ኢትዮጵያ በቅርቡ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ ገብታለች። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የዋጋ ንረትን ለመቀነስ እንደሚያግዝ ይነሳል። የሀገር ውስጥ ገቢን፣ የፋይናንስ ዘርፉን አካታችነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግና የውጭ ምንዛሬ መዛባትን ለማስተካከል እንደሚያግዝም ተገልጿል። ማሻሻያው ሀገሪቱን ወደ ገበያ መር ኢኮኖሚ ሥርዓት ሊያስገባት እንደሚችል ደግሞ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለመሆኑ ገበያ መር ኢኮኖሚ ሲባል ምን ማለት ነው? በአሁኑ ዘመን ዓለም ላይ በዚህ መንገድ ኢኮኖሚያቸውን የሚያንቀሳቅሱ ሀገራት እነማን ናቸው? ስኬታቸውስ ምን ይመስላል? ስንል ጠይቀናል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርኸ (ዶ/ር)፤ ገበያ መር ኢኮኖሚ ሲባል ገበያው ዋጋን እንዲወስን የሚያስችል ነው። ባለሀብቶች የሚሳተፉበት፣ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ሊያፈሱ የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል ሥርዓት መሆኑን ያስረዳሉ።
በገበያ መር ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግሥት ድርሻ ሙስናን፣ የግሉን ዘርፍ፣ ኪራይ ሰብሳቢነት መቆጣጠር፣ የፖሊሲዎች ለውጥ ማድረግና የተለያዩ ተግባራት መፈጸም መሆኑን ጠቅሰው፤ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ሰላምና ጸጥታን ማምጣት፣ ኢንቨስተሮች ሥራቸው የሚሠሩበትን ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር መሆኑን ይናገራሉ።
በአፍሪካ ውስጥ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ የገበያ መር ኢኮኖሚ ከሚከተሉት መካከል እንደሚጠቀሱ ገልጸው፤ ቻይና፣ ቬትናም፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን፣ ኢንዶኔዢያ፣ የምሥራቅ አውሮፓ ሀገራት በገበያ መር ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ማደጋቸውንም ያስረዳሉ።
የገበያ መር ኢኮኖሚን በመጠቀም ዓለም ላይ ብዙ ነገሮች እየተቀየሩ ነው የሚሉት ባለሙያው፤ ሀገራቱ የንግድ ሚዛናቸው በከፍተኛ ደረጃ ተስተካክሎ በርካታ የውጭ ምንዛሬ ትርፍ እንዳላቸው ይገልጻሉ።
የገበያ ኢኮኖሚ ትግበራ እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ቤተሰብ ያለውን ኢኮኖሚ ለማሻሻል የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሀገሪቱ ወደ ውጪ የሚላከውን ምርት ማሳደግ እና ዕሴት መጨመር፣ መጠኑን ከፍ ማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ለግሉ ዘርፍ፣ ለገበያ የኢኮኖሚው መሠረትና ምሰሶ የሚሆኑ ነገሮች እየተፈጠሩ እንደሚገኝ በመግልጽ፤ የካፒታል ገበያ መጀመር፣ የውጪ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት እና የውጪ ምንዛሬ በገበያ ደረጃ መወሰን ለዕድገት ምሰሶ እንደሚሆኑ ያስረዳሉ።
ባለሀብቶች በካፒታል ገበያው ካፒታል ማመንጨት የሚችሉበትና አክሲዮን እየሸጡ ኩባንያዎችን መፍጠር የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ገልጸው፤ የባንኮች የውጪ ምንዛሬ መጠን ከጥቁር ገበያው በላይ መሆን ሀገሪቱ በርከት ያለ የውጪ ምንዛሬ እንድታገኝ እንደሚረዳም አመላክተዋል።
የኢኮኖሚው አስተዳደር እየተስተካከለ መሄድ ለገበያ ኢኮኖሚው መሠረት እንደሚሆን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት በኩል ሀገርን መጠበቅ፣ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች እንዳይወርድ መከላከል፣ የግሉ ዘርፍ ሊሠራቸው የማይችሉ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን መሥራት እንደሚኖርበት ይናገራሉ።
በመንግሥት በኩል የአስተዳደርና የቁጥጥር ሥራዎችን፣ የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የመዋዕለ ነዋይና ፊስካል ፖሊሲዎችን በትክክል መተግበር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በዚህም ሀገሪቱን ከተረጂነት ማውጣት እንደሚቻል ያስረዳሉ።
መንግሥት ከፍተኛ ልምድና ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች መመደብ እንደሚጠበቅበት በመግለጽ፤ በተለይም መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር ሀገር እንዳይዘረፍ መቆጣጠር እና መከታተል እንደሚገባው አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ በርካታ የመንገድ፣ የኃይል ማመንጫ፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተሠርተዋል የሚሉት ባለሙያው፤ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ከመጣ፣ ለኩባንያዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠርና የገበያ አስተዳደሩ ማሻሻል ከተቻለ የገበያ መር ኢኮኖሚ ውጤታማ ሊሆን ይችላል ይላሉ።
በገበያ መር ኢኮኖሚ ውስጥ ዋጋ፣ የአቅርቦት መጠን የሚወሰነው በገበያ እንጂ መንግሥት በሚያወጣው ኮታና የዋጋ ተመን አይደለም የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር አጥላው ዓለሙ (ዶ/ር) ናቸው።
የገበያ መር ኢኮኖሚ ሁሉም ነገር በገበያ የሚወሰን ነው የሚሉት አጥላው (ዶ/ር)፣ የገበያ ዋጋዎች በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ባለው መስተጋብር የሚወሰን በመሆኑ የዋጋ ጣሪያና ወለል የሚባሉ ነገሮች ላይ መንግሥት አይገባም ይላሉ።
አብዛኛው ገበያ መር ኢኮኖሚ እንከተላለን በሚሉ ሀገራት ላይ መንግሥት ጣልቃ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ አንድ አንድ ሀገራት ላይ የመንግሥት ተጽዕኖ የበረታ ሲሆን ሌሎች ላይ ደግሞ በመጠኑ ጣልቃ በመግባት የቀረውን ገበያው እንደሚመራ ያስረዳሉ።
በገበያ ብቻ የሚመራ ኢኮኖሚ የሚለው ዕሳቤ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያለበት እንደሆነ ገልጸው፤ በአብዛኛው ሀገራት የሚታየው ጥምር (Mixed) ኢኮኖሚ ሲሆን ነገር ግን በአውሮፓ፣ አሜሪካም እና ቻይና ገበያው ትልቅ ሚና ሲጫወት ይስተዋላል ሲሉ ይናገራሉ።
በአሁኑ ጊዜ ንጹህ ገበያ መር ኢኮኖሚ ባይኖርም በአብዛኛው ጉዳዮች መንግሥት ጣልቃ አይገባም የሚሉት አጥላው (ዶ/ር)፤ አውሮፓና አሜሪካ ኢኮኖሚዎች ላይ መንግሥት ጣልቃ እንደሚገባና በኢኮኖሚው የገበያው ሚና ግን ቀላል የሚባል አለመሆኑን ያስረዳሉ።
ገበያ መር ኢኮኖሚ አቅርቦትና ፍላጎት በግለሶች የሚወሰን በመሆኑ መንግሥት ይመራዋል፤ ያስተዳድረዋል እንጂ የግለሰቦችን ነጻነት፣ ሀብት የማፍራት መብት የተከበረ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥት ጣልቃ የሚገባው በሥርዓትና ደንብ መሠረት ለኢኮኖሚው አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መሆኑን ይናገራሉ።
በገበያ መር ኢኮኖሚ ውስጥ ሰዎች ነጻነታቸው፣ የመሥራት የመበልጸግ፣ ሀብታቸውን የማንቀሳቀስ መብቶች እንደሚከበሩ በመግለጽ በዚህም አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውሮፓ ሀገራት፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን ኢኮኖሚያቸው የዳበረ ሀገራት መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም