የህትመት ሚዲያ ተግዳሮቶችን እንዴት ማሻገር ይቻላል?

ዜና ትንታኔ

የሀገራችን የመገናኛ ብዙሃን ዘርፉ እድገት እያሳየ ሲሆን በተቃራኒው ፈር ቀዳጁ የህትመት ሚዲያ ማደግ ባለበት ልክ እያደገ አይደለም፡፡ ለዚህም የማንበብ ባህል መቀነስ፣ መረጃን በቀላል የዲጂታል አማራጮች ማግኘት መቻል እና የህትመት ዋጋ መናር የህትመት ሚዲያው እንዳያድግ የሚጎትቱት ምክንያቶች እንደሆኑ የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡

የህትመት ሚዲያው ለማህበረሰባዊ እድገት ከፍተኛ ሚና ያለውና የማንበብ ባህልን የሚፈልግ ዘርፍ ቢሆንም በሀገራችን ያለው የማንበብ ባህል ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መምጣቱ እውን ነው፡፡

ለመሆኑ የህትመት ዘርፉ ለማህበረሰባዊ፣ ለኢኮኖሚና ፖለቲካዊ እድገት ያለው አስተዋጽኦ ምንድነው? ዘርፉ ያሉበት ችግሮች ምንድናቸው? ያሉትን ችግሮችን ለመሻገር መሠራት ያለባቸው ተግባራትስ ምንድናቸው? የሚሉ ጉዳዮች ላይ የዘርፉ ምሁራን ለኢፕድ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምህርና ተመራማሪ ጌታቸው ጥላሁን (ዶ/ር)፤ የህትመት ሚዲያ ሃሳብን ፣ባህልን፣ ፍልስፍናን፣ እውቀትን፣ ይዘትን በዋናነትም መረጃን ለረዥም ጊዜ በመሰነድ በጽሁፍ የሚያቀርብ ነው ይላሉ፡፡

በሁለተናዊ እድገት ውስጥ የህትመት ዘርፉ ያለው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም የሚሉት ጌታቸው ጥላሁን (ዶ/ር)፤ ማህበረሰቡ እውቀቱንና ባህሉን እንዲሁም ማንነቱን እርስ በእርስ የሚጋራበትና የሚያስተላልፍበት መሆኑን ይገልጻሉ።

አንድ ማህበረሰብ የንባብ ባህል ሲኖረውና ያነበበውንም ሲወያይበት አጠቃላይ የሆነ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የባህል እድገትን ሊያመጣ እንደሚችል ይናገራሉ።

ጌታቸው (ዶ/ር)፤ የህትመት ዘርፉ ያሉ ችግሮች በርካታ ናቸው፤ በዋናነት የዲጂታል ሚዲያው እየተበራከተ መምጣት የሚጠቀስ ነው፡፡

የዲጂታል ሚዲያው በአጭር ጊዜ ብዙ መረጃ በተለያዩ አማራጮች ማግኘት የሚቻልበት በመሆኑ የሰዎች ምርጫ መሆን ችሏል፡፡ ይህም የህትመት ዘርፉን በእጅጉ ጎድቶታል ይላሉ፡፡

የህትመት ሚዲያው በተፈጥሮው ጊዜን፣ አስተውሎትን እንዲሁም ጥሞና ይፈልጋል የዲጂታል ሚዲያው ግን በተቃራኒው ነው ሲሉ የሚናገሩት መምህሩ፤ በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ በዲጂታል ሚዲያው ተጽዕኖ ምክንያት ጋዜጦችንም ሆነ ሌሎች የህትመት ውጤቶችን የማንበብ ልምዱ በእጅጉ መቀነሱን ያነሳሉ፡፡

በሌላ በኩል ከህትመት ግብዓቶች የዋጋ መናር፣ የማንበብ ባህል መቀነስ፣ የህትመት ዘርፉን የሚያበረታታ ፖሊሲ አለመኖር ፣ ሃሳብን በነጻነት ያለመጻፍ፣ ለሁሉም እድሜ ክልል የሚሆኑ ህትመቶች አለመኖር የህትመት ዘርፉ እየደከመ እንዲመጣ ምክንያት የሆኑ ሌሎች ጉዳዮች መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡

የህትመት ዘርፉ ወደቀደሞ ቦታው እንዲመለስና እንዲያድግ ለማድረግ በዋናነት የማንበብ ባህልን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን የሚገልጹት ጌታቸው ጥላሁን (ዶ/ር)፤ ለሁሉም የእድሜ ክልል ተነባቢ የሆኑ ጽሁፎችን ለአንባቢው ማበርከትም ሌላኛው የቤት ሥራ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ በመንግሥት በኩልም የህትመት ዘርፉን የሚያበረታታ ፖሊሲ መንደፍ እንሚያስፈልግ ይናገራሉ።

ህትመት ሚዲያው ከየትኛውም ሚዲያ ቀድሞ የተፈጠረ መሆኑን የሚያነሱት ደግሞ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህርና የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርሃን ደጀን ናቸው፡፡

የህትመት ሚዲያ የተዋጀው ህብረተሰብን ለማንቃት፣ መረጃን ለማሳወቅና የሚዲያ ምንነትን ለመግለጽ ነው የሚሉት አቶ ደጀን፤ በዓለም ላይ የእንግሊዝና የፈረንሳይ አብዮት ሲቀሰቀስ፣ አሜሪካ ነጻነቷን ስታውጅ፣ ሀገራችንም ሃይለሥላሴን ጨምሮ ሌሎች መሪዎችን ስታስተናግድ የህትመት ሚዲያው ያበረከተው ሚና ቀላል አልነበረም ይላሉ፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ የህትመት ሚዲያው እየተቀዛቀዘ መምጣቱንና በተለይም መጽሄቶች የድሮ ዝናቸውና ተነባቢነታቸው እየቀነሰ መምጣቱን የሚያነሱት መምህሩ፤ ለዚህም ዋነኛ ምክንያት የሚሆነው ከዲጂታል ሚዲያው መረጃን በቀላሉ ማግኘት መቻሉ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

አሁን ላይ የህትመት ሚዲያው በሌሎች አማራጮች የገበያው እየወጣ ይገኛል፡፡ ይህም የዲጂታላይዜሽ ጋር የተገናኘ በመሆኑ ሲሆን በሚዲያው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘርፍ የኤሌክትሮኒክስ አማራጮች በሰዎች ተመራጭ እየሆነ መጥቷል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

የህትመት ሚዲያው አሁን ካለበት ችግር ሙሉ በሙሉ መውጣት አይችልም የሚሉት መምህሩ፤ ሆኖም አሁን ያለውን አቅም ይዞ እንዲቀጥል ዘርፉ እራሱን በማዘመን ወይም ኮንቨርጅድ የሚዲያ ሥርዓትን በመጠቀም አማራጮችን ማስፋት ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ህትመቱ ለሕጋዊ አማራጮችና ለሰነድ (ለአርካኢቭነት) እንዲውል መደረግም ያስፈልጋል ይላሉ።

ሚዲያው እንዲቀጥልና ማንበብ ክህሎት እንዲጨምር በዘርፉ ያሉ ጫናዎችን በመረዳት የህትመት ወጪዎችን በተለይም ከውጭ የሚገቡ ወረቀቶችን ከታክስ ነጻ የማድረጉ ሥራ የመንግሥት መሆን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት የማስታወቂያ ሥራዎች ለህትመት ሚዲያው ቅድሚያ እንዲሰጥ እድል ሊፈጥር እንደሚገባ ገልጸው፤ ይህም የህትመት ሚዲያው በኢንዱስትሪው ላይ እንዲቆይ እንደሚረዳው ይናገራሉ፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ፈር ቀዳጅ የሆነው የህትመት ሚዲያ በአንድ ሀገር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ውስጥ ጉልህ ሚና ይጫወታል። በተለይም በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ከፍተኛ ሚና አለው። በተለይ ለሕዝብ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ፣ በማሳወቅ፣ በማስተማርና በማዝናናት የሚዲያ ሚናውን ይጫወታል። እንዲሁም የዜጎችን ሃሳብን የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብት ተግባራዊ በማድረግ እና የተለያዩ አመለካከቶችንና አስተያየቶችን በማስተናገድ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መዳበር ከፍተኛ ድርሻ ያበርክታል።

ይህ ፈር ቀዳጁን ሚዲያ ሚናውን እንዲጫወት ተግዳሮቶችን ፈትቶ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል፡፡

ከሕትመት ዋጋ መናርና ከድጅታል ሚዲያው መምጣት ጋር ተያይዞ አጣብቂኝ ውስጥ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የሕትመት ሚዲያ ኢንዱስትሪ ለመታደግ ሁለተናዊ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም ምሁራኑ ይመክራሉ፡፡

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You