የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድጋሚ የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተደረገባቸው የግድያ ሙከራ አምልጠው “ደኅንነቱ የተጠበቀ” ቦታ እንደሚገኙ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስታወቁ። ትራምፕ ፍሎሪዳ በሚገኘው የጎልፍ መጫወቻ ሜዳ ላይ ሳሉ ነው የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው። “ተጠርጣሪ የተባለ” ግለሰብ በቁጥጥር ሥር እንደዋለም ባለሥልጣናቱ ገልፀዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የደህንነት ጥበቃ ተቋም የሆነው ሲክሬት ሰርቪስ ባልደረቦች አንድ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ግለሰብ ተመልክተው ተኩስ እንደከፈቱበት ተናግረዋል። የሀገር ውስጥ የወንጀል ምርመራ ክፍል የሆነው ኤፍቢአይ ደግሞ ትራምፕ ግለሰቡ ከነበረበት ቦታ ከ275 እስከ 455 ሜትር ርቀት ላይ ነበሩ ብሏል።

ኤኬ47 የተባለው ዓይነት የጦር መሣሪያ እና ማነጣጠሪያ እንዲሁም ሁለት ቦርሳዎች እና ጎፕሮ የተባለ ካሜራ በሥፍራው መገኘታቸውን ፖሊስ አስታውቋል። አንድ የዓይን እማኝ እንደተናገረው ተጠርጣሪው ተኩስ ሲከፈትበት ከተደበቀበት ጫካ ወጥቶ ወደ አንድ ጥቁር ኒሳን መኪና ዘሎ ገብቷል።

የዓይን እማኙ የተጠርጣሪውን መኪና እና የሰሌዳ ቁጥር ፎቶ ያነሳ ሲሆን፣ ይህች መኪና ከቆይታ በኋላ ማርቲን ካውንቲ በተባለው በጎልፍ መጫወቻው ሰሜናዊ ክፍል ተገኝታለች። የፓልም ቢች ካውንቲ የፖሊስ ኃላፊ እንደሚሉት “ተጠርጣሪው መኪናው ውስጥ ሳለ በማርቲን ካውንቲ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል።”

ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው በላኩት የኢሜይል መልዕክት “ደህና ነኝ” በማለት ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ገልጸዋል።“ምንም ነገር ቢመጣ ወደኋላ አይመልሰኝም። በፍፁም እጄን አልሰጥም” ሲሉም ትራምፕ ጽፈዋል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከሁለት ወራት በፊት ገደማ ፔንሲልቬኒያ ግዛት ውስጥ በምትገኝ ከተማ የምርጫ ቅስቀሳ እያካሄዱ ሳለ በተፈፀመባቸው የግድያ ሙከራ ጆሯቸው በጥይት መጨረፉ ይታወሳል።

ሲክሬት ሰርቪስ በኤክስ ገፁ እሑድ ከሰዓት በአካባቢው አቆጣጠር 8፡00 ገደማ ከትራምፕ ጋር በተያያዘ ለተከሰተ አደጋ ምላሽ እየሰጠ እንደሆነ ጽፏል። ማር-አ-ላጎ የሚባለው ፍሎሪዳ ግዛት የሚገኘው የትራምፕ ንብረት የሆነው ግዙፍ ጊቢ እና የጎልፍ መጫወቻ እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ መንገዶች የተዘጉ ሲሆን፣ በርካታ የፀጥታ ሰዎች በሥፍራው ተሰባስበሰው ይገኛሉ።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ተጠርጣሪው ራያን ዌስሊ ራውዝ የተባለ የ58 ዓመት የሀዋይ ግዛት ነዋሪ ነው ሲሉ ውስጥ አዋቂ ምንጮችን ጠቅሰው ዘግበዋል ። ራያን የተባለው ግለሰብ ኖርዝ ካሮላይና ግዛት ሳለ የተለያዩ ወንጀሎች ይፈፅም የነበረ ግለሰብ እንደነበር ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

ግለሰቡ የጦር መሣሪያ ደብቆ ማስገባት፣ በቁጥጥር ሥር አልውልም ብሎ በማስቸገር፣ በመኪና ገጭቶ በማምለጥ፣ ባልታደሰ መንጃ ፈቃድ ማሽከርከር እንዲሁም የተሰረቀ ንብረት ይዞ በመገኘት ጥፋተኛ ተብሎ ያውቃል።

ዋይት ሐውስ እንደዘገበው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና ምክትሏ ካማላ ሀሪስ ስለሁኔታው ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል። ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው በመትረፋቸው የተሰማቸውን እፎይታ ገልጸዋል። ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን ከዶናልድ ትራምፕ ጋር አንገት ለአንገት የተናነቁት ካማላ ሀሪስ ደግሞ “ትራምፕ ላይ በተቃጣው ጥቃት በጣም አዝኛለሁ” ማለታቸው ቢቢሲ ጠቅሶ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን መስከረም 7/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You