‹‹የመድን ፈንድ መቋቋም ገንዘብ አስቀማጮች ዋስትና እንዲኖራቸው ያስችላል›› – አቶ መርጊያ ዋቆያ የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የኦፕሬሽን ዳይሬክተር

አሜሪካን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን እና እንግሊዝን ጨምሮ ብዙዎቹ ያደጉ ሀገሮች የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ በማቋቋም ከቀደምቶቹ መካከል ተጠቃሾች ናቸው:: አንዳንዶቹ እነ ካናዳና ጣሊያን፣ እንግሊዝን የመሳሰሉትን ሀገራት ከአንድ አልፈው ሁለት ዓይነት የመድን ፈንድ በማቋቋም፤ ገንዘብ አስቀማጮች በባንኮች ላይ ከፍተኛ መተማመን እንዲኖራቸው ይሠራሉ:: መንግሥት የሚያስተዳድረው መድን ፈንድ አንደኛው ሲሆን፤ ሌላኛው በግለሰቦች የሚቋቋም መድን ፈንድ ባደጉት ሀገራት እየተለመደ መጥቷል::

የመድን ፈንዶች ዋነኛ ሥራ ባንኮች እና ማይክሮ ፋይናንሶች በሚያጋጥማቸው ቀውስ ምክንያት ሲወድቁ፤ ፈንዶቹ ለገንዘብ አስቀማጮቹ ገንዘብ የሚከፍሉበት መንገድ ነው:: በርግጥ ሰዎች የፋይናንስ ተቋማትን አምነው ገንዘባቸውን እንዲያስቀምጡ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ማቋቋም ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው::

ሆኖም በኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ሳይቋቋም በፊትም ቢሆን፤ ሕዝቡ በፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ የሚያስቀምጠው በሙሉ መተማመን ነበር:: አሁን ደግሞ መተማመኑን የበለጠ መሬት ለማስረገጥ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ተቋም በማቋቋም ኢትዮጵያ 184ኛ ሀገር ሆናለች::

የተቀማጭ መድን ፈንድ በአዋጅ ቁጥር 482/2013 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ ሥራውን ከጀመረ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል:: ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሆነው ይኸው ፈንድ፤ ዋና አላማው በባንክና በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ተቀማጭ ገንዘብ ላስቀመጡ ግለሰቦች የመድን ሽፋን መስጠት ነው:: በዚሁ መነሻ ቀድሞም ቢሆን በኢትዮጵያ ባለው ተሞክሮ ሰዎች ገንዘባቸውን ባንክ ሲያስቀምጡ፤ በመንግሥት ርግጠኞች ናቸው:: አዋጁ ከፀደቀበት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ፈንዱ ያስፈለገበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው? ኢንሹራንስ የምትሰጡት ወይም ለአስቀማጮች የምትከፍሉት ጣራ ምን ያህል ነው? የምትከፍሉትን ገንዘብ የምታገኙት ከየት ነው? የሚሉ እና ሌሎችም ተያያዥ ጥያቄዎችን በማቅረብ ከኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የኦፕሬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርጊያ ዋቆያ ጋር ያደረግነውን ቆይታ በሚከተለው መልኩ አቅርበንላችኋል::

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የተቋቋመበት አላማ ምንድን ነው ?

አቶ መርጊያ፡- ሰዎች ‹‹መንግሥት ገንዘባችንን ያስቀምጥልናል›› ብለው መንግሥትን አምነው በባንክና በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ ያስቀምጣሉ:: ነገር ግን ባንክ ሊወድቅ ይችላል:: ተቸግሮ ገንዘቡን ባንክ ያስቀመጠ ሰው ባንኩ በራሱ ችግር ቢወድቅ፤ አስቀማጩ ገንዘቡን ማጣት የለበትም:: በሌሎች ሀገሮች የተለመደው አስቀማጮች ኢንሹራንስ አላቸው:: ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የገንዘብ አስቀማጮች ኢንሹራንስ ሳይቋቋም ቆይቷል:: ሆኖም የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ በአዋጅ ቁጥር 482/2013 ዓ.ም ተቋቁሟል:: የመድን ፈንድ ተቋቁሞ ሥራውን ከጀመረ ሁለት ዓመታት አስቆጥሯል::

የተቋቋመው ለገንዘብ አስቀማጮች ጥበቃ ለመስጠት ነው:: ከዚህ በኋላ አንድ ባንክ ወይም ማይክሮ ፋይናንስ ከወደቀ ገንዘብ አስቀማጮች ገንዘባቸውን አያጡም:: ይህ የሆነው በዋናነት ለገንዘብ አስቀማጩ ኢንሹራንስ ለመስጠት እና ሕዝቡ በፋይናንስ ተቋማቱ እንዲተማመን ለማስቻል ነው:: ቀደም ሲል ሰዎች ‹‹ባንኮች ወይም የፋይናንስ ተቋማት የሆነ ነገር ቢሆኑ ገንዘቤ ምን ይሆናል? ›› ብለው ይሰጉ ነበር:: ከአሁን በኋላ ገንዘቡን የሚያስቀምጥ ሰው ባንኩ ችግር ቢገጥመው ‹‹ገንዘቤን ከየት አገኛለሁ?´ ብሎ አይሰጋም::

ይህ ፈንድ በመፈጠሩ ማይክሮ ፋይናንሶችም ቢወድቁ፤ ገንዘብ አስቀማጭ እንደሚከፈለው ስለሚተማመን ገንዘቡን ቤቱ አያስቀምጥም፤ ይቆጥባል:: የቁጠባው ጥቅም ለገንዘብ አስቀማጩ ብቻ አይደለም:: ለሀገር እና ለሕዝቡ ትልቅ ጠቀሜታ አለው:: የፋይናንስ ዘርፉ ተረጋግቶ ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል ያግዛል:: በተጨማሪ ከሕዝቡ ከፍተኛ ቁጠባ እንዲሰበሰብ ዕድል ይፈጥራል:: የተቀመጠው ቁጠባ ደግሞ ለብድር ይውላል:: በተዘዋዋሪ ኢኮኖሚው ያድጋል::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ተሞክሮ ሰዎች ገንዘባቸውን ባንክ ሲያስቀምጡ በመንግሥት ርግጠኞች ናቸው:: አዋጁ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የፀደቀበት እና ፈንዱ አሁን ላይ ያስፈለገበት የተለየ ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ መርጊያ፡- ደንቡ ከረቀቀ በኋላ ብዙ ጊዜ ቆይቷል:: እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ለውጥ ሲመጣ ወዲያው ፀድቋል:: ከዚህ በፊት የዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍም በየጊዜው የገንዘብ አስቀማጮች ፈንድ ለምን የላችሁም? ብለው እንደ ግኝት በተደጋጋሚ ያቀርቡ ነበር:: ‹‹የፋይናንስ ዘርፍ ካለ የገንዘብ ተቀማጭ ፈንድ መኖር አለበት::›› የሚል ተደጋጋሚ አስተያየት ይሠጡ ነበር:: ሆኖም ለረዥም ጊዜ ሳይኖር ቆየ:: በኋላ ሲታይ ለፋይናንስ ዘርፉ መረጋጋት አንደኛው መሳሪያ መሆኑ ታወቀ::

ብሔራዊ ባንክ ባንኮችን ይቆጣጠራል:: ይህንን የሚያደርገው እያንዳንዱ ባንክ ጠንካራ እና ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥሉ ነው:: ብሔራዊ ባንክ የሚሠራው እንዳለ ሆኖ የተቀማጭ ኢንሹራንስም አስፈላጊ ነው:: በሌላ በኩል የተቋቋመው በአይ ኤም ኤፍም በዓለም ባንክም ተቀባይነት ስላለው ነው::

አዲስ ዘመን፡- ፈንዱ የፋይናንስ ተቋማት ሲወድቁ ገንዘቡን የሚሰጠው ከየት አምጥቶ ነው?

አቶ መርጊያ፡- ገንዘቡን ለመክፈል በቂ ገንዘብ ሊኖረን ይገባል:: ለሕዝቡ መተማመኛ ልንሰጥ እና አለንላችሁ ለማለት የምንችለው በቂ ገንዘብ ሲኖረን ነው:: ይህንን በሚመለከት ከመንግሥት በወጣው ደንብ መሠረት፤ ከባንኮች እና ከማይክሮ ፋይናንሶች ገንዘብ መሰብሰብ እንድንችል በሕግ ሥልጣን ተሰጥቶናል::

አሁን ባለው ሁኔታ የሚሰበሰበው ባንኮች እና ማይክሮ ፋይናንሶች ካላቸው ቁጠባ ውስጥ ዜሮ ነጥብ ሶስት በመቶ በየዓመቱ እየከፈሉን ነው:: ከሰበሰብን በኋላ መልሰን ኢንቨስት እናደርገዋለን:: በኢንቨስትመንቱ ተጨማሪ ገንዘብ እናገኛለን:: በሁለት ዓመት ውስጥ ሰብስበን ክምችቱ 12 ነጥብ 11 ቢሊዮን ብር ደርሷል:: አሁን መክፈል የሚያስችል በቂ ሀብት እያመነጨን ነው:: ይሄ አንዱ የገንዘብ ምንጭ ነው::

በተጨማሪ ግን ከፋይናንስ ተቋማት ለመቋቋሚያ ዜሮ ነጥብ አራት በመቶ ሰብስበን ነበር:: በተጨማሪ 850 ሚሊዮን ብር ይሰበሰባል:: አሁን ትልቁ ሥራ ከባንኮች እና ከማይክሮ ፋይናንሶች ገንዘብ መሰብሰብና ኢንቨስት ማድረግ ነው:: ኢንቨስት የምናደርገው ለግምጃ ቤት ሰነድ ግዢ ነው:: እንዲሁም ገንዘቡ ንግድ ባንክ የሚቀመጥ ሲሆን፤ እዚያም ትርፍ ያስገኛል:: አንድ ባንክ ወይም ማይክሮ ፋይናንስ ሲወድቅ ባለን ገንዘብ ለእነርሱ ክፍያ እንፈፅማለን::

አዲስ ዘመን፡- የምትከፍሉት ክፍያ ጣራው ምን ያህል ነው?

አቶ መርጊያ፡- በባንኩ ወይም በማይክሮ ፋይናንሱ ቁጠባ ያስቀመጡ እስከ 100 ሺህ ብር ድረስ እንሠጣቸዋለን:: ይህ ማለት አንድ ሰው ሃምሳ ሺህ ብር ካለው ሙሉውን ብር ያገኛል:: 100 ሺህ ብር ካስቀመጠ፤ ያስቀመጠውን ሙሉ ለሙሉ ያገኛል:: 150 ሺህ ብር ካስቀመጠ ግን 100ሺህ ብሩን ያገኛል:: ቀሪው 50 ሺህ ብር ደግሞ የባንኩ ወይም የማይክሮ ፋይናንሱ ንብረት ተሸጦ ይሠጠዋል ማለት ነው::

የተቀማጭ ኢንሹራንስ በባህሪው አካሄዱ ሙሉ ለሙሉ አይሸፍንም:: የትም ሀገር ላይ ይህ አይደረግም:: 100 ሺህ ብሩን ግን እያጠናን ወደፊት ከፍ ልናደርግ እንችላለን:: አሁን ባለው ሁኔታ በባንክ እና በማይክሮ ፋይናንስ ገንዘብ የሚያስቀምጡት 97 በመቶ የሚሆኑት ከ100ሺህ ብር በታች ነው:: ስለዚህ እኛ የምንሠራው ለብዙሃን ነው:: ብዙ ሕዝብ ከዚያ በላይ አስቀምጦ፤ እኛ የምንሰጠው አነስተኛ ከሆነ ተቋማችን ሕዝብን ጠቀመ ማለት አይቻልም:: ትልልቅ ተቀማጭ ያላቸው እጅግ በጣም ውስን ናቸው:: ስለዚህ የእኛ ሽፋን ብዙሃንን የሚያዳርስ ነው::

አዲስ ዘመን፡- 100ሺህ ብርን እንደመነሻ የወሰዳችሁት አቅማችሁን ማዕከል አድርጋችሁ ነው? ወይስ በትክክል ብዙሃኑን ስለሚሸፍን ነው?

አቶ መርጊያ፡- ሁለቱንም እናያለን:: ለምሳሌ የሕዝቡ ቁጠባ አድጎ የብዙሃን ቁጠባ 200ሺህ ብር ከደረሰ፤ ብዙዎች የእኛን ፈንድ አይጠቅምም ብለው የራሳቸውን አማራጭ ሊወስዱ ይችላሉ:: ችግሩ ሕዝቡ በፈንዱ ካላመነ ሰዎች ችግር ተፈጠረ ሲባል ሮጠው ባንክ ይሰለፋሉ:: ባንክ ወደቀ ቢባልም ፈንዱ ካለ ሕዝቡ ገንዘቡን እንደሚያገኝ ርግጠኛ ስለሚሆን፤ ወደ ባንክ አይሔድም:: ፈንዱ ምንም አይጠቅመኝም ብሎ ካሰበ ግን አደጋ ነው:: ስለዚህ ሽፋናችን ለሕዝቡ ምን ያህል የሚዋጥ ነው? የሚለውን በየጊዜው ጥናት እናጠናለን:: ያም ቢሆን የማይቻል ቃል መግባትም ተገቢ አይደለም:: ስለዚህ የምናየው ከሁለቱም በኩል ነው:: በቅርቡ ማሳደግ የምንችል ከሆነ እናሳድጋለን:: ነገር ግን የፈንዱ አቅም እና የሰፊው ሕዝብ ሽፋን ጎን ለጎን ታይቷል::

አዲስ ዘመን፡- ዜሮ ነጥብ ሶስት ከተቀማጭ ከመሰብሰብ በተጨማሪ ገንዘቡን ኢንቨስት የምታደርጉት በምን መልኩ ነው?

አቶ መርጊያ፡- ለእያንዳንዱ ባንክም ሆነ ማይክሮ ፋይናንስ የሚጠበቅባችሁን ይህን ያህል ገንዘብ ገቢ አድርጉ ብለን ደብዳቤ እንጽፍላቸዋለን:: ሂሳባችን ያለው ብሔራዊ ባንክ ነው:: ባንኮችም ሆኑ ማይክሮ ፋይናንሶች ገንዘቡን የሚያስገቡልን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነው:: እኛ ደግሞ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ጨረታ በየሁለት ሳምንቱ ሲወጣ፤ ፈንዱ የራሱን ጥናት በየጊዜው ያደርጋል:: እየተጫረተ ይገዛል:: በውስጥ አሠራር ስንሳተፍ እና ስናሸንፍ ሰርተፍኬት ይላክልናል:: በየዓመቱ ትርፉን እና ያለውን ሰብስበን በድጋሚ ኢንቨስት እናደርጋለን::

አዲስ ዘመን፡- ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጭ የሏችሁም?

አቶ መርጊያ፡- በብዛት ገንዘቡን የምናስቀምጠው የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ (ትሬዠሪ ቢል) ላይ ነው:: ከዚህ በፊት እንደሚታወቀው የግምጃ ቤት ሰነድ የሚያስገኘው ብር በጣም ትንሽ፤ በዓመት 10 በመቶ የማይሞላ ነበር:: በዚህ ላይ እኛም ስጋት ነበረብን:: ምክንያቱም ይሄ ፈንድ የሚሰበስበው ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ መጠኑን በማሳደግ የፈንዱን አቅም ለማሻሻል እና ሕዝቡ የሚተማመንበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያስቸግራል ብለን ተጨንቀን ነበር::

የዋጋ ንረት አለ:: አሁን ግን የግምጃ ቤት ሰነድ የሚያስገኘው ብር በጣም እየጨመረ ወደ 18 በመቶ ደርሷል:: ይህ ለፈንዱ መልካም ዕድል ነው:: በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው፤ አብዛኞቹ ትኩረት አድርገው የሚሠሩት የግምጃ ቤት ሰነድ ላይ ነው:: ምክንያቱም ለክፍያ ሲፈለግ ወዲያው ገንዘቡን ማግኘት የሚቻለው እዚያ ላይ ሲሆን ነው:: ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ላይ ከገባ ግን ገንዘቡን ወዲያው ማግኘት ይከብዳል::

አዲስ ዘመን፡- ከፋይናንስ ተቋማት ተቀማጭ ዜሮ ነጥብ ሶስት በመቶ መሰብሰባችሁ የሚቀጥለው እስከ መቼ ነው? በሂደት የሚቀንስበት ሁኔታ አለ?

አቶ መርጊያ፡- የጀመርነው ወደኋላ ቀርተን ነው:: ሌሎች ሀገሮች ኢንሹራንስ ፈንድ አቋቁመው ብዙ ልምድ ወስደዋል፤ አሁን ብዙ ካፒታል አላቸው:: እኛ ግን አዲስ ጀማሪዎች በመሆናችን በቂ ፈንድ ሊኖረን ይገባል:: አሁን ባለው ሁኔታ ገና ከጀመርን ሁለት ዓመታችን በመሆኑ ዛሬ ላይ በቀጣይ ክፍያውን በዚህ መጠን እንቀንሳለን ለማለት ያዳግታል::

አሁን በዚሁ እንቀጥላለን:: ነገር ግን ፈንዱ በቂ ገንዘብ አለኝ ብሎ ሲያምን መቀነስም ይቻላል:: ወይም ፈንዱ በቂ ገንዘብ ካለው መሰብሰቡንም ሊያቆም ይችላል:: አስፈላጊ ከሆነም መልሶ ለአባል ፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ ሊመልስ ይችላል:: ወይም ከመንግሥት ያገኘውን ድጋፍ ‹‹ራሴን ችያለሁ›› ብሎ ገንዘቡን ሊመልስ ይችላል:: አሁን ግን ገና አዲስ ጀማሪዎች በመሆናችን በቂ ገንዘብ አለን ብለን የምናምንበት ጊዜ ላይ አይደለንም::

ከላይ የተነሳው ለምን 100 ሺህ ብር ብቻ ይሆናል? ለምን 200 እና 300 ሺህ አናደርግም የሚለውም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው:: በ100 ሺህ ብር ብቻ መተማመን መፍጠር ከባድ ሊሆን ይችላል:: ለአስቀማጮች የሚከፈለው እስከ 200ሺህ እና 300 ሺህ ቢሆን፤ የተሻለ ሊሆን እና በጣም ጥሩ እምነት ሊገነባ ይችላል:: ስለዚህ ያንን ገንዘብ ለማግኘት

ፈንዱን የበለጠ በገንዘብ ማጠናከር ያስፈልጋል:: ሆኖም የዜሮ ነጥብ ሶስት በመቶ ክፍያውም እንደ ሁኔታው እየታየ የሚቀንስ ይሆናል::

በዚህ ሀገር ላይ ሁለት ዓይነት ወለድ የሌለው እና ወለድ ያለው የባንክ ሥርዓት አለ:: ገንዘብ አስቀማጮቹም በተመሳሳይ መልኩ ወለድ የሚፈልጉ እና ወለድ የማይፈልጉ ናቸው:: እኛ የምንሠራው የሁለቱንም ፍላጎት ለማሟላት ነው:: ከሁለቱ ገንዘብ ይሰበሰባል:: የሚቀመጠው ሕጉ በሚፈቅደው መልኩ ተለያይቶ ነው:: ስለዚህ የተሰበሰበውን ደግሞ መልሰን ኢንቨስት እናደርጋለን:: አሁን ባለው ሁኔታ ንግድ ባንክ እናስቀምጣለን::

አዲስ ዘመን፡- ገንዘቡን ኢንቨስት ከማድረግ በተጨማሪ መልሳችሁ ባንክ የምታስቀምጡት ከሆነ ዞሮ ዞሮ ያው አይደለም?

አቶ መርጊያ፡- በርግጥ ገንዘቡን የምናስቀምጠው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው:: ሁሉም በብሔራዊ ባንክ አስፈላጊው ጥበቃ የሚደረግላቸው በመሆኑ፤ ምንም እንኳ ብዙዎቹ ባንኮች ጥሩ ሁኔታ ላይ ቢሆኑም፤ ንግድ ባንክ ካለው ማኔጅመንትም ሆነ ከሌሎች አኳያ ሲታይ የተሻለ ጥንካሬ አለው:: ባንኩ ትልቅ ባንክ በመሆኑ የመውደቅ ዕድሉ እጅግ አነስተኛ ነው:: በብሔራዊ ባንክ የሚሰጠው ትኩረትም ከፍተኛ ነው:: ይህ የተወሰነው በቦርድ ደረጃ ፀድቆ ነው::

በርግጥ የዓለም ባንክም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቦ ነበር:: ለባንክ ኢንሹራንስ ገንዘቡን መልሶ ባንክ ማስቀመጥ አይገባም የሚል ሃሳብ ተሰንዝሯል:: ሆኖም ሌላ አማራጭ የለንም:: ሙዳራባ ላይ ከማስቀመጥ ውጭ ምንም አማራጭ የለም:: እዚያ ገቢ ካላደረግነው ትርፍ ማመንጨት አንችልም:: ስለዚህ ንግድ ባንክ ተመርጧል::

አዲስ ዘመን፡- የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ምን ይመስላል?

አቶ መርጊያ፡- ሌሎች ሀገሮች የሰበሰቡትን ወደ ባንክ አይወስዱም:: ምክንያቱም እነርሱ ሀገር የካፒታል ማርኬት አለ:: በአስተማማኝ የካፒታል ማርኬቶች ላይ ይሳተፋሉ:: አማራጭ የሌላቸው እና ባንክ የሚያስቀምጡ በጣም ጥቂት ናቸው:: ወደ ባንክ ማስቀመጥ የሚመከር እና የተለመደ አይደለም:: እኛ ሀገር ወለድ አልባ የራሱን አካሄድ የተከተለ ሱኩክ የሚባል የግምጃ ቤት ሰነድ ያስፈልጋል፤ እርሱ እኛ ሀገር ዲዛይን አልተደረገም:: ዲዛይን ሲደረግ የምናስተካክለው ይሆናል::

አዲስ ዘመን፡- አንድ ባንክ ወደቀ የሚባለው ምን ሲሆን ነው?

አቶ መርጊያ፡- ይሄንን የሚያውቀው አንድ ባንክ ጤናማ አለመሆኑን የሚተነትነው ብሔራዊ ባንክ ነው:: የሚከታተለው እና ድጋፍ የሚሰጠው ሲወድቁም ወድቀዋል የሚለው ብሔራዊ ባንክ ነው:: መጀመሪያ ፈቃድ ብሔራዊ ባንኩ ይሰጣል:: በኋላም ‹‹አንድ ባንክ ሥራ መሥራት አይችልም፤ ከዚህ በኋላ ወድቋል›› ብሎ ሲያምን በራሱ መስፈርት ፍቃድ ይነጥቃል:: በመቀጠል ባንኩ ወይም ማይክሮ ፋይናንሱ መውደቁን ወደ ፈንዱ ያስተላልፋል:: ለገንዘብ አስቀማጮቹ ገንዘባቸውን መልሱላቸው ይላል:: ይህንን የሚገልፀው ብሔራዊ ባንክ ነው:: ነገር ግን እኛ ባለን መረጃ መሠረት ሁሉም ባንኮች በጥሩ ደረጃ ላይ ናቸው::

እኛ ባንኮቹ ያሉበትን ደረጃ ጤናማነታቸውን የመከታተል ኃላፊነትም የለብንም:: ብሔራዊ ባንክ ባለው የጤናማነት መመዘኛዎች አማካኝነት ጥሩ ደረጃ ላይ ናቸው ማለት ይቻላል:: እኛን የሚያስጨንቀን ይሄኛው አይደለም:: እኛ የምንጨነቀው ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ነጥቄያለሁ ቢል፤ ለመክፈል ዝግጁ ሆነን መጠበቃችንን ነው::

አዲስ ዘመን፡- ብሔራዊ ባንክ ከሚነጥቀው ፈቃድ በተጨማሪ ለምሳሌ ባንኮች በተፈጥሮ አደጋ በመሬት መንቀጥቀጥ ወይም ሰው ሠራሽ በሆነ መልኩ በጦርነት ምክንያት አንድ ባንክ ወይም ማይክሮ ፋይናንስ የተቀማጭ ገንዘቡን ለመክፈል ቢቸገሩ የምታስተናግዱበት ሁኔታ አለ?

አቶ መርጊያ፡- በቅድሚያ መታወቅ ያለበት አንድ ባንክ ሊወድቅ የሚችለው በምን ምክንያት ነው የሚለው ነው:: ዋናው ጉዳይ በተፈጥሮ አደጋ ተበዳሪዎቹ ላይ የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም ድርቅ ተከስቶ ተበዳሪዎቹ መክፈል ባይችሉ ባንኩም ለአስቀማጮቹ የሚሰጠውን ገንዘብ ሊያጣ ይችላል:: ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ ችግር ያጋጥመውና ባንኩ ወደቀ ይባላል:: በሌሎቹም በተለያዩ ምክንያቶች ባንኩ ከወደቀ ፈንዱ ክፍያ የመክፈል ግዴታ አለበት::

አዲስ ዘመን፡- ክፍያውን የምትፈፅሙት በምን መልኩ ነው?

አቶ መርጊያ፡- ይሄ ፈንድ ቢሮ ያለው አዲስ አበባ ብቻ ነው:: ገንዘብ አስቀማጮች ደግሞ የሚገኙት በተለያዩ ክልሎች ነው:: እነርሱ ጋር የምንደርሰው በተወካይ አማካኝነት በ (ፔ ኤጀንት) ነው:: ባንኩ በጣም ሰፊ ተደራሽነት ስላለው የቅርንጫፍ ብዛቶቹም እንደሚታወቀው ብዙ በመሆናቸው፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካኝነት ለማሰራጨት ተዋውለናል:: ክፍያ የምንፈፅም ከሆነ ክፍያው የሚሆነው በንግድ ባንክ ነው:: ወደፊት ቴክኖሎጂው ሲያድግ በቀጥታ በቴክኖሎጂው ክፍያ የምንፈፅምበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል:: አሁን ባለው ሁኔታ ግን የእኛ ከፋይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በቴሌ እና በሳፋሪኮም ወይም ኢ-መኒ አካባቢ የሚቀመጡ ገንዘቦችን በተመለከተ ምን ይላሉ?

አቶ መርጊያ፡- በርግጥ እነዚህ በቴክኖሎጂ ተቀማጭ እየሰበሰቡ ነው ማለት ይቻላል:: ነገር ግን እነዚህኞቹም ቢሆኑ የሚሰበስቡትን ዋናውን ገንዘብ የሚያስቀምጡት ባንክ ውስጥ ነው:: ባንኮች ላይ ያለው ገንዘብ ኢንሹራንስ አለው:: ስለዚህ በባንኮች በኩል በተዘዋዋሪ እነሱም ኢንሹራንስ አላቸው ማለት ይቻላል:: ባንኩ ላይ የሆነ ነገር ቢፈፀምም ገንዘባቸውን ያገኛሉ:: ዞሮ ዞሮ ግን የእነዚህም አካውንት ኢንሹራንስ ውስጥ የተካተተ ነው:: ነገር ግን አካሄዱን በዝርዝር ማውጣት ይቀራል:: ወደፊት ከጀርባ ያሉት ተጠቃሚዎች በምን መልኩ ተጠቃሚ ይሆናሉ? የሚለው ነገር በዝርዝር የሚታይ ይሆናል::

አዲስ ዘመን፡- ከተቋቋማችሁ በኋላ የፋይናንስ ተቋም ወድቋል ብላችሁ የከፈላችኋቸው አስቀማጮች አሉ?

አቶ መርጊያ፡- አንዲት ከ1 ሺህ 500 በታች ገንዘብ አስቀማጮች ያሏት አነስተኛ ማይክሮ ፋይናንስ ፈርሳለች:: ለእዚህች ማይክሮ ፋይናንስ አስቀማጮች ክፍያ ለመፈፀም ዝግጅት እያደረግን ነው:: ዋን ማይክሮ ፋይናንስ የምትባል ሲሆን፤ ከእርሷ ውጪ ያጋጠመ ነገር የለም:: ይህች ማይክሮ ፋይናንስ አነስተኛ እና በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ገንዘብ የምትሰበስብ ስለነበረች፤ በተጨማሪ የሚጠበቅባትን ክፍያ ትፈፅም ስለነበር ፈንዱ ለአስቀማጮች የመክፈል ኃላፊነት አለበት::

አዲስ ዘመን፡- ሰዎች ገንዘባቸውን ሕብረት ሥራ ማህበራት ጋር ያስቀምጣሉ፤ ከሕብረት ሥራ ማህበራት ይበደራሉ:: እናንተ የሕብረት ሥራ ማህበራትን ታካትታላችሁ? ሌሎች የማታካትቷቸው የፋይናንስ ተቋማት አሉ?

አቶ መርጊያ፡- አባል የሚሆኑት በሕጋችን ላይ በግልፅ የተቀመጡት ከኅብረተሰቡ ገንዘብ ለመሰብሰብ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የወሰዱ ብቻ ናቸው:: ማንኛውም ፈቃድ የወሰደ ግን አባል መሆን ግዴታው ነው:: የትም ቦታ እየሔድኩኝ ገንዘብ እሰበስባለሁ የሚል የመድን ፈንዱ አባል መሆን አለበት:: ይሄ በግዴታ የተቀመጠ ነው:: በአሁኑ ጊዜ አባል ያልሆኑት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና የሕብረት ሥራ ማህበራት ናቸው:: የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከሕዝቡ ገንዘብ አይሰበስብም:: የሕብረት ሥራ ማህበራት ደግሞ ፈቃድ የሚወስዱት ከብሔራዊ ባንክ አይደለም:: ከሌላ መንግሥታዊ አካል ነው:: ቁጠባውንም የሚሰበስቡት ከአባሎቻቸው ነው:: እርስ በርሳቸው የሚተዋወቁ በመሆናቸው ይህን ያህል ሕዝብ ላይ አደጋ አያመጡም::

ሕብረት ሥራ ማህበራት ብዙ ቅርንጫፍ እየከፈቱ ገንዘብ ስለማይሰበስቡ እነርሱ አይካተቱም:: በርግጥ አንዳንድ በስፋት የሚንቀሳቀሱ፣ ፈርጠም ያሉ እና ከባንክ ጋር የሚቀራረቡ አሉ:: በሌሎች ሀገሮች እነርሱም የኢንሹራንሱ አባል ናቸው:: ይህ መታየት አለበት:: ምክንያቱም ከብዙ ሰው ገንዘብ ስለሚሰበስቡ እና ብዙ ሰው ስለሚያበድሩ ብዙ ሰው ተጎጂ ይሆናል:: እነርሱን ከጀርባ ሆኖ የሚጠብቅ መኖር አለበት:: የእኛ ተቋም ግን ትኩረቱ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ላገኙት ብቻ ነው::

አዲስ ዘመን፡- ከደንበኛ ቁጥር ጀምሮ የባንኮች መረጃ እናንተ ጋር መኖር አለበት:: ለእዚህ ደግሞ ቴክኖሎጂን መጠቀም የግድ ነው:: ምን ያህል ቴክኖሎጂን እየተጠቀማችሁ ነው?

አቶ መርጊያ፡- ፈንዱ በተቋቋመበት ሕግ በቀጥታ ከባንኮች መረጃ የመሰብሰብ ሥልጣን ተሰጥቶታል:: መረጃው ደግሞ የሚሰበሰበው እጅ በእጅ ከሆነ፤ ሊሆን አይችልም:: በተጨማሪ ክፍያው ራሱ ሲፈፀም ወዲያው ገንዘባቸው መመለስ አለበት:: እናም እጅ በእጅ ገንዘብ መክፈል አዳጋች ነው:: ባንኩ ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ በ90 ቀን ውስጥ እንከፍላለን:: ይህንን ካላደረግን ሕዝቡ በእኛ ላይ እምነት ሊኖረው አይችልም:: ቴክኖሎጂው ያስፈልጋል:: ከተቋቋምን ገና ሁለት ዓመታችን ነው:: አስፈላጊው ቴክኖሎጂ እንዲኖረን እየሠራን ነው::

የምናቋቁመው ቴክኖሎጂ ከሌሎች ሀገሮች ልምድ በመውሰድ፤ የሚያስፈልገውን መረጃ ከባንኮች እና ከማይክሮ ፋይናንሶች የሚሰበስብልን መሆን አለበት:: ክፍያ ስንከፍል ለዚያም የሚያስፈልገንን ሥርዓት የሚዘረጋልንን ቴክኖሎጂ ለመገንባት ጥረት እያደረግን ነው:: በዚህ ላይ የዓለም ባንክም ለማገዝ ቃል ገብቶልናል:: ስለዚህ ከቴክኖሎጂ አንፃር እየሠራን ነው:: ገንዘብ ማሰባሰቡ ጥሩ እየሔደ ነው:: በሌላ በኩል ልዩ ትኩረት የምንሰጥበት የቴክኖሎጂው ጉዳይ ነው:: በዚህ ላይ በቂ ልምድ አለመኖሩ አንደኛው ፈተና ሊሆን ይችላል::

በሀገር ደረጃ የተቋቋምነው እንደ አዲስ ነው፤ ስለዚህ ከውጭ ከሌሎች ሀገሮች ልምድ መቅሰም አለብን:: የተደራጀ ሥርዓት (ሲስተም) የሚያስፈልገው በምን መልኩ ነው? የሚለውን የተለያዩ ሀገሮችን እያየን ነው:: ሮጠን ቴክኖሎጂውን በማቋቋም ነገ የምንፈልገውን የማይሠራ እንዳይሆን በደንብ የተጠና እና የተፈተሸ መሆን ስላለበት ረዥም ጊዜ ወስዶብናል:: በቀጣይም ረዥም ጊዜ ያስፈልገዋል:: ምክንያቱም ሲስተሙ በቀላሉ የሚሠራ ጉዳይ አይደለም:: ከ86 አባል ባንኮች እና ማይክሮ ፋይናንሶች መረጃ የሚሰበስብ እና የሚያጠናቅር ሥርዓት (ሲስተም) መገንባት ቀላል አይደለም::

አዲስ ዘመን፡- ከዕቅዳችሁ አንፃር ምን ያህል እየሠራችሁ ነው? እያጋጠማችሁ ያለ ችግር ካለም ይግለፁልን?

አቶ መርጊያ፡- መሥራት የማንችለውን አናቅድም:: መሥራት የምንችለውን ፈትሸን እናቅዳለን:: በዕቅዳችን መሠረት ከ90 በመቶ በላይ እየሄድን ነው:: ለምሳሌ በዕቅዳችን መሠረት መሰብሰብ የምንችለውን ገንዘብ አቅደናል:: በዚያ በኩል አፈፃፀማችን ጥሩ ነው:: ነገር ግን ፈተና የሆኑ ነገሮች አሉ:: አንደኛው የልምድ ማነስ ፈተና ነው:: በኢትዮጵያ ይህን የሚያህል ኢንሹራንስ የለም:: ልምድ እያካበትን ያለ ነው ከሌሎች ሀገሮች በማየት እና በማንበብ ነው::

የምንሠራው የሰው ኃይልንም ራሳችን አሰልጥነን ነው:: በዚህ ላይ ልምድ የለንም:: አንድ ማይክሮ ፋይናንስ ሲወድቅ ከየት ተነስቶ የት ይደርሳል? በምን ያህል ፍጥነት ክፍያ ላይ መደረስ አለበት? በሚለው ላይ ራሱ ልምድ የለም:: ኬንያ እና ዑጋንዳ ግን ባንክ ወድቆባቸው አይተውታል:: በዚህ ላይ የተፈተሸ ልምድ አላቸው:: አስቀድሞ ዝግጅት ካልተደረገ፤ ችግሩ ሲከሰት የሚያዝ የሚጨበጠው ይጠፋል:: ስለዚህ በተግባር የተፈተሸ ልምድ የለንም:: አሁን እያየን እየሠራን ነው::

አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ የውጭ ባንኮች ሲመጡ አሠራራችሁ የሚሆነው እንዴት ነው? ምን ያህል ተዘጋጅታችኋል?

አቶ መርጊያ፡- አዳዲስ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የሕግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል:: ከዚያ አኳያ ፈንዱ የአሠራር ለውጥ አያደርግም:: ባንኮቹ ከሕዝቡ ተቀማጭ ገንዘብ ይሰበስባሉ ብለን እናስባለን:: ስለዚህ በሀገር ውስጥ ባንኮች የሚተገብሩት ሕጎች እነርሱ ላይም ይተገበራሉ:: ለምሳሌ የሚሰበሰበው ገንዘብ ከእነርሱም የሚሰበሰብ ይሆናል:: ስለዚህ እነርሱ ሲመጡ የተለየ ነገር የለንም:: ምክንያቱም ማንኛውም ከሕዝቡ ተቀማጭ የሚሰበስብ አካል ገንዘብ መክፈል አለበት:: በዋናነት ሲመጡ የፈንዱ አባል መሆን አለባቸው::

ከብሔራዊ ባንኩ ፈቃድ እንደወሰዱ ቀጥታ አባል እንዲሆኑ እና በየጊዜው እንደ ሀገር ውስጥ ባንኮች ሁሉ የውጭዎቹም መክፈል ያለባቸውን መክፈል ይኖርባቸዋል:: ስለዚህ የተለየ ነገር የለንም:: ሲመጡ ከመጡበት ሀገር ጋር ግንኙነት መኖር አለበት:: እርሱ ወደፊት የሚሆን ነው::

አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የሚሉት ነገር ካለ ዕድሉን ልስጥዎ!

አቶ መርጊያ፡- አሁን ባለው ሁኔታ ፈንዱ በባንኮችም ሆነ በማይክሮ ፋይናንሶች ቁጠባ ላስቀመጡ ሰዎች እስከ 100ሺህ ብር ኢንሹራንስ ይሰጣል:: ሕዝቡ ያለ ስጋት በፈለገው ባንክ እና ማይክሮ ፋይናንስ ቁጠባውን ያስቀምጣል:: ይህ ሕዝቡ በባንኮች እና በማይክሮ ፋይናንሶች ላይ መተማመን እንዲሰማው ነው:: የተለመደው ለመኪና ኢንሹራንስ የሚከፍለው ራሱ የመኪናው ባለቤት ነው:: በዚህኛው ኢንሹራንስ ግን የሚከፍሉት ባንኮች እና ማይክሮ ፋይናንሶች ናቸው:: ዜጎች ቁጠባቸው ኢንሹራንስ ያለው መሆኑን በማወቅ ነገም ያለ አንዳች ስጋት ቁጠባቸውን እንዲቆጥቡ መልዕክት አስተላልፋለሁ::

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ::

አቶ መርጊያ፡- እኔም አመሰግናለሁ::

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You