
የኢትዮጵያ የአመጋገብ ባህል የተወሰኑ የምግብ አይነቶች ላይ ያተኮረ በመሆኑ ሕፃናት መቀንጨር፤ መቀጨጭ እያጋጠመ ነው፤ በመቀንጨር ምክንያትም ሀገሪቱ በዓመት 55 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር እያጣች ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይፋ ባደረገው የአመጋገብ ሥርዓት በአንድ የምግብ ማዕድ ላይ አራት የምግብ ምድብ መገኘት አለበት፤ ሳይንሱ የሰው ልጅ በቀን ስድስት የምግብ ምድቦችን በመጠኑ መመገብ አለበት ቢልም በኢትዮጵያ በኢኮኖሚና በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እየተመገቡ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡
የተመጣጠነ ምግብ ዜጎች አለመመገባቸው፤ ሕፃናትን ለቅንጨራና ለቅጨጫ ሲያጋልጥ 67 በመቶ የሚሆነው አምራች ኃይል ደግሞ በአካልና በአዕምሮ የቀነጨረ እንዲሆን ማድረጉን አመላክቷል፤ የመቀንጨሩ ማሳያም የትምህርት አቀባበሉ ዝቀተኛ፤ ቴክኖሎጂን የመላመድ ባህሉ አነስተኛና በክስተቶች ምክንያታዊ ያልሆነ መሆኑ ማሳያ ነው፡፡
መጋቢት14 ቀን 2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የጤና ሚኒስቴር ከተባባሪ አካላት ጋር ባከናወኑት የምግብና ሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂ መነሻ ዳሰሳ ጥናት፣ በሁሉም ክልሎች ዝቅተኛ የምርት ስብጥር በመኖሩ ሕፃናት የመቀንጨር ምጣኔ እ.ኤ.አ. በ2016 ዓ.ም ድረስ ከነበረው ብዙም ለውጥ አላሳየም ይላል፡፡
ባልተስተካከለ የአመጋገብ ሥርዓት ምክንያት ከአምስት ዓመት በታች ከሚገኙ ሕፃናት ውስጥ 39 በመቶው መቀንጨር አጋጥሟቸዋል፤ 11 በመቶ የሚሆኑት ካላቸው ቁመት ጋር የሚመጣጠን ክብደት የላቸውም፤ 22 በመቶ የሚሆኑት በዕድሜያቸው ሊኖራቸው የሚገባ ክብደት እንደሌላቸው በጥናቱ ተቀምጧል፡፡
ስድስት በመቶ የሚሆኑ ሕፃናት ሰውነት ከሚያስፈልገው በላይ ምግብ በመመገብ በዕድሜያቸው ሊኖራቸው ከሚገባ ክብደት በላይ ማስመዝገባቸውንም በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
በሁሉም ክልሎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ለአካለ መጠን የደረሱ ሴቶች፣ በወጣትነትና በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጃገረዶችና ሕፃናት የንጥረ ምግቦች እጥረት ተጎጂ ናቸው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከአምስት ዓመት በታች ከሚገኙ ሕፃናት ግማሽ ያህሉ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጎዱ ሲሆኑ፤ ከተጉዱትም ውስጥ 43 በመቶ የሚሆኑት በገጠር፤ 29 በመቶ የሚሆኑት በከተማ ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች የተመጣጠነ ምግብ ያለማግኘት ምጣኔ የተለያየ ነው፤ የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘት የመቀንጨር መጠን በአፋር 42 በመቶ፣ በኦሮሚያ 41 በመቶ፣ በአማራ 40 በመቶ፣ በደቡብ 40 በመቶ መሆኑን በጥናቱ ተዳሷል፡፡
በሀገሪቱ ለአቅመ አዳም ከደረሱ ሴቶች ውስጥ 19 በመቶ የሚሆኑት መመዘን የሚገባቸው ከክብደት በታች ናቸው። ከክብደት በታች ከሆኑ 19 በመቶ ውስጥ 22 በመቶ የሚሆኑት በገጠር፣ 15 በመቶ የሚሆኑት በከተማ የሚኖሩ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ከስድስት እስከ 23 ወራት ከሚገኙ ሕፃናት ውስጥ 47 በመቶ የሚሆኑት ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ሲሆኑ፤ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ካጋጠማቸው 47 በመቶ ውስጥ 75 በመቶ በሶማሌ፣ 53 በመቶ በደቡብ፣ 50 በመቶ በጋምቤላ የሚገኙ ናቸው፡፡ 45 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ መካከለኛ የምግብ እጥረት አለባቸው፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ነሐሴ 9/2016 ዓ.ም የሰቆጣን ቃል ኪዳን ስምምነትና የማስፋፊያ ምዕራፍ ስትራቴጂ ትግበራና የቀጣይ እቅዶችን በተመለከተ በተካሄደው ውይይት ላይ እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ ከሁለት ዓመት በታች የሚገኙ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሕፃናት መቀንጨር ላይ ይገኛሉ፡፡
በተመሳሳይ ቀን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ በኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በታች የቀነጨሩ 39 በመቶ፤ የቀጨጩ 11 በመቶ ሕፃናት አሉ፡፡
በጤና ሚኒስቴር የሥርዓተ ምግብ ባለሙያ ወይዘሮ ቤዛዊት ወርቁ በሰጡት አስተያየት፤የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የአመጋገብ ሥርዓት ኃይልና ሙቀት ሰጪ እንዲሁም ጣፋጭ ምግቦች ላይ ያተኮረ ነው፤ይህም የአመጋገብ ሥርዓት ለአላስፈላጊ ውፍረት እየዳረገ ነው፡፡
በከተማ ማህበረሰብ ዘንድ ጣፋጭ፣ ኃይልና ሙቀት ሰጪ ምግቦችን ሕፃናት እየተመገቡ ለአላስፈላጊ ውፍረት እየተጋለጡ ነው ብለዋል፡፡ ማህበረሰቡ የተመጣጠነ ምግብ ማለትም ኃይልና ሙቀት ሰጪ፤ ገንቢ፤ በሽታ ተከላካይ፣ ቅባትና ማዕድናት የያዘ የአመጋገብ ሥርዓት የለውም፤ በተለይ አትክልትና ፍራፍሬን የመጠቀም ባህሉ ዝቀተኛ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው ለቅንጨራና ለቀጫጫነት እየተጋለጡ ነው፤ የሕፃናትን መቀንጨርና መቀጨጭን ለመከላከል የተመጣጠነ ምግብ አልባ የሆነውን የአመጋገብ ሥርዓትን ማስወገድ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡
የተመጣጠነ ምግብ የመመገብ ሥርዓትን ማዳበር የተስተካከለ ጤና፤ አቋም፤ ፈጣን የትምህርት አቀባበልና የቴክኖሎጂ አቀባበል፤ በቀላሉ ለበሽታ የማይጋለጥና ቢጠቃም በህክምና ቶሎ የሚያገግም አካል እንዲኖር ያደርጋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የሥርዓተ ምግብ ባለሙያ ቢራራ መለሰ በበኩላቸው፤ የሀገሪቱ የአመጋገብ ባህል የተወሰኑ ምግቦች ላይ የተዛመደ ነው፤ አትክልትና ፍራፍሬን የመጠቀም ባህል ዝቅተኛ ነው፡፡
በአንድ የምግብ ማዕድ አራት የምግብ ምድቦች፤ በቀን ስድስት የምግብ አይነቶች አስፈላጊ ናቸው፤ዜጎች ግን በኢኮኖሚና በግንዛቤ እጥረት የተመጣጠነ ምግብ እየተመገቡ አይደለም፤ ባለመመገብም የአካልና የአዕምሮ መቀንጨር ምክንያታዊ አልባ ትውልድ እየተፈጠረ ነው ይላሉ፡፡
አንድ ሰው በቀን ስድስት የምግብ ምድቦችን ማለትም የኃይልና ሙቀት ሰጪ፤ በሽታ ተከላካይ፣ ገንቢ፣ ማዕድን፣ ቅባት ምግቦችን በመጠኑ ማግኘት አለበት ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
እአአ አቆጣጠር በ2023 ዓ.ም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባደረገው ጥናት፤ በሀገሪቱ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ 39 በመቶ የሚሆኑት የቀነጨሩ፤ 22 በመቶዎች እድገታቸው ከሚጠበቀው በታች፤ 11 በመቶ የአጭር ጊዜ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ናቸው፤ ስድስት በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የምግብ አቅርቦት አግኝተው ከልክ በላይ በመመገብ ለአላስፈላጊ ውፍረትና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የተጋለጡ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ ባለመመገባቸው 67 በመቶ የሆነውን አምራች ወጣት በአካልና በአዕምሮ እንዲቀነጭር አድርጎታል፤ ትምህርትን በፍጥነት የሚቀበል፤ ፈጠራን አስፋፍቶ ችግር የሚፈታ፤ ቴክኖሎጂን በቶሎ የሚላመድና በክስተቶችና በነገሮች ምክንያታዊ የሆነ ወጣት ለማፍራት አመጋገብ ሥርዓትን ማመጣጠን እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡
ሀገሪቱ የአመጋገብ ሥርዓት አለመስተካከል በሚደርስ መቀንጨር ምክንያት 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ታጣለች፤ በመቀንጨር ምክንያት የምታጣውን 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለማዳን፤ አምራች ዜጋዋን ሙሉ አቅም ተጠቅማ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተመጣጠነ ምግብ የመመገብ ባህልን ማዳበር ተገቢ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡
የተመጣጠነ የምግብ ሥርዓት የተስተካከለ አቋም፣ ጤናማ አካል፣ በሽታን የሚከላከልና ከበሽታ ቶሎ የሚያገግም፤ ትምህርትን፤ ቴክኖሎጂን በፍጥነት የሚቀበልና የሚላመድ፣ የፈጠራ ሥራ የሚሠራ፤ ሀገርንና ሕዝብን በሥነ ምግባር የሚያስተዳድር ዜጋ ለመፍጠር ትልቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡
የተመጣጠነ ምግብ ብቻውን አካላዊ፣ አዕምሮዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማምጣት አይችልም፤ አካላዊ እንቅስቃሴ መስራት ተገቢ ነው ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም