አዲስ አበባ፡– ባለፈው ነሐሴ ወር ጀርመን በስሎይንጋን ከተማ የደረሰውና ለሦስት ሰዎች ህልፈት ምክንያት የነበረውን የስለት ጥቃት ተከትሎ የድንበር ፍተሻና ጥበቃዋን ልታጠናክር ነው።
ጥቃቱን እንዳደረሰ የተጠረጠረ ግለሰብ ሶሪያዊ ዜግነት ያለው ሲሆን፤ ያቀረበው የጥገኝነት ጥያቄ ወድቅ ተደርጎ ከጀርመን ተጠርዞ እየወጣ ነበር ተብሏል። በዚህም ሳቢያ የጀርመን መንግሥት የድንበር ጥበቃውን እንዲያጠናክር ጫና ሲደረግበት ነበር። አይ ኤስ የተባለው ቡድን የዚህን ጥቃት ኃላፊነት ወስዷል።
ከአምስት ቀናት በኋላ ሥራ ላይ የሚውለው እና ለስድስት ወራት የሚቆየው አዲሱ የድንበር ጥበቃ በአካባቢያዊ ምርጫ ትልቅ ተቀባይነት ያገኘ ነው።
የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፋኢሰር መንግሥት መደበኛ ላልሆኑ ስደተኞች “ጠንካራ መስመር” ያስቀምጣል ያሉ ሲሆን፤ የሚስፋፋው ፍተሻ የእስላማዊ ጽንፈኝነትን እና ድንበር ተሻግረው የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ “ሕዝባችንን ከዚህ ስጋት ለመከላከል ባለን አቅም ሁሉንም ነገር እናደርጋለን” ሲሉም አክለዋል።
ጀርመን በምሥራቅ እና ደቡብ ከሚያዋስኗት ፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ስዊዘርላንድ እና ኦስትሪያ ድንበሮች ላይ የባቡር እና የየብስ ፍተሻ ታደርጋለች።
በአዲሱ አሰራር መሠረት በሁሉም ደንበሮች ላይ ፍተሻ ይጀመራል።
ሆኖም ይህ እርምጃ ከደህንነት ይልቅ ፖለቲካ የተጫነው ነው የሚል ትችት እያስተናገደ ነው።
ከናዚ በኋላ በምሥራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ከፍተኛ ድምጽ ያገኘው የጀርመን የቀኝ አክራሪ ፓርቲ ስደተኞችን የመቀነስ ዕቅዱ ላይ በሚገባ አልሠራም በሚል ከፍተኛ ጫና እየደረሰበት ነው።
ጀርመን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአንጻራዊነት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ጥገኝነት ጠያቂ በሀገሪቱ እንዲኖር ፍቃድ ሰጥቷል።
ጀርመን ከአውሮፓውያኑ 2015 እስከ 2016 ባለው ጊዜ እንደ ሶሪያ ካሉ አገራት ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን የተቀበለች ሲሆን፤ የዩክሬን ጦርነት በ2022 ሲቀሰቀስ ደግሞ 1.2 ሚሊዮን የዩክሬን ዜጎችን ተቀብላለች።
ኤኤፍዲ የተሰኘው ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ስደተኞችን የሚመለከት አዲስ እቅድ ያወጣ ሲሆን፤ በዚህ ሳምንት መጨረሻ በሚደረገው ምርጫ የተሻለ አፈጻጸም እንደሚኖረው ተገምቷል።
ሆኖም የቀድሞ የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ መስፈርቱን የሚያሟሉ ጨምሮ ሁሉንም ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ድንበር የመውሰድ ዕቅድ አቅርቧል። ከዚያም ከድንበር ተነስተው ወደ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት እንዲሻገሩ ማድረግ የዕቅዱ አካል ነው።
ሆኖም ይህ ዕቅድ ከኦስትሪያ ተቃውሞ ገጥሞታል። የኦስትሪያ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ቢልድ ለተባለው መገናኛ ብዙኀን ትናንት ሰኞ በሰጡት አስተያየት፤ አገራቸው በጀርመን ተቀባይነት ያጣን ስደተኛ እንደማትቀበል ተናግረዋል።
“በዚህ ጉዳይ የሚለወጥ አቋም የለም” ሲሉ አክለዋል። ባለፈው ነሐሴ ከደረሰው የስለት ጥቃት በኋላ የጀርመን መንግሥት ስደተኞች ላይ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም