፈል ሙሉ አገልግሎት ማግኘትና መጠቀም ይችላል። ይህ ከመሆኑ በፊት ደግሞ ተጠቃሚው /ተማሪው/ የሚሰጠው የመተግበሪያ መፈተሻ እንዲኖረው ተደርጓል። ተማሪው መጀመሪያ መተግበሪያው ለማውረድ ሲገባ መተግበሪያውን አይቶት፣ ወድዶት እና መርጦት እንዲጠቀምበት ስለሚያስፈልግ ሙከራ ፈተናዎችን ያለምንም ክፍያዎች መጠቀም ይችላል። መተግበሪያ በዚህ መልኩ ከፈተሸ በኋላ መተግበሪያው ከተመቸው የሚጠበቅበት የአገልግሎት ክፍያ ከፍሎ አገልግሎቱን እንዲያገኝ ይደረጋል።

ይህ መተግበሪያ እንደቲክቶክና ቴሌግራም ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም የማስተዋወቅ ሥራዎች ተሰርቷል፤ እየተሰራም ነው። በተጨማሪም መተግበሪያው በደንብ እንዲተዋወቅ ተማሪዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሶ፤ አንድ ቀድሞ መተግበሪያው የተጠቀመ ተማሪ ለሌሎች ተማሪዎች በመንገርና በመጠቆም ተማሪዎች እርስ በእርስ በሚሰጣጡት መረጃ ተደራሽነቱ እንዲሰፋ ምክንያት እየሆነ መሆኑን ተናግራል።

በቀጣይም አሁን ላይ መጽሐፉ እየተቀየር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ለተማሪዎች የማይጠቅሙ ጥያቄዎችን በመቀነስ፤ የሚጠቅሙትን ደግሞ በመጨመር እንዲበዙ የማድረግ ስራ ይሰራል የሚለው አማን፤ ተማሪዎቹ እንደዚህ አይነት የማትሪክ ጥያቄዎችና መግቢያ ፈተናዎች ቀድመው አግኝተው ከሰሩና የራሳቸውን ጥረት ካደረጉ ውጤታማ የማይሆኑበት ምክንያት እንደሌለ ይገልጻል።

ተማሪዎች የሚፈለገውን ውጤት አምጥተው ውጤታማ እንዲሆኑ ስለሚፈልግ ወደፊት ተማሪዎችን ውጤታማ ሊያደርጉ የሚያስችል ሥራዎች እንደሚሰራ የሚገልጸው አማን‹‹ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ያለውን የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች እንኳን ብንመለከት ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ኢትዮ ማትሪክ የተሰኘውን መተግበሪያ ሲጠቀሙ እንደነበር አውቀናል። የሞባይል መተግበሪያው በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች እንደተጠቀሙት ማወቅ ችለናል›› ይላል።

ለአብነት ሲጠቅስም ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ውጤት ካመጡት ተማሪዎች መካካል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ያለውን ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች መተግበሪያውን መጠቀማቸው ታውቋል። በዘንድሮ ዓመት ከትግራይ ክልል ከፍተኛ ውጤት ያመጣውን ተማሪ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችም እንዲሁ መተግበሪያውን እንደተጠቀሙ መረጃዎቹ ያሳያሉ። በተጨማሪም በከፍተኛ ደረጃ ተማሪዎችን በማሳለፍ ከሚታወቁ ትምህርት ቤቶች መካከል ለምሳሌ ኦዳ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመተግበሪያው ተጠቃሚ ነበሩ።

‹‹ከምንም በላይ ግን የእነዚህ ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ የራሳቸው ጥረት ነው። ተማሪዎቹ መተግበሪያውን ተጠቅመው ጥያቄዎች መስራት መቻላቸው በራሱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የራሱ አስተዋጽኦ ያበረክታል›› የሚለው አማን፤

እነዚህ ተማሪዎች መተግበሪያውን ሲጠቀሙ ስማቸውና የትምህርት ቤታቸውን ስም ስለሚያስመዘግቡ ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ሲያመጡ መተግበሪያውን መጠቀማቸው እና አለመጠቀማቸው በቀላሉ መለየት ያስችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ተማሪዎች ራሳቸው በስልክና በቴሌግራም በኩል መተግበሪያው እንደጠቀማቸው በመናገር የሚያሳወቁበት ሁኔታ መኖሩን አመላክቷል ።

ጀማሪ ሥራ ፈጣሪ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህ መተግበሪያ ተግባራዊ እንዲደረግና ወደ ቢዝነስ እንዲቀየር በሚደረጉ ሂደቶች ጥቃቅን የሚመስሉ ተግዳሮቶች አጋጥመውት እንደነበር የሚያነሳው አማን፤ ሆኖም ግን እነዚህን መሻገርና ወደኋላ መተው ስለሚያስፈልግ በሀሳቡ ያለውን ፈጠራ ወደ ተግባር በመለወጥ ለብዙዎች መፍትሔ ሆኖ ተደራሽ እንዲሆን ጠንክሮ መስራትና ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይገልጻል። በቀጣይም ችግር ሆኖ መፍትሔ ለሚሹ ነገሮች በተማረበት የትምህርት መስክ በሙያው የሚችለው የመፍትሔ ሀሳብ በማመንጨት እንደሚሰራ ተናግሯል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን መስከረም 14/2017 ዓ.ም

Recommended For You