አዲስ አበባ፡– ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር ለዘመናት ያቆየውን የአብሮነት እሴት በማጎልበት ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚና የብሔራዊ መውሊድ አከባበር ዓቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሼህ አብዱልሃሚድ አሕመድ ገለጹ፡፡
የአንድ ሺህ 499ኛው የነብዩ ሙሐመድ ሰ.ዐ.ወ መውሊድ(ልደት) በዓል ‹‹የሠላሙ ነብይ›› በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች በዛሬው ዕለት በታላቁ አንዋር መስጅድ በድምቀት ይከበራል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚና የብሔራዊ መውሊድ አከባበር ዓቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሼህ አብዱልሃሚድ አሕመድ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ነቢዩ መሐመድ በሕይወት ዘመናቸው ስለ ሠላም፣ ስለ ይቅር ባይነት፣ ስለ መከባበር፣ ስለ መረዳዳት፣ ስለ ፍትሕ እና ስለ ሐቀኝነት አስተምረዋል፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙም በዓሉን ሲያከብር ለዘመናት ያቆየውን የአብሮነት እሴት በማጎልበት ሊሆን ይገባል፡፡
“ነቢዩ መሐመድ የተወለዱት መልካም ነገሮችን ሊያስተምሩና መጥፎ ነገሮችን ደግሞ ሊቃወሙ በመሆኑ መልካም ሥራቸውን በማስተማር ይከበራል” ብለዋል።
ነቢዩ መሐመድ በሕይወት ዘመናቸው ስለ ሠላም፣ ስለ ይቅር ባይነት፣ ስለ መከባበር፣ ስለ መረዳዳት፣ ስለ ፍትሕ እና ስለ ሐቀኝነት ማስተማራቸውን ያወሱት ሼህ አብዱልሃሚድ፤ ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር ለዘመናት ያቆየውን የአብሮነት እሴት በማጎልበት ሊሆን እንደሚገባው ከምክር ቤቱ መልዕክት መተላለፉን ጠቁመዋል፡፡
የእስልምና ሃይማኖት ለሠላም የሚሰጠው ትኩረት ትልቅ መሆኑን ገልጸው፣ ዜጎች ልዩነታቸውን አቻችለው በሠላም በመኖር የነብዩን ፈለግ መከተል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በዓሉ የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት ቁርዓን በመቅራት (በማንበብ)፣ የነብዩ መሐመድ የሕይወት ታሪክ በንባብ እንዲሁም በቀደሙ ጊዜያት ታሪካቸው በግጥምና በዜማ የተጻፉ (መንዙማ) በማቅረብ እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ከድህነት ለመውጣት የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ እድገት ሊሠራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም በዓሉ ሲከበር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ለሀገር ሠላም ዱአ (ጸሎት) በማድረግ የነብያዊ ፈለጋቸውን በመከተልና በማሰብ መሆን እንዳለበት ሼህ አብዱልሃሚድ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2017 ዓ.ም