የሰው ልጅ በምድር ላይ እንዲኖር ከሚያስችሉት መሠረታዊ ፍላጎቶች መካከል እንደ ምግብ (ውሃ)፣ አየር፣ መጠለያና አልባሳትን የመሳሰሉት በዋናነት ሲጠቀሱ የኖሩ ናቸው። ባለንበት ዘመን ከሰው ልጅ ዘመናዊ አኗኗር እና እየተላመደ ከመጣቸው በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አንጻር መሠረታዊ ፍላጎት ወደመሆን የተሸጋገሩና ከሕይወቱ ጋር የተሳሰሩ ሌሎች ጉዳዮች አሉ።
በተለይም ከሰው ልጅ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ ጋር በእጅጉ የተቆራኘውና ከፀሐይ ብርሃን ቀጥሎ ለምንኖርባት ዓለም እንደ ዓይን ብሌን በመሆን የሚያገለግለው፤ ለየትኛውም የምርምርና የፈጣራ ሥራ የጀርባ አጥንት የሆነው ኤሌክትሪክ ቅንጦት መሆኑ ቀርቶ መሠረታዊ ፍላጎት እየሆነ መጥቷል። በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ካለው ወሰን አልባ አገልግሎቱ አንጻር አሁን ላይ ምሁራን ኤሌክትሪክን ከመሠረታዊ ፍላጎቶች ተርታ ሲያሰልፉት ይታያል።
ዛሬ ዓለም ለደረሰበት የስልጣኔ ከፍታ እና ለሰው ልጆች አኗኗር መዘመን ድንቅ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ቀደምት ግኝቶች መካከል ኤሌክትሪክ ግንባር ቀደም ስለመሆኑ የሚከራከር አይኖርም። ኤሌክትሪክ የሰው ልጆችን ድካም አቅልሏል፤ ምርታማነትን አሳድጓል፤ ሀገራትን አስተሳስሯል፤ እድገታቸውን አፋጥኗል፤ ኢኮኖሚያቸውን አስወንጭፏል፤ ከፈጠራ ሥራዎችና ግኝቶች ጀርባም ጉልህ ሚና ተጫውቷል። ዛሬም ኢትዮጵያ የነገ የማደግና የመበልጸግ ተስፋዋን ኤሌክትሪክ ላይ አድርጋ ከተፈጥሮ ሀብቶቿ ማለትም ከውሃ ፣ ከንፋስ፣ ከፀሐይ ብርሃን ፣ ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይልን በማምረት ላይ ትገኛለ ች።
የኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይል ልማት ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚቀዳ ስትራቴጂ ሲሆን ከውሃ 45ሺ ፣ ከጂኦተርማል 10ሺ ሜጋ ዋት እንዲሁም ከንፋስና ከፀሐይ 1ሺ ጊጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል እምቅ አቅም እንዳላት ጥናቶች ያመለክታሉ። እስካሁንም ከ5ሺ 200 ሜጋ ዋት በላይ ከውሃ፣ ከንፋስና ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ላይ ደርሳለች።
ኢትዮጵያ አብሮ መልማትና ማደግን የምታስቀድም ሀገር በመሆኗ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉ ለጋራ ዕድገትና ልማት ኃይልን በማቅረብ የቀጣናውን የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከርም ትሠራለች፤ እየሠራችም ትገኛለች። የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የሆኑ የዓለማችን ሰዎች አሁንም የኤሌክትሪክ አገልግሎት እያገኙ አይደለም። በኢትዮጵያ ደግሞ ከ65 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ አይደሉም።
መንግሥታት ሕዝቦቻቸውን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ በምትኩ ዕድገትና ብልጽግናን ለማምጣት በርካታ የልማት ሥራዎችን ያከናውናሉ። በአመዛኙ የልማት ሥራዎችን የሚያንቀሳቅሰው ሞተር ደግሞ ኤሌክትሪክ ነው። በዚህም መነሻነት ኢትዮጵያ የዜጎቿን ሕይወት ለመቀየር በግብርና፣ በመሬት አጠቃቀም፣ በደን ልማትና ጥበቃ፣ በኢኮኖሚያዊና የሥነ ምህዳር ሥርዓት ማጎልበት፣ በተሻሻሉና ተመራጭ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና ኢንዱስትሪ ልማት፣ በትራንስፖርት አገልግሎትና ግንባታ ሥራዎች አጠቃቀምና በታዳሽና ንጹህ ኃይል ልማት ዘርፍ ላይ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ መገንባት ከጀመረች ሰነባብታለች።
አረንጓዴ ልማት ዛፎችን በመትከል ብቻ የሚተረጎም ሳይሆን የበካይ ጋዞችን ልቀት ማስቀረት የሚችሉ ታዳሽ ኃይሎችንም በማልማት ንጽህ አየር እንዲኖር ማድረግንም ያካትታል። የበካይ ጋዞች ልቀት ቀነሰ ማለት ዓለም በአየር ሙቀት መጨመርና እርሱን ተከትሎ በሚመጣው የኦዞን መሸንቆርና መሳሳት ችግር ሳይፈጠርባት ሚዛኗን ጠብቃ እንድትጓዝ ያደርጋታል። ተፈጥሮ ሚዛኗን ስትጠብቅ ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ ይዘንባል፤ ወንዞች በልካቸው ይሞላሉ፤ የድርቅና የጎርፍ አደጋዎችም ስጋት መሆናቸው ይቀንሳል። የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቆጣጠር ከሚያስችሉ ጉዳዮች አንዱ ለኢንዱስትሪዎችና ለተለያዩ አገልግሎቶች የምንጠቀመውን ኤሌክትሪክ ከታዳሽ ኃይል ማልማት የሚለውም ኢትዮጵያ የምትከተለው ፖሊሲዋ ነው።
ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገትን ማረጋገጥ እንዲያስችላት በኃይል ልማቱ ዘርፍ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ግዙፍ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን መገንባት ችላለች። ከእነዚህ መካከል የዘመናት ቁጭት የወለደው የሕዝቦችን የመልማት አቅም የሚወስነውና የይቻላል ስሜት ማሳያ የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንዱ ነው።
አባቶቻችን ልዩነታቸውን ወደ ጎን ብለው የዓድዋ ጦርነትን ድል እንዳደረጉ ሁሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም እንድንለማና እንድናድግ ለማይፈልጉ ኃይሎች በራስ አቅም፣ ገንዘብና ጉልበት መሥራት እንደምንችል ያሳየንበት፣ የዚህ ዘመን ትውልድ ዐሻራ ነው። ይህም በልማቱ ላይ የተደገመ የአልሸነፍ ባይነት ዳግማዊ የዓድዋ ድል ተምሳሌት ነው።
ይህ ፕሮጀክት ከሌሎች ግድቦች ልዩ የሚያደርገው በውስጥና በውጫዊ ኃይሎች ጠንካራ ፈተና የገጠመውና ፈተናውን አሸንፎ ከስኬት የደረሰ መሆኑ ነው። ኢትዮጵያ እንደሌሎች ሀገራት የራሷ ሀብት በሆነው በዓባይ ወንዝ ላይ ተጠቃሚ እንዳትሆንና የበይ ተመልካች ሆና እንድትቀር ለዘመናት ይደርስባት የነበረውን ክልከላ “ጆሮ ዳባ ልበስ” በማለት የማይደፈረውን በመድፈር፣ የማይቻለውን በመቻል ለውጤት ማብቃት ችላለች።
ከውስጣዊ ችግሮች አንጻርም የግድቡን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ለመሥራት ኃላፊነት ወስዶ የነበረው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በፈጠረው የጊዜ መጓተት፣ የጥራት መጓደል፣ የአስተዳደር እና የብልሹ አሠራር እንከን፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በተባለው ጊዜ ተጠናቆ ጥቅም ላይ የመዋሉን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነበር።
ይሁንና በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የተከሰተው ሀገራዊ የመንግሥት ለውጥ ለህዳሴው ግድብ መድህን እንደነበር የአደባባይ ሀቅ ነው። በተለይ በግድቡ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለመፍታት የለውጡ መንግሥት የሥራ ተቋራጩን የመቀየርና ሥራውን በጥብቅ ዲስሊፕሊን መምራት በመቻሉ ፕሮጀከቱ ከነበረበት ህመም ድኖ ለዛሬው ውጤት መብቃት ችሏል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ከኃይል ጠቀሜታው ባሻገር ዘር፣ ቀለም፣ ፆታ፣ ሃይማኖት፣ ብሄር፣ ቋንቋ፣ ክልል ሳይለይ የሕዝቦችን አንድነት የፈጠረ፣ የአልሸነፍ ባይነትን ክንድ ያሳየ፣ የዘመናት ቁጭትን የመለሰ፣ የዜጎችን ገንዘብ፣ ጉልበት፣ ሃሳብና እውቀትን ያሰባሰበ፣ የቁጠባ ባህልን ያዳበረ፣ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ፣ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ከፍተኛ ሚና የተጫወተ፣ ለቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር በር የከፈተ፣ የሀገራችንንም የመደራደር አቅም ያሳደገ፣ ለዓሳ ሀብት፣ ለቱሪዝም ልማት፣ ለጥናትና ምርምር ዕድል የሰጠ እና የይቻላል መንፈስ የተተረጎመበት ፕሮጀክት ነው።
የለውጡ መንግሥት ሀገር መምራት በጀመረበት ማግስት ለህዳሴ ግድብ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረትና ድጋፍ አበው “የምሥራች ፍሬ ቀመስኩ” እንዲሉ ከሚጠበቀው 5ሺ 150 ሜጋ ዋት ውስጥ በ2014 ዓ.ም በወርሃ የካቲት 375 ፣ በወርሃ ነሐሴ 375 በድምሩ 750 ሜጋ ዋት በማመንጨት ኢትዮጵያ “የህዳሴው ግድብ የምሥራች ፍሬን” መቅመስ ችላለች።
በዘንድሮ የክረምት ወቅትም ሁለት ተርባይኖች ኃይል ወደ ማመንጨት ገብተዋል። በመጪው ታህሳስ ወርም ኃይል የሚያመነጩ ተርባይኖች ቁጥር ወደ ሰባት እንደሚደርስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በነበራቸው የሥራ ጉብኝት ገልጸዋል። የህዳሴው ግድብ ሥራ በመጪው ዓመት ሙሉ ለሙሉ የሚጠናቀቅ መሆኑንም ጠቅሰዋል። እንግዲህ ይህ ግድብ ኢትዮጵያውን አቅማቸውን ገንዘባቸውንና ሃሳባቸውን አስተባብረው የወለዱት አንጋፋው ልጃቸው እንደሆነ ዓለም የሚያውቀው ሀቅ ነው።
ይህ ታላቅ ፕሮጀክት ጠንካራ ህብረ-ብሄራዊ አንድነትን ያጎለበተ፣ የሀገርን ገጽታና ኢኮኖሚም የገነባ ነው። መንግሥት ፕሮጀክቱ በትክከለኛ የጥራት ደረጃና በተያዘለት ጊዜ እንዲከናወን በማገዝ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ አመራር ቦርድንና ተቋሙን እንደ አዲስ በማዋቀር፣ በአዲስ የተዋቀሩት የሥራ አመራር ቦርዱና ተቋሙ ሥራው በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመራ በማድረግ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ብሄራዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤትም እንዲሁ ሕዝባዊ ድጋፍ በማሰባሰብ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
ከሁሉም በላይ የግድቡ ባለቤት የሆነው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ (እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሕፃናት) ተመራማሪዎች ሙያተኞች፣ ዲፕሎማቶች፣ ዲያስፖራዎች ወዘተ የነገ ተስፋችንን የሚያለመልመውን ታላቁ ግድብ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በእውቀት የማይተካ ድጋፍ አድርገናል፤ያም ብቻ ሳይሆን ላባችንን አንጠፍጥፈን ደማችንንም አፍስሰን የመጨረሻው ምእራፍ ላይ አድርሰነዋል። ዛሬ የምሥራች ፍሬውን ቀማምሰናል፤ ነገ ደግሞ ተዝቆ ከማያልቀው በረከቱ ጠግበን ለጎረቤቶቻችንም በመትረፍ እጅ ለእጅ ተያይዘን ለምንገነባት ዘመናዊዋ ዓለም በጋራ እንጠቀምበታለን።
ፍሰሀ ጌታቸው
አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም