የእሴቶች መላላት ያስከተለው ስጋት

የሰው ልጅ እምነት፣ ፍቅር እና ሰላም የሕይወት መርሁ ማድረግ እንዳለበት ተደጋግሞ ይገለፃል። ቢቻል ትህትና፣ በጎነት እና ቸርነት ቢታከል መልካም ስለመሆኑም ይነገራል። ሆኖም የሚታየው በተቃርኖ የተሞላ ስለመሆኑ ብዙዎች አስተያየት ይሠጣሉ። ራስወዳድነት እና ስግብግብነት፤ ሰዎችን መጥላት አልፎ ተርፎ መግፋት እና ሕፃናትን እስከ መድፈር የደረሰ የሞራል ዝቅጠት ይስተዋላል የሚል ተደጋጋሚ ሃሳብ ይሰነዘራል። ሃሳቡን በተመለከተ ምን ይላሉ? ለእዚህ መነሻው ምንድን ነው? የሚያስከትለው ጉዳት ምን ያህል ነው? ወደ ፊት ምን ይሆናል? ስንል የሥነልቦና ባለሞያዎችን አነጋግረናል።

በአማኑኤል ሆስፒታል ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት ቤተልሔም ለማ እንደሚናገሩት፤ ፍቅር እና ሰላም አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። እነዚህ እየቀነሱ የመጡባቸው ምክንያቶች ለመለየት ሰፋፊ ጥናቶች ያስፈልጋሉ። በቅድሚያ ግን የአዕምሮ ክፍሎችን በደንብ ማወቅ ይገባል። በግለሰብ ደረጃ ሰዎች ለምን ሞራላዊ እሴቶቻቸውን እያጡ መጡ? የሚለው ከሥነልቦና ሳይንስ አንፃር ሲታይ ሳይኮዳይናሚክ የሚባል የሥነልቦና ዘውግ ላይ ማተኮር የግድ ነው።

ዘውጉ ስለሰው ልጅ አስተሳሰብ፣ ባህሪ እና ሥነልቦና ሰፋ አድርጎ በመተንተን ሶስት የዓዕምሮ ክፍሎች እንዳሉ ያነሳል። ቅድሚያ የሚቀመጠው ሊድ ነው። ይህ በዋናነት ሰዎች ከእንስሳት ጋር የሚጋሩዋቸውን ደመነፍሳዊ ስሜቶች እና ፍላጎቶች የሚመነጩበት የዓዕምሮ ክፍል ነው። ይህ አካላዊ እና ስሜታዊ ደስታን በመሻት የሚመራ የዓዕምሮ ክፍል ሲሆን፤ በምንም ዓይነት መልኩ ፍላጎቱን ከማሳካት ወደ ኋላ የማይል ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ተፈጥሯዊ የሆኑ ለምሳሌ ፆታዊ እና መሠረታዊ ፍላጎቶችን፣ ፍቅርን፣ ጥላቻን እና ከሰዎች ጋር ግንኙነት የማድረግ ፍላጎትን የሚይዝ መሆኑንም አመላክተዋል። የሁለተኛውን እና ኢጎ የሚባለው የዓዕምሮ ክፍል ሥራን በተመለከተም ሲያስረዱ፤ ደመነፍሳዊ የዓዕምሮ ክፍልን በመቆጣጠር ከማሕበረሰባዊ የሞራል እሴቶች ጋር መጓዝ እንዲቻል የሚያደርግ ነው ይላሉ። በዋነኛነት ምክንያታዊነትን እና እውነታን በማገናዘብ ስሜትን የሚይዝ የዓዕምሮ ክፍል ሲሆን፤ ከገሃዱ ዓለም እውነታ ጋራ በተሰናሰነ መልኩ የሚያስኬድ ሚዛን የሚያስጠብቅ መሆኑንም አመላክተዋል።

የመጨረሻው እና ሶስተኛው የዓዕምሮ ክፍልን በተመለከተም የገለፁት የሥነልቦና ባለሞያዋ ቤተልሔም፤ ሱፐር ኢጎ መሆኑን በመጠቆም በዋነኝነት የሚመራው በማሕበራዊ ሞራላዊ እሴት ላይ መሆኑን ያስረዳሉ። ይህ ክፍል በወላጆች፣ በሚኖርበት ማሕበረሰብ ዘንድ የሚዳብረው የሥነምግባር ሕገ ደንብን አጠቃሎ የሚይዝ ነው። ይህ የዓዕምሮ ክፍል ከሌሎች ክፍሎች በተለየ ሕገ ደንቦችን እንዲጠብቁ ያስገድዳል ሲሉ አብራርተዋል።

ሁለት የተራራቁ የዓዕምሮ ክፍሎችን በተመለከተ ሲያስረዱ፤ ሰዎች ከእንስሳት ጋር አንድ የሚያደርጋቸውን እንስሳዊ ስሜትን እና በተቃራኒው በኩል ያለውን ሱፐር ኢጎ የሚባለው ማሕበራዊ እሴቶችን የያዘው መካከል ግጭት ይፈጠራል። የግል ፍላጎት ሲጎትት በተቃራኒው የማሕበራዊ ፍላጎት እሴትም ይስባል። መሃል ላይ ያለው ኢጎ ከነባራዊው እውነታ ጋራ እያስታረቀ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ሁለቱንም ሚዛናቸውን አስጠብቀው ተጣጥመው እንዲሔዱ ጥሩ ማሕበራዊ ግንኙነቶች እንዲኖሩ ያደርጋል ብለዋል።

እንደየሥነልቦና ባለሞያ ቤተልሔም ገለፃ፤ ኢጎ በደንብ ካልጎለበተ፤ ከቁጥጥር ውጪ ሲሆን፤ ፅንፍ የያዘ የእንስሳዊ ፍላጎት ትግበራ ይካሄዳል። ወይም በሌላ በኩል ግላዊ አቋም ሳይኖር በጣም ማሕበረሰብ ተኮር መሆን እና ማሕበረሰባዊ ፍላጎት ላይ ብቻ የማተኮር ዝንባሌ ይፈጠራል። አጣጥሞ አለማስኬድ እና ከኢጎ ቁጥጥር ውጪ መሆን ለተለያዩ የሥነልቦና ቀውሶች ያጋልጣል። ስለዚህ ዋናው ጉዳይ አስታራቂው የዓዕምሮ ክፍል በተዛባ ቁጥር ብዙ ዓይነት የሥነልቦና ችግሮች ያጋጥማሉ።

‹‹ ኢጎ የሰዎችን ዓዕምሮ የሚመራ ነው። ኢጎ ደካማ ሲሆን፤ የመጥፎ አስተሳሰብ ተጋላጭነት እና የስብዕና ችግር ሌሎችም ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡›› ያሉት የሥነልቦና ባለሞያ ቤተልሔም፤ በተቃራኒው ኢጎ ጠንካራ ሲሆን፤ የዳበረ ምክንያታዊ የመሆን ዕድል ይጨምራል ብለዋል። ለምሳሌ በአብዛኛው የኢጎ ችግር ሰለባ የሆኑ ሰዎች በጣም አሰቃቂ በሆነ መንገድ ሰውን መግደል፤ ሕፃናትን አስገድዶ መድፈር ለመሳሰሉት ጉዳዮች ተጋላጭ ይሆናሉ። ሌሎችም ብዙ ጉዳዮች አሉ። ይህ ከሥነልቦና ዘውግ አንፃር ሳይኮዳይናሚክ አንዲት ቅርንጫፍ ነው። ሰዎች ለምን ይህንን ያደርጋሉ? ለሚለው ራሱ ሌሎች ብዙ ዘውጎች አሉ ብለዋል።

በአብዛኛው ከላይ ከተጠቀሰው የሳይኮዳይናሚክ እሳቤዎች አንፃር ሲታይ፤ ሊድ ብቻ ሲመራ የራስ ፍላጎት ላይ ብቻ ያተኮረ ስለሚሆን፤ እነዚህ የሞራል እሴቶች እና መልካም ሥነምግባር የሚባሉት ነገሮች እየላሉ እንዲመጡ ያደርጋል። እውነታን መሠረት ባደረገ መልኩ ምክንያታዊ ሆኖ ነገሮችን ማገናዘብ አለመቻል በመጨረሻም ከባድ ችግር ያስከትላል። በተደጋጋሚ ወንጀሎች ከተፈፀሙ በኋላ ‹‹ስሜቴ ገፋፍቶኝ በደመነፍስ›› የሚባሉ ምላሾች የሚሰጡት፤ የዚህ ውጤት በመሆናቸው ነው ብለዋል።

እንደየሥነልቦና ባለሞያ ቤተልሔም ገለፃ፤ የኢትዮጵያውያን ባሕላቸው፣ አኗኗራቸው እና ሥነምግባራቸው በየዕለቱ ለምን እየቀነሰ መጣ? እንደባሕል ኢትዮጵያውያን ሲታወቁበት የኖሩበትን ሰው ወዳድነት እና ሃይማኖታዊነት ለምን ቀነሰ? ለምን ጭካኔ በዛ? ሲባል ከላይ የተገለፀው እንዳለ ሆኖ፤ ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች አሉ። አሁን ላይ ስኬት እና ዘመናዊነት የሚለካበት መንገድ ተቀይሯል። አንደኛው ዓለም ወደ አንድ መንደር እየተቀየረች መሆኑ፤ በጣም በፍጥነት እየተቀያየረ ያለ የአኗኗር ሥርዓት፤ ዘመን አመጣሽ እሳቤዎች እና የባሕል ግጭት መንሰራፋት ከምክንያቶቹ መካከል ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።

በዚህ ዘመን ቴክኖሎጂው በሁሉም እጅ ውስጥ በመሆኑ፤ እያንዳንዱን ነገር ማግኘት የሚቻልበት ዕድል አለ። ቴክኖሎጂን መጠቀም መልካም ቢሆንም፤ በተቃራኒው የማይቀር አሉታዊ ተፅዕኖዎች እንዳሉበት ያመላከቱት የሥነልቦና ባለሞያዋ፤ በፊት የነበረ ባሕላዊ እሴቶች መተሳሰብ አብሮነት እንዲሁም ኢትዮጵያ ስትታሰብ የሚመጣው ምስል እየተሸረሸረ እና እየላላ እንዲመጣ ቴክኖሎጂው ዋነኛውን ሚና ይጫወታል የሚል እምነት እንዳላቸው አብራርተዋል።

አሁን ስኬት የሚመዘነው ራስ ላይ ያተኮሩ ሥነልቦናዊ እሳቤዎች ላይ በመንጠልጠል እና ራስን በማስቀደም ብቻ ሆኗል። በየትኛውም ቦታ እና ሁኔታ ከሰዎች ጉዳት እና ጥቅም ይልቅ የራስ ጥቅም ላይ ብቻ ማተኮር ይስተዋላል። ሌሎችም ብዙ የአስተሳሰብ ችግሮች እና ለውጦች እየመጡ መሆናቸውን አስታውሰው፤ ዓለምን ሰዎች የሚረዱበት ሁኔታ፤ ግንኙነትን የሚያዩበት መንገድ፣ ማሕበረሰባዊ መስተጋብርን የሚያስተናግዱበት አካሄድ እየተቀየረ መሆኑንም አብራርተዋል።

በሌላ መልኩ የሥነልቦና ባለሞያዋ ቤተልሔም የትምህርት ሥርዓቱ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችም በራሳቸው ተፅዕኖ የሚኖራቸው መሆኑን አስታውሰው፤ ዘመናዊ ማሕበረሰብ ወይም ግሎባላይዜሽን ጋር ተያይዞ የመጣ ግላዊነት የፈጠረው ተፅዕኖ የማሕበረሰብ እሳቤ፣ ሞራል እና ሥነምግባር የሚባሉ ነገሮች ቀስ በቀስ እየላሉ እንዲሔዱ ምክንያት መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ መምህርቷ እና የሥነልቦና አማካሪ እና ከሥነልቦና ጋር የተያያዙ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት የሚታወቁት ወይዘሮ ምሕረት አብርሃ በበኩላቸው፤ መልካም እሴቶች የመላላታቸው ሚስጢር ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ መነሻዎች አሉት። የሰው ልጅ ያለው የዓዕምሮ መዋቅር ከሌሎች እንስሳዎች በተሻለ መልኩ ከነገሮች ጋር የመላመድ አቅም አለው። እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ድረስ የተገነባበት ባሕሪው አብሮት የሚኖር ሲሆን፤ በኋላም በአኗኗር ሂደቱ ከነገሮች ጋር ተላምዶ በተወሰነ መልኩ ራሱን እያስተካከለ የሚሔድ ፍጥረት ነው።

‹‹በመለማመድ ሂደት ውስጥ የሚወስደው የሚመቸውን ወይም ጥሩውን ብቻ ሳይሆን መጥፎውንም የሚቀበል እና ለምዶት የሚፈፅም ፍጥረት ነው፡፡›› የሚሉት አማካሪዋ፤ ዘመናት በየአስር ዓመቱ ተከፋፍለው ሲታዩ፤ ብዙ የየአስር ዓመት ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ከሃያም ሆነ ከሰላሳ ዓመት በፊት የሰው ልጅ ማሕበራዊ ዳራው፤ በየሚደርስበት ዘመን እየተለያየ እየተቀያየረ የሚመጣ ነው። ከ60 ዓመታት በፊት የነበረ ማሕበራዊ ግንኙነት፣ የነበረው ቴክኖሎጂ፣ ግለሰባዊ አስተሳሰብ ከአሁኑ በእጅጉ የተለየ መሆኑን አብራርተዋል።

ግለሰባዊ አስተሳሰቡ ላይ ጥናት ሲደረግ ከኢኮኖሚያዊ፣ ከማሕበራዊ እና ከፖለቲካዊ ዘርፍ እና ከሌሎችም አንፃር ሲታይ፤ ከዛሬው በጣም የተለየ ነው። ለዚህ አንደኛው ምክንያት ተብሎ በአማካሪ ምሕረት የተገለፀው፤ እንደሥነልቦና ባለሞያ ቤተልሔም ሁሉ በአሁኑ ሰዓት በጣም በከበደ መልኩ የሰዎች አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ያለው ግሎባላይዜሽን ነው። እንደአማካሪዋ ገለፃ፤ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት በጣም እየጠነከረ ነው። ይህ ካደጉ አገሮች ይልቅ እንደኢትዮጵያ ባሉ ባላደጉ አገሮች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው። በጎ ገፅታው እንዳለ ሆኖ በተቃራኒው የሚፈጥረውም ጫና ከባድ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ቲክቶክ፣ ቲውተር፣ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ሌሎችም ማሕበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። ዓብይ ሚዲያዎች (ሜንስትሪም ሚዲያው) ራሱ የማሕበራዊ ሚዲያን መስሏል። ምክንያቱም እነርሱም ቢሆኑ የሰውን ልብ የሚገዙበት መንገድ አንደኛው ይኸው ነው ብለው ያስባሉ ብለዋል።

እንደአማካሪ ምሕረት ገለፃ፤ በሌላ በኩል ከ40 እና ከ50 ዓመት በፊት የነበረውን ማሕበራዊ አስተሳሰብ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች ጠብቆ ለመቆየት የሚያስችሉ ግብዓቶች አሉ? የሚለውም ሊታሰብበት ይገባል። እንደግለሰብ ጠቅልሎ ለመፈረጅ ቢያዳግትም ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፤ ማሕበራዊ ሚዲያው በአብዛኛው የሰውን ማሕበራዊ ሕይወት የሚያስተሳስር ሳይሆን ቁሳዊነትን የሚያበረታታ ነው።

ሰዎች በቅንጦት የተሞላ ሕይወት እንዲኖሩ የሚያነሳሳ እና ግለሰባዊነትን የሚያዳብር ሲሆን፤ ለምሳሌ ‹‹የዛሬ ምግቤ፣ የዛሬ ልብሴ፣ የዛሬ መኪናዬ፣ ዛሬ የምሔድበት ቦታ እያሉ የተቀናጡ ነገሮችን ያሳያሉ። ቁሳዊነት በትውልዱ የእጅ ስልክ ላይ ጨዋታ በሚመስል መልኩ በመቀመጡ ልጆች በአቋራጭ መክበር ላይ እንዲያተኩሩ ያበረታታል። በስክሪን እንዳየው መኖር ያልቻለ ወጣት በቅዠት ውስጥ ይገባል። ያንን ለማግኘት ለመስረቅም ሆነ ለማታለል በቀላሉ ይነሳሳል፡፡›› ሲሉ ራስወዳድነት እና ቁሳዊነት የሚጎለብትበትን ሁኔታ እና ትውልዱ ብልሹ እንዲሆን ቴክኖሎጂ እያስከተለ ያለውን ጣጣ አመላክተዋል።

በተመሳሳይ ቴክኖሎጂው የሰው አካል ፆታዊ ግንኙነት ላይም አንደመርኪያ መንገድ ብቻ እንደሆነ እንዲያስቡ እንደሚያበረታታ አስታውሰው፤ ዓላማ ያለው ፈጣሪ የፈጠረው ትውልድን የመተካት ሥርዓት እንደሆነ የመርሳት ሁኔታ አለ። በአጠቃላይ ቴክኖሎጂው ትናንት የነበረ እሴት እንዲሸረሸር፣ ማሕበራዊ ሕይወት እንዲላላ፤ ግለሰባዊነት እንዲዳብር፣ ሴታዊነት (ፌሚኒዝም) እንዲስፋፋ የዘመን አመጣሹ ቴክኖሎጂ በመንስኤነት የሚቀመጥ መሆኑን አክለው ገልፀዋል።

በተደጋጋሚ ይሔ ትውልድ ራስ ወዳድ ነው፤ ለሌሎች አያስብም ይባላል። ነገር ግን አሁን የደረሰውን ትውልድ ቀርፆ ያመጣው ማን ነው? ይህ የሆነው መቼ ነው? ትውልድ መካከል ክፍተት የተፈጠረው እንዴት ነው? የሚሉት ጥያቄዎች ሰፊ ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ናቸው ብለዋል።

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታወቀው እንደምን አደርክ? ብሎ ቆሞ ደህንነትን ሲጠይቅ ነው። ችግር አለ ሲባል በምንም ዓይነት ሁኔታ ለሌላው ሰው የሚደርስ መሆኑ ይታወቃል። ባለፉት የተወሰኑ ዓመታት ግን ይህ ላልቷል። አሁን ያለውን ወጣት ሰላምታ የከበደው፤ ማቀፍ እና መሳቅ ያዳገተው ነው። በእርግጥ ለዚህ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ሆኖም ዛሬ የሚነሱት ችግሮች እዚህ የደረሱት ትናንት ያልተሠራ ክፍተት በመኖሩ ነው። ትናንትና የዕምነት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና ወላጆች የመንግሥት እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገቢው መንገድ ያልሰሩት ክፍተት ስለነበረ ነው የሚሉት አማካሪዋ፤ ዛሬም ይህ ክፍተት ቀጥሏል የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ። በቀጣይ ምን ይሆናል የሚለው አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡

ባደጉት አገራት ቴክኖሎጂው ጠንካራ የሥራ ባሕል እና የመተሳሰብ እሴት እንዲኖር የሚያበረታታ ባለመሆኑ፤ አንዳንዶቹ ወደ ተዛባ አስተሳሰብ በመሔዳቸው ብዙ ጥናቶች እየተጠኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። አክለውም ኢትዮጵያም ከዓለም ውጭ እንዳልሆነች አስታውሰው፤ በቅርቡ ጥናት ባይደረግም በተለይም ቲክቶክ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥም በዕድሜ ለመከፋፈል እንኳ በሚያዳግት መልኩ ብዙ ሰው ሱሰኛ ሆኗል፤ ታክሲ ውስጥ፣ ባስ ውስጥ፣ በየሥራ ቦታው ሰዎች ጊዜያቸውን ለቲክቶክ ሰጥተዋል ብለዋል።

የሕግ አካላት ሳይቀሩ ከባድ ወንጀሎች እየተፈፀሙ ተገቢውን እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ችላ የማለት ሁኔታ መኖሩን አስታውሰው፤ የራሳቸውን አጋጣሚ ገልፀዋል። የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ አንድ ጉዳይ ገጥሟቸው ወደ ሕግ አካል ሲሔዱ፤ የተሰጣቸው መልስ እጅግ አስደንጋጭ እንደነበር አስታውሰዋል። ለእዚህ ምክንያት መሰላቸት ወይም ግራ መጋባት አለ ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡

ሆኖም ይህ ሁሉ ቢሆንም የአሁኑ ትወልድ ነገ ኢትዮጵያን የሚያስቀጥልበት ከቴክኖሎጂ እና ከአዳዲስ ከኢኖቬሽን ሥራዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች አሉት። አማካሪዋ መፍትሔ የሚሉትንም ሲጠቁሙ፤ ባለድርሻ አካላት ማሕበራዊ ተቋማት የዕምነት ተቋማት ትምህርት ቤቶች፣ የመንግሥት አካላት፣ የማሕበራዊ ዘርፍ መሪዎች ማለትም የሀገር ሽማግሌዎች እና ወላጆች እነዚህ ሁሉ ባለድርሻዎች መሥራት እንዳለባቸው ገልፀዋል።

አሁን አዕምሮ ውስጥ የማይታይ አደገኛ በሽታ እየተስፋፋ እና ቀስ በቀስ ሰዎችን እየገደለ በመሆኑ፤ በኮቪድ ጊዜ እንደነበረው ዓይነት ንቅናቄ ያስፈልጋል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመው፤ ያለበለዚያ የሚሆነው ያስፈራል ብለዋል።

ባደጉት አገራት ሆቴሎች ዋይፋይ እየጠፋ የሚፈቀደው ሰዎች ከሰዎች ጋር ብቻ እንዲነጋገሩ ነው የሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ምክንያቱም የደረሱበት የስልጣኔ ጥግ ያመጣባቸው መዘዝ ብዙ መሆኑን ተረድተዋል ያሉት አማካሪዋ፤ ድህነት የወንጀሎች ሁሉ አባት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ድህነት ላይ የተዛባ አስተሳሰብ የሚጭን ቴክኖሎጂ ተጨምሮ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መናጋቱ ታክሎበት፤ ወንጀሎች የማይስፋፉበት ምንም ምክንያት የለም ሲሉ ተናግረዋል።

መልካም እሴቶች እንዲጠነክሩ፤ ባለድርሻ አካላት እና የሥነልቦና ባለሞያዎች በሚችሉት መልኩ ትውልድን የመቅረፅ ሥራ መሠራት አለባቸው ሲሉ ለሞያ አጋሮቻቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።

እንደአማካሪዋ ምህረት ሁሉ በሌላ በኩል የሥነ ልቦና ባለሞያዋ ቤተልሔምም ‹‹ከሚሰማው እና ከሚታየው አንፃር አስጊ ሁኔታ ላይ ነን፡፡›› ካሉ በኋላ፤ ማሕበራዊ እሳቤዎችን የትምህርት ፖሊሲው ምን ያህል ቦታ ሰጥቷቸዋል? የሚለው ጉዳይ ትልቅ መሠረታዊ ነገር መሆኑን ጠቁመዋል።

ከትምህርት ፖሊሲው በተጨማሪ በየዕለቱ የሚሰሙ ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ዘግናኛ ነገሮች እንደሀገር የሚመለከታቸው ተቋማት፣ የዘርፉ ባለሞያዎች እና ማሕበረሰቡ በጉዳዮች ላይ አተኩሮ መወያየት እና በጥናት ላይ የተመሠረተ ሥራ መሠራት እንዳለበት አብራርተዋል። በፍጥነት ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶ ማሕበረሰቡን በማወያየት ወደ ሥራ ካልተገባ ወደ ፊት በጣም የሚያሰጋ ነው ብለዋል፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You