በሱማሌ ክልል ከመኸር እርሻ 31 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል

አዲስ አበባ፡- በሶማሌ ክልል በ2016/17 የምርት ዘመን ከመኸር እርሻ 31 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ የሩዝ እርሻም እየተከናወነ ይገኛል።

የሶማሌ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አህመድኑር አብዲ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2016/17ዓ.ም የምርት ዘመን በክልሉ ሶስት ሺህ ሄክታር መሬትን በሩዝ ሰብል ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን፤ እስከ ነሐሴ 30/2016 ድረስም 530 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል፤ የዝናቡ ስርጭት እስከ ጥቅምት ወር ስለሚቆይ ቀሪውን መሬት በሩዝ የመሸፈን ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በክልሉ የሩዝ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የምርምርና ዘሩን የማብዛት እንቅስቃሴ በትኩረት እየተሰራ ነው ሲሉም ገልጸዋል። በክልሉ በርካታ የሰብል አይነቶችን ማለትም በቆሎ፣ ማሽላ፤ስንዴ፣ገብስና በተወሰነ ደረጃም ጤፍ እንዲሁም ሩዝ ለመጀመሪያ ጊዜ የማምረት ስራ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በክልሉ የታቀደውን 31 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በማግኘት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሰብሎችን በሰው ሀይል የማረም፤ ኬሚካል የመርጨት፣ ፀረ ተባዮችን የመከላከል፤ በሽታ እንዳያጠቃ የመከታተል ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሮች ከ20 ሺህ በላይ ኩንታል በቆሎና ማሽላ፤ 10 ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘሮችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፤ እየተሰራም ነው ብለዋል።

በክልሉ በበጋ መስኖ ከሚለመው መሬት በስተቀር የአፈር ማዳበሪያ የሚፈልግ መሬት የለም ያሉት ኃላፊው፤ ያለውን ለም አፈር ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፊል አርብቶ አደሮችን ወደ እርሻ የማስገባት ስራ እየተሰራ ነው ሲሉ አብራርተዋል። በሶማሌ ክልል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ቴክኖሎጂውን የመጠቀም ስራ እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል።

የክልሉ አርሶ አደሮች ምርጥ ዘርን የመጠቀም ፍላጎታቸው እያደገ ነው፤ ክልሉ የሚፈልጉትን ያኽል ምርጥ ዘር ተደራሽ እያደረገ ቢሆንም እጥረት አለ፤ እጥረቱን ለመፍታት እየተሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ አህመድኑር አያይዘውም ክልሉ ለም አፈር ያለው ቢሆንም የክልሉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የአፈር ማዳበሪያ የመጠቀም ፍላጎት ከፍተኛ ነው፤ ነገር ግን ፍላጎቱን የሚያሟላ አቅርቦት የለም፤ በ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን 70 ሺህ ኩንታል ብቻ የአፈር ማዳበሪያ ነው ማቅረብ የተቻለው ብለዋል።

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You