ዓይጥ በበላ ዳዋ ተመታ፤ የአሁኑ ዘመን የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ውጤት

የሆድ ነገር ሆድ እንደሚቆርጠው ሁሉ፤ የትምህርት ነገርም ያው ነው። ሆድ ባይቆርጥ እንኳን እራስ ያዞራል፤ ህሊናን ያጦዛል። በተለይ ወደ እኛ ሀገር ሲመጣ በመንግሥታት መለዋወጥ ቁጥር ስር ነቀላዊ ለውጥ የሚካሄድበት የትምህርቱ ዘርፍ አየር ለመሳብ እንኳን ፋታ ሳይሰጥ ትንፋሽ እስኪያጥር ድረስ ያስለፈልፋል፤ ቀለም እስኪያጥር ያስሞነጫጭራል። የሚያሳዝነው፤ ያ ሁሉ ሆኖም ጉዳዩ ሁሌም እዛው መሆኑ ነው።

ማንኛውም ጊዜ የመነጋገሪያ ርእስ እንደሚኖረው ሁሉ፤ አሁንም በትምህርቱ ዘርፍ የሰሞኑ ሕዝባዊ፣ በተለይም በትምህርት ባለ ድርሻ አካላት ዘንድ የጋራ አጀንዳ ሆኖ ሲያነጋግር እየተሰማ ያለው የ2016ቱ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ነው።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል ውጤት በማስመልከት ሰኞ (ጳጉሜ 4 ቀን 2017 ዓ•ም) እለት (‹‹በሰላም እንዳናከብርበት ምነው በዓመት በዓሉ ዋዜማ?›› በማለት ቅሬታቸውን ያሰሙ ነበሩ) ይፋ አድርገዋል።

በዚሁ መግለጫም፣ የዘንድሮውን 12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ከወሰዱ 674ሺህ 823 ተፈታኞች ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ተማሪዎች 5.4 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ሚኒስትሩ አስታወቁ። 1ሺህ 363 ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ አላሳለፉም። ይህ ማለት 637ሺህ 823 ያህል ተማሪዎች ወድቀዋል ማለት ነው። አጠቃላይ ውጤቱ ይህንን መምሰሉን ይዘን የተፈታኞችን ዳራ እንፈትሽ።

አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ (ወይም፣ አሳማ በበላ ጉፍጡራን በዱላ) እንዲሉ የአሁኑ ዘመን ተማሪዎች የተሰጣቸውን ተቀበሉ እንጂ ያልተሰጣቸውን ከየትም አላመጡትም። ኩረጃ ባሕል እንዲሆን በተዘረጋው ሥርዓት መሠረት ወደ ኩረጃ ገቡ፤ ማጥናት የፋራ እንዲሆን በተዘረጋው መስመር መሠረት አለማጥናት አራዳ ሆኖ ያገኙት ዘንድ ሥርዓቱ ‹‹በርቱ አላቸው (ይህ ‹‹ነገር ለማሞቅ›› ታስቦ ሳይሆን እምናውቀው ነው)። አስተማሪህን (የቀለም አባትህን) አክብር የሚለው ‹‹የአድሀሪያን ነው››፤ ‹‹ዲሞክራሲያዊ አይደለም›› ወዘተ ተብለው (በግምገማው መሰረት) አስተማሪን መናቅ፣ ማዋረድ (መምህራን በቴሌቪዥን እስኪያለቅሱ ድረስ) ‹‹ወግ ነው›› ተባሉ፤ ወግ አድርገውት ዘለቁ። ደሞ የምን ከፍተኛ ውጤት፣ ከ700 ለሴቶች 101፤ ለወንዶች ከ300 መቶ በላይ ማለፊያ ሆኖ በተወሰነው መሰረት ወደ የዩኒቨርሲቲዎቻቸው ተሰማሩ። የምን አራት ዓመት፣ ሶስት መቼ አንሶት ተባሉና በሶስተኛቸው ውልቅ አሉ። ታዲያ ዛሬ ወደቁ፣ ተንከባለሉ ወዘተርፈ ማለት የምን አትርሱኝ ነው? የነበረው እጅ እግር የሌለው የትምህርት ሥርዓት ባጠፋው (የአሁኖቹ ተፈታኞችና ወዳቂዎች የዚያ ፖሊሲ ልጆች መሆናቸውን ልብ ይሏል) ተወቃሾቹ እነዚህ ልጆች ሊሆኑ ይገባልን?? ‹‹አሳማ በበላ ጉፍጡራን በዱላ›› አይሆንምን?›› ‹‹አይሆንም›› የሚል ካለ ‹‹ሲተረጉሙ ይደርግሙ›› እንዲሉ ነውና ችግሩ የወደቁት ጋ ብቻ ሳይሆን ሰፊ ነው ማለት ይሆናል።

እንደ የመጀመሪያው ርእሰ መምህርና የትምህርት ሊቁ ዶክተር ልዑልሰገድ ዓለማየሁ ብያኔ ቢሆን ኖሮ 5.4 በመቶ ተማሪዎች ሲያልፉ፤ የወደቁቱ (637ሺህ 823) መምህራን ናቸው። በመሆኑም፣ እሳቸው ጋ ‹‹ዓይጥ በበላ ዳዋ ተመታ›› ይሉ ፈሊጥ አይሰራም።

ይሄንን ያህል በመቶዎቹ (…%) የ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች የማንበብም ሆነ የመጻፍ ክሂል የላቸውም ብሎ ማሳቀል ‹‹ከየት ያምጡት?›› የሚል ጥያቄን እንዳያስነሳ፤ ወይም፣ ‹‹ዓይጥ በበላ ዳዋ ተመታ›› ዓይነት አስተያየቶችን እንዳይጋብዝ ተገቢውን ጥንቃቄና አስፈላጊውን ዝግጅት ከወዲሁ ማድረግ ያስፈልጋል። አሁን በዚሁ ዘርፍ እየተካሄደ ያለው ሪፎርምም ይህንን ከስሩ ሊያሰምርበት ይገባል። (እዚህ ላይ፣ ከራሱ፣ ከትምህርት ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ተማሪዎች የቋንቋ ትምህርት እየተማሩ የንባብም ሆነ የጽሑፍ ክሂል የማይኖራቸው ከሆኑ ሲሰጥ የነበረው የቋንቋ ትምህርት አላማ-ተኮር (Goal oriented) አይደለም። ይህንን በየትምህርት ዓይነቶቹ እየወሰዱ፣ እየመነዘሩ ማየት ይቻላል።)

የደቡቧ ጀግና ሲፌኔ ተክሉ የዘንድሮውን ፈተና 575/600 በማምጣት አጃኢብ ማሰኘቷን ይዘን፤ የቃሊቲ ማረሚያ ማዕከል የመጀመሪያ ደረጃና አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሳምሶን ወንድሜነህ ‹‹በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በቃሊቲ ማረሚያ ማዕከል በመደበኛ የትምህርት መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከነበሩ 21 የተፈጥሮ ሳይንስ የሕግ ታራሚ ተማሪዎች መካከል ሰባቱ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያስችለውን ውጤት›› አመጡ በማለት የገለፁት ተስፋ ሰጪ ዜና እንዳለ ሆኖ፤ ‹‹ከ1ሺህ 300 በላይ ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ [ከዘንድሮ ማትሪክ ተፈታኞች] አላሳለፉም።›› ሲባል ምን ማለት ነው? ጉዳዩስ ከሞራል፣ ከህላዌነት፣ ከማንነት (ኢንስቲቲዩሽናል አይዴንቲቲ)፣ ሙያዊነት (ፕሮፌሽናሊዝም)፣ ከትምህርት ሳይኮሎጂ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከጊዜ ወዘተ አኳያ እንዴት ይታያል? ያነጋግራል፤ ያወያያል፤ ያመራምራል።

ዳዋ ‹‹በማያገባው ምክንያት ለምን ይደበደባል?›› በሚል ብሶቱ በማህበረሰቡ ዘንድ ፅድቅናን ባገኘ ተረትና ምሳሌ እንደተገለጸው ሁሉ፤ እኛም ባለችን አቅም መጣ፣ ወይም ተገኘ የተባለው የብሔራዊ ፈተናው ውጤት የልጆቹ ሳይሆን የሥርዓቱ ነው ማለት እንወዳለን። ይህ ማለት ግን ልጆቹን ነፃ ለማውጣት ታስቦ ሳይሆን የእነሱን ሌላ ጊዜ ለማየት ካለ ፍላጎት የመነጨ ነው።

ማንም እንደሚያውቀው፣ የፍትህ ጥያቄ የሆነው ‹‹አይጥ በበላ • • •››ም ይሁን ‹‹አሳማ በበላ ጉፍጡራን በዱላ›› በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። ‹‹ተረትና ምሳሌ›› ወይም ‹‹ምሳሌያዊ ንግግር›› ብቻ ተብሎ በውስጡ የተሸከመው ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ‹‹ወጊድ ይሁዳ›› ሊባል አይገባውም። ይልቁንም፣ የፍትህ ሥርዓት ሲበላሽ በተሻለ የፍትህ ሥርዓት መስመር ይይዛልና በአሁኑ ሪፎርም እሱ ላይ ማተኮሩ ሁላችንንም አትራፊ ያደርጋል።

ያለፈው የትምህርት ፖሊሲ፣ የአሁኑ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ ጠቅለል አድርገው ‹‹ሆን ተብሎ በትምህርት ላይ የተሰራ አሻጥር›› ይበሉት እንጂ ሲዘረዘር ምን ምን ማለት እንደ ሆነ በርካታ ማስረጃዎችን እየደረደርን መመልከት ይቻለናል። ያገር ሰው ነገር አልጥም ሲለው፤ ፍርድ ሲዛባ፤ ፍትህ ሲጓደል ሲያይ ‹‹ዓይጥ በበላ ዳዋ ተመታ›› እንደሚለው፣ ምን ያህል የግርምቢጥ የሆኑ ጉዳዮች በ‹‹አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ›› ውስጥ ተሰግስገው እንደነበር መመልከት ይቻላልና በንፁሃን ላይ በትራችንን አናንሳ።

‹‹በአንድ መምህር ሁሉንም›› ዓይነት (Self-con­tend ይባል የነበረው) የመማር-ማስተማር ሥነ ዘዴ አንዱና የመጀመሪያው የትምህርት ሥርዓቱ ውድቀት መነሻ ሲሆን፤ ይህም ከአንድ እስከ አራተኛ ክፍሎች፣ ሁሉንም ዓይነት የትምህርት ዓይነቶች አንድ አስተማሪ ብቻ እንዲያስተምር ተደርጎ የነበረበት ሥርዓት ነበር። በቃ፣ በዚህ ሥርዓት (የመማር-ማስተማር ሥነ ዘዴ መሆኑ ነው) መሠረት ሥዕል ነሽ የለ፣ እንግሊዝኛ፣ ሂሳብ … ሁሉንም የሚያስተምረው አንድ አስተማሪ ብቻ ነው። እዚህ ላይ አንድ የሚገርም ጉዳይ ቢኖር መምህር ‹‹ሀ›› ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያስተማረውና መምህር ‹‹ለ›› ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያስተማረው፤ ሁለቱም ለአንድ ብሔራዊ ፈተና እኩል መቀመጣቸው ነው።

እዚህም ላይ በመምህራን መፍረድ እንደማይቻል መገንዘብ ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም በወቅቱ ‹‹ኧረ በሕግ፣ ኧረ ይሄ ነገር አያስኬድም፤ ኋላ ልጆቹን ይጎዳል …›› በማለት ሲቃወሙ የነበሩ መምህራን ምን ምን ዓይነት ችግሮች ሲደርሱባቸው እንደነበር ይታወቃልና ነው። (የዛሬዎቹም ይሁኑ የሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወላጆች በዚሁ የመማር-ማስተማር ሥርዓት ውስጥ ማለፋቸውን ያስታውሷል።)

እንደው ነገሩን እያነሣን እንየው ከተባለ እኮ ‹‹ተማሪዎች ቢያንስ ሦስት ቋንቋዎችን እንዲማሩ ይደረጋል›› የተባለው በዛ ‹‹አዲሱ …›› በተባለው የትምህርት ፖሊሲ ሳይሆን፤ በዚህኛው፣ ሪፎርም እያደረገ ባለውና ‹‹ለ28 ዓመታት ሲተገበር የቆየውን የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲን የሚተካና አዲስ የመምህራንን የሙያ ደረጃን፣ የተማሪዎችን የክፍል ዕርከኖችን፣ በሥርዓተ ትምህርት የሚካተቱ ቋንቋዎችን፣ እንዲሁም በርካታ የትምህርት ሂደቶችንና አሰራሮችን የሚቀይር ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀደቀ።›› ከተባለ ከየካቲት 2015 ዓ.ም ወዲህ ባለው ሪፎርም ነው። ምናልባት በዛኛው የብሔር ቋንቋዎች ስማቸው ከፍ ብሎ ይጠራ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ወፍ የለም … ወፍ።

ከናካቴው ተሰርዞ የነበረውም ‹‹እንግሊዝኛ ግን ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንደ ትምህርት ዓይነት ይሰጥና እንደ ማስተማሪያ ቋንቋ ደግሞ በአስገዳጅነት ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ይሰጣል።›› የተባለውም በዚህኛው ነውና በዛኛውማ የቋንቋ ነገር መላቅጡን አጥቶ ነበር ማለት ይቻላል። የሚገርመው ግን ‹‹በእንግሊዝኛ አንድ መስመር እንኳን መጻፍ የማይችሉ ምሩቃን …›› ማለታችን ነውና ጉዳዩ ‹‹አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ›› ሆኖ የወደቅነው እኛ እንዳንሆን ያሰጋል።

‹‹የመምህራን የትምህርት ዝግጁነትና ደረጃዎች አንደኛው ሲሆን፣ ከአንደኛ ደረጃ ቀደም ላሉና ዕድሜያቸው አምስትና ስድስት ዓመት የሆኑትን የቅድመ-አንደኛ የትምህርት ደረጃ ተማሪዎች ለማስተማር አነስተኛው የትምህርት ደረጃ ‘ሰርተፊኬት’ እንዲሆን›› የተወሰነው በዚህ፣ ከላይ በጠቀስነው ሰነድ አማካኝነት መሆኑን ስንመለከት በዛኛው የነበረውን መገመት አይቸግርምና ምን ያህል በትምህርት እንደ ተቀለደ ተገቢ የሆነ ማሳያ ነው።

መምህራንን በተመለከተ የማህበራቸው ተወካይ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ በነበረው የትምህርት ፖሊሲ ሙሉ ለሙሉ ደረጃውን አሟልቶ የሚያስተምር መምህር እንደሌለ›› መናገራቸው ሲታሰብ ዛሬ ‹‹ወደቁ›› የሚባሉት ተማሪዎች መውደቃቸው ሳይሆን ሊገርም የሚገባው ቢያልፉ ነበርና ‹‹ይሄንን ያህሉ ወድቀው፤ ይህንን ያህሎቹ ብቻ አለፉ›› በማለት ልንዘባበትባቸው አይገባም – መች አስተማርናቸውና።

ድሮ ድሮ ኢትዮጵያ ከራሷም አልፋ ለሌሎች፣ እህት ሀገራት ትተርፍ እንደ ነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ታሪክ ዘግቦት (ለምሳሌ፣ አዲስ ዘመን፣ ነሐሴ 1 ቀን 1951 ዓ•ም ‹‹የመምህራን ስብሰባ በዋሽንግተን›› በሚል ርእስ ለንባብ እንዳበቃው) እንደምንመለከተው የኢትዮጵያ መምህራን በተወካዮቻቸው አማካኝነት አሜሪካ (ዋሽንግተን) ድረስ በመሄድ የዓለም መምህራን ኮንፌዴራሽዮን ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ በመገኘት ከአቻዎቻቸው ጋር ስለ ዓለም (በተለይም ስለ አፍሪካ) የትምህርት ይዞታ ይወያዩ ነበር፤ የኢትዮጵያም አስተዋፅኦና ተሳትፎ ቀላል አልነበረም። የሀገራችን በርካታ ምሁራን (በተለይ በ1960ዎቹና 70ዎቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲካሄዱ የነበሩት ጥናቶች) ጥናታዊ የትኩረት አቅጣጫም የትምህርት ሁኔታ በአፍሪካ ምን መሆን ያለበት መሆኑ ላይ የሚያጠነጥን እንደ ነበር መረጃዎች (ለምሳሌ፣ በሁለት ቋንቋዎች ይዘጋጅ የነበረው የዩኒቨርሲቲው ‹‹ውይይት›› መጽሔት) ያመለክታሉ።

ፕሮፌሰር መስፍን በመጨረሻው መጽሐፋቸው (ዛሬም እንደ ትናንት?፣ ነሐሴ 2012 ዓ•ም) ክፍል አስራ ሦስት ስር ‹‹ትምህርት›› በሚለው ርእሳቸው ስር ‹‹የእኛ ባሕላዊ የትምህርት ዘዴ በጣም የሚያስደንቅና በፍጥነት እድገትን የሚያስከትል ነው›› (ገጽ 132) ቢሉም፤ ከባሕሉ ያፈነገጠ፤ ከባህር የወጣ አሳ ከሆንን ሰነባበትን።

የእጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› እንደሚዘረዝረው ከሆነም የኢትዮጵያ ትምህርት፤ በተለይም ከፍልስፍናው አኳያ ወደር የሌለው ሲሆን፤ በተለይ ‹‹የቅኔ ትምህርት ለኢትዮጵያ ትልቅ ሀብት ነው››። (ገጽ 74) እጓለ ይህንን ይበሉ እንጂ በአሁኑ ዘመን ይህንን የትምህርት (ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና) አባ ከና እያለው ያለ ማንም የለም። (ከዚህ መጽሐፍ በተለይ ‹‹ያሬድ ወይም ስለኢትዮጵያ ስልጣኔ›› በሚል ርእስ ስር በክፍሎች ተከፋፍሎ የቀረበውን ክፍል ይመልከቱ።) ወደ ተማሪው እንምጣ።

በመምህር ኪዳነ ማሪያም ጌታሁን በተዘጋጀውና ብዙም ልብ ባልተባለው ድንቅ ጥናት (ጥንታዊው የቆሎ ተማሪ፣ 3ኛ እትም፣ 1994 ዓ•ም) ላይ እንደ ሰፈረው፣ የጥንቱ የቆሎ ተማሪና የዛሬው (በተራዛሚው ጥንታዊውና ዘመናዊው) የተነፃፀሩ ሲሆን:-

የጥንት ተማሪ ቁርሱ ፀሎት፣ ያውም በቁመት፤

የዛሬ ተማሪ ቁርሱ ብስኩት፣ ያውም በወተት፤

(ዝርዝሩን ከመጽሐፉ መግቢያ ቀጥሎ ባለው ሶስተኛ ገጽ ይመልከቱ)

ይሁን እንጂ፣ ከላይኛው የደራሲው ሃሳብ የምንረዳው ሁሉ በደጅ፣ ሁሉ በእጅ በሆነበት በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የእውቀት ነገር ተሽሎ መገኘት ሲገባው በተቃራኒው ሆኖ መገኘቱን ነውና የአሁኑ ዘመን የትምህርት ሁኔታና ይዞታ በብዙ አጥኚዎች ተመዝኖ ጥያቄ ምልክት ስር ከወደቀ ቆይቷል። በርግጥ ይህ በእኛ ብቻ ሳይሆን የብዙ ሀገራት ችግር ነውና የጋራ ጥረትን የመሻቱም ጉዳይ ሳይጠቀስ ሊታለፍ የሚገባው አይደለም። በመሆኑም፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ በተቋሙ የተንሰራፋውን የጥናትና ምርምር ሥራዎች ምንተፋ (ፕላጂያሪዝም)ን ለማስቀረት በውድ ዋጋ ሶፍትዌር ከውጭ እንዳስመጣው ሁሉ የአንድን ሀገር የትምህርት ችግር ለመፍታት የሌላውን ሀገር የመፍትሔ ሃሳብም ሆነ መሳሪያ ሥራ ላይ ማዋልን ችላ ማለት አይገባም።

እራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት ምስክርነታ ቸውን የሰጡ፣ አቶ አበራ የተባሉ ሰው ‹‹እራሴን ምሳሌ ባደርግ በምህንድስና በጥሩ ውጤት ተመርቄያለሁ አሁን እንግሊዘኛ አቀላጥፌ መናገር አሊያም አንብቤ መረዳት አልችልም። ግን ደሞ ሁሉንም ኮርሶች የተማርኩዋቸው በእንግሊዘኛ ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሌላው ደግሞ የግል አሳይመንት፣ የቡድን አሳይመንት እና ፕሮጀክት እየተባሉ የሚሰጡን ግዴታዎችን በቀጥታ ከኢንተርኔት download እናደርጋለን። አሊያም ሌሎች የሰሩትን ገልብጠን እንሰጣለን። ከዚህ ላይስ የኛ ሚና ምንድን ነው? የሚሰጡን ኮርሶችም ከሀገራችን ሁኔታዎች ጋር አይዛመዱም። አሁን ላይ ሳስበው በሌለን ችግር ላይ የተሰጠ መፍትሔ ይመስለኛል። ሁሉንም ሌሎች ችግሮቻቸውን የፈቱባቸውን መፍትሔዎች ከምንወስድ ለራሳችን ችግር በራሳችን አቅም መፍትሔ ስለመፈለግ ብንማርስ?›› በማለት የሰጡት አስተያየትም ሆነ ሌሎች ለትምህርት ሥርዓታችን መውደቅ ማሳያዎች ብቻ ሳይሆኑ አሁን እየተሰራ ላለው ሪፎርምም ግብዓት ናቸው።

አጥኚዎች እንደሚሉት ‹‹የትምህርት መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ መጣል ከጀመረ ከመቶ ዓመታት በላይ የተቆጠረ ሲሆን ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በፊት ትምህርት የሚሰጠው በመንግሥትና በሃይማኖት ተቋማት ዙሪያ ለአስተዳደራዊ ክሂሎት፣ ለቀኖናና ለሃይማኖት እውቀት ሲባል›› ነበር፡፡

‹‹ዛሬስ?›› ሲባሉ፤ ‹‹የዛሬው ለምንም አይሆን›› የሚለው መልሳቸው ነው።

እንደምንገነዘበውም ሆነ ብዙዎች ጊዜና ጉልበት፤ እንዲሁም ገንዘባቸውን በማፍሰስ እንደ ደረሱበት ኢትዮጵያ በታሪኳ በነጭ ተወርራ፤ ቅኝም ተገዝታ አታውቅም። ይህም ያሏትን መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ሀብቶች ሳታስነካ ጠብቃ ለማቆየት አስችሏታል። ይሁን እንጂ፣ በብልሹ የትምህርት ሥርዓቶች ምክንያት እነዚህን እሴቶች፣ ሀብቶች በትምህርት አማካኝነት ለትውልዶች ማስተላለፍ አልተቻላትም። ይህም በበኩሉ አሁን ያለውን፤ የምንመለከተውን ችግር ፈጥሯል።

ባጠቃላይ፣ ያለፉትን ማድነቅ ተገቢ ሆኖ የወደቁትን ማውገዝ ልክ አይመጣም። የትምህርት ሥርዓታችን፣ ባለቅኔው ደበበ ሰይፉ እንዳለው፣ መታሸት፣ መወቀጥ፣ መደለዝ፣ መፈተግ ያስፈልገዋል። ባጭሩ፣ ሪፎርሙ ትርጉም ባለው፤ ሀገርና መጪውን ትውልድ ባገናዘበ መልኩ ሊተገበር፤ የለውጥ አሰራሩም ተጠናክሮም ሊቀጥል ይገባል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You