ብሔራዊ ትርክት – አሰባሳቢው ጥላ

ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “የትርክት ዕዳና በረከት” በሚል ርዕስ በቅርቡ ባሳተሙት መጽሐፋቸው፤ ትርክት ሁን ተብሎም ይሁን በተለምዶ በዓላማ የሚዘጋጅ ንግርት መሆኑን ገልጸዋል።

ሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል እንደሚሉት፤ ትርክት ብዙ ጊዜ ታሪክን፣ እምነትን፣ ባህልን እና አመለካከትን የሚይዝ ሲሆን፤ የሚነገርበት ምክንያትም አለው። የሚዘጋጀውም ለዚያ ምክንያት ሲባል ነው። የሚካተቱት ከተዘጋጀበት ዓላማ ጋር የሚሄዱ ሃሳቦችና ታሪኮች ናቸው።

ብዙ ጊዜ የትርክቶች በጎነትና እኩይነት በትርክት ቀራፂዎቹ እጅና ፍቃድ ወይም ቁጥጥር ስር ሊወድቅ እንደሚችል የሚያመላክቱት ፀሐፊው፤ በበጎ ዓላማ ከተዘጋጁ በአንድ ሀገር ሕዝቦች መካከል መግባባትና አንድነት እንደሚፈጥሩ ሁሉ፣ በዕኩይ ዓላማ ከተዘጋጁ ደግሞ መቃቃር በመፍጠር የግጭት አዙሪት ውስጥ ያስገባሉ ነው የሚሉት።

ለአንድ ወገን ዓላማ የተቀረፀ፣ ልዩነትን እና ብዝሃነትን ያልተቀበለ፤ ማቀራረብና ማግባባት ዓላማው ያልሆነ ኅብረ ብሔራዊነትን የማይፈጥር ትርክት፣ ባለፉት ዘመናት ኢትዮጵያን ብዙ ፈትኗታል። ብዙ ዋጋም አስከፍሏታል ሲሉም ያክላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም (ዶ/ር) በተለያዩ መድረኮች ስለ ኢትዮጵያ ታላቅ ትርክት መገንባት እንደሚገባና የጋራ ገዥ ወይም ታላቅ ትርክት መገለጫው ሚዛናዊነት፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ፍትሐዊ የሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲሁም አብሮነት መሆኑን ሲናገሩ ይደመጣል።

ኢትዮጵያን በህብረ ብሔራዊነት ወደ ከፍታ ለማሻገር ከራስ ባለፈ ለሌሎች ማሰብ፣ በጋራ ትናንት እና በጋራ ነገ አጀንዳዎች መሰባሰብ እና አርበኛ መሆን እንደሚገባም ያነሳሉ።

ለመሆኑ ባለፉት ስድስት ዓመታት አሰባሳቢ ብሔራዊ ትርክትን ለማጠናከር ምን ተሰርቷል? በአዲስ አበባ እና በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩት የፖለቲካ ተመራማሪው ሙሉጌታ ደበበ (ዶ/ር) ብሔራዊ ትርክት የአንድ ሀገር ሕዝብ በጋራ የሚኖረው እሴት፣ ግንዛቤ እና አስተሳሰብ ነው ይላሉ።

ዶክተር ሙሉጌታ እንደሚሉት፤ ብሔራዊ ትርክት ስንል ኢትዮጵያ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ማለታችን ነው። ጥቃቅን ልዩነቶችን ትተን የጋራ በሆኑ ነገሮች ላይ ስንሰባሰብ የሚመጣ ጥላ ነው። ኢትዮጵያ የውጭ ወራሪዎችን ከመመከት አንጻር በምሥራቅ አፍሪካ ስትጫወት የነበረው ሚና ቀላል አይደለም። በቀጥታና በጎረቤቶቿ አማካኝነት በውክልና የሚመጡባትን ሃይማኖታዊ እና ጎሳዊ ግጭቶችን የመፍጠር ሙከራዎችን ሁሉ ተቋቁማ የኖረች ታላቅ ሀገር ናት። ይሄ በራሱ ትልቅ ትርክት ነው። ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ነበረች፤ አሁንም ታላቅ ናት ወደፊትም ደግሞ እጅግ ታላቅ ሀገር እናደርጋታለን የሚለው አመለካከት የጋራ ትርክታችን ነው።

እያንዳንዱ ሥርዓት የራሱ ትርክት እንዳለው የሚያነሱት የፖለቲካ ተመራማሪው፤ የኢህአዴግ እና የደርግ ሥርዓቶችም የየራሳቸው ትርክት ነበራቸው። በተለይም በዘመነ ኢህአዴግ የነበረው ትርክት አሁን ላለንበት ዘመን በከፍተኛ ደረጃ ደንቃራ ሆኗል። አመለካከት፣ እንደ ሕዝብ ጠቅላላ ከሥነ ምግባር እና ከወጣቱ የመማርና ሀገር ከመለወጥ አቅም አንጻር በጣም ብዙ ጣጣዎች መጥተዋል ነው የሚሉት።

ባለፉት ስድስት ዓመታት አጋር ብለን የምንፈርጀው ሕዝብ ሳይኖር ሁሉም ሕዝቦች የሚሳተፉበት፤ በጋራ የምናድግበት እና ወደ ብልጽግና የምናመራበት ሀገር ነው ያለን የሚል አመለካከት እየተገነባ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ይሄ አመለካከት እስከሚሰርጽ ድረስ ፈተናው ቀላል እንደማይሆን ይገልጻሉ።

ከለውጡ ወዲህ አሰባሳቢ ብሔራዊ ትርክትን ለማጠናከር ብዙ እየተለፋ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ሙሉጌታ፤ ብሔራዊ የሆነው ብልጽግና ፓርቲ መመስረቱ በራሱ አንድ ፋይዳ አለው ብለው እንደሚያስቡ ይናገራሉ።

አንዱ ብሔር በቁጥር ስላነሰ እና ስለበዛ ወይም ጉልበት ስላለውና ስለሌለው ልዩነት ሳይደረግበት ሁሉም እንደ አቅሙ የሀገሪቱ ባለቤት ሆኖ የሚሄድበት ሁኔታ ተፈጥሮ ፌዴራሊዝሙ በትክክል መሬት የሚይዝበት መንገድ መኖሩ ጥሩ ነው ሲሉም ያክላሉ።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በየጊዜው በሚፈጠሩ የተለያዩ ሁነቶች ብሔራዊ ትርክት እና አንድነት እንዲጎላ እየተደረገ መሆኑን የሚያመላክቱት የፖለቲካ ተመራማሪው፤ ታላቁ ቤተመንግሥት አንድነት ፓርክ ተብሎ ተሰይሟል፤ እንዲሁም ፊት ለፊቱ የሚገኘው ትልቅ አረንጓዴ ስፍራ ወዳጅነት አደባባይ ተብሏል፤ በእነዚህ ሁሉ መንገዶች ብሔራዊ ትርክትን ማጉላትና የሰፈር ጉዳዮችን የማኮሰስ ሥራ እየተሠራ ነው። ውጤቱ በአጭር ጊዜ የሚታይ ባይሆንም አዝማሚያው ወደ ጥሩ አቅጣጫ እየሄድን እንደሆነ ያሳያል ብለዋል።

አያይዘውም፤ አንዱ ሌላው ላይ ተጽዕኖ ሳያደርግ ሁሉም የሚሳተፍበት የጋራ ሥርዓት ለመመስረት በሚደረገው ጥረት ችግሮቻችንን እየፈታን እየሄድን ነው ብዬ አስባለሁ። ሌሎች ሀገሮችም በተመሳሳይ መንገድ ብዙ ሃይማኖታዊ ችግሮችን፣ የኢኮኖሚ ልዩነቶችን፣ የእውቀት መራራቅን እና ብሔር ተኮር ፈተናዎችን አልፈው ነው መደማመጥና ማደግ ደረጃ ላይ የደረሱት። እኛም ወደዛ የምንገባ ነን ብዬ አምናለሁ ይላሉ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ቋሚ ተጠሪ ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ህብረብሄራዊ ሆኖ ሁሉንም ማንነቶች ይዞ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችለው ብሔራዊ ትርክት ነው። ብሔራዊነት ላይ በጋራ መሥራት አለብን የሚል አቅጣጫ ይዘን ነው የለውጡን ጉዞ የመራነው ይላሉ።

በአንድ በኩል ህብረብሔራዊነትን ወይም ብዝሃነትን የማይቀበል እሳቤ የተሸከመ ትርክት የሚያራምዱ አሉ። ይህ ትርክት ከኢትዮጵያ ባህሪ ያፈነገጠ ነው። ኢትዮጵያውያን የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግና ማንነት ይዘን ኢትዮጵያ የምትባል ትልቅ ሀገር በአፍሪካ ቀንድ ፈጥረናል።

በሌላ በኩል በብዝሃነታችን ምክንያት እምብዛም አንድ የሚያደርገን ነገር የለም፤ ከአንድነት ይልቅ የየራሳችን ነጠላ ውጤት ይበልጣል ብለው የሚያስቡ ወገኖች አሉ። ይህ ትርክት ኢትዮጵያውያን በዘመናት ሂደት የገነቡትን እና ያጎለበቱትን የጋራ ሀገራዊ እሴት ስለሚንድ ከፋፋይና ነጣጣይ ነው፤ ለሀገር ግንባታ የማይጠቅምና የሚያሳንሰን ነው ብለዋል።

የለውጡ መንግሥት አቋም ሁለቱም ጽንፍ የያዙ የግራና ቀኝ አመለካከቶች ለኢትዮጵያ እንደማይጠቅሙ በመረዳት የሚጠቅመን ህብረብሔራዊነትን የሚቀበል፣ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንንም ይዞ የሚነሳ በንዑስ ማንነቶችና በሀገራዊ አንድነት መካከል ሚዛን ሆኖ ጠንካራ ሀገር መገንባት የሚያስችል አካሄድ መከተሉን ገልጸዋል።

“ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት የመደመር መጽሐፍም ብሔራዊነትን የሚመለከት ሃሳብ ተካቷል። እኛ እንደ ብልፅግና ፓርቲ ስንመሰርትም አንዱ ማዕከላችን ብሔራዊነት ነበር። የመንግሥት ፖሊሲዎችና የዕቅድ አቅጣጫዎችም የተቃኙት በዚሁ መንገድ ነው” የሚሉት የመንግሥት ተጠሪው፤ በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ከላይኛው አመራር ጀምሮ እስከ ታች አባላት ድረስ እሳቤው ዋነኛ የንቅናቄ ማዕከል እንዲሆን ተደርጓል። በተጨማሪም ሕዝባዊ መሆን ባሉባቸው ጉዳዮች ላይ ለሕዝቡ ቀርቦ ውይይት ሲካሄድበት ከርሟል። በመገናኛ ብዙኃንም ጠንካራ ሀገራዊ ትርክት እንዲኖር ለማድረግ ብዙ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል ነው የሚሉት።

በሌላ በኩል የከራረሙ ችግሮችን ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋምና ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን የሚጠቁሙት ዶክተር ተስፋዬ፤ ኮሚሽኑ ከትርክት እና ከታሪክ ጋር የሚያያዙ አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑና ኋላቀር ከሆነው የፖለቲካ ባህላችን ጋር የሚያያዙ፣ በየጊዜው ሀገራችንን ለትርምስ፣ ለግጭት እና ለጦርነት እየዳረጉ የመጡ ጉዳዮችን ቁጭ ብለን በመነጋገር እንድንፈታ የሚያደርግ መሆኑን ይገልጻሉ።

ካለፉት ጊዜያት ጋር የሚያያዙ ቁርሾዎች የሚፈቱበት የሽግግር ፖሊሲ ተቀርፆ ወደ ሥራ እየተገባ እንደሚገኝም የሚያመላክቱት የመንግሥት ተጠሪው፤ የተዛባውን ትርክት ለማስተካከል ባለፉት ስድስት ዓመታት የተጀመሩት ተከታታይ ሥራዎች የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስገኙ ኢትዮጵያውያን በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።

ለሁላችንም የምትሆን ሀገር ለመገንባት የተስተካከለ ትርክት መያዝ እንደሚያስፈልግ ማመን አለብን። ምክንያቱም አጀንዳው ከአንድ የፖለቲካ ቡድን ወይም በአንድ ወቅት ከሚኖር መንግሥት ጋር የሚያያዝ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው ሲሉም አሳስበዋል።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You