ከፓራሊምፒክ ጀግኖቹ አንደበት

ከቀናት በፊት የተጠናቀቀው የፓሪስ 2024 ፓራሊምፒክ በኢትደዮጵያ የፓሪሊምፒክ ዓለም አቀፍ ተሳትፎ ታሪክ በውጤታማነት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ኢትዮጵያን ፓሪስ ላይ የወከለው ቡድን በአራት አትሌቶች ተሳትፎ ሶስት ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብም በኦሊምፒክ ውጤት ለተከፋውን ሕዝብ ክሳል። በዚህም የፓራሊምፒክ ቡድኑ ወደ ከትናንት በስቲያ ሃገሩ ሲመለስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

ቡድኑ ከትናንት በስቲያ ንጋት ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ሲደርስ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል። በ17ኛው የፓሪክ ፓራሊምፒክ ተሳታፊ የነበረው ቡድን ሁለት አሯሯጮችን ጨምሮ በስድስት አትሌቶች ተሳትፎ ሁለት የወርቅና አንድ የብር በጥቅሉ ሶስት ሜዳሊያ እንዲሁም ዲፕሎማ በማስመዝገብ መመለሱ ይታወሳል።

በ1ሺ500 ሜትር (ሙሉ በሙሉ ዓይነ ስውራን) የዓለም ክብረ ወሰንን 4፡27.68 በሆነ ሰዓት በመስበር አሸናፊ የሆነችው አትሌት ያየሽ ጌቴ፣ በተገኘው ውጤት ኩራትና ደስታ የተሰማት መሆኑን በአቀባበሉ ወቅት ተናግራለች። ውድድሩ ከባድ ቢሆንም ወደ ፓሪስ ከመሄዷ አስቀድሞም የወርቅ ሜዳሊያውን ለማሳካት እና ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ ማለሟ ውድድሩ ላይ የነበረውን ሁኔታ እንድትቋቋም አድርጓታል። በቀጣይም በዚሁ ስኬት ለመቀጠል እንዲሁም የምትሳተፍባቸውን ርቀቶች የመጨመር ፍላጎት ያላት ሲሆን፤ ለዚህም ጠንክራ እንደምትሰራ ገልፃለች። የፓራሊምፒክ ክለቦች እንደ ሃገር ቢቋቋሙ ደግሞ እሷን መሰል በርካታ ውጤታማ አትሌቶችን ለማፍራት እንደሚቻልም ጠቁማለች።

በኢትዮጵያ የፓራሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በቶኪዮ ፓራሊምፒክ ላይ ያስመዘገበችው አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ደግሞ፣ ፓሪስ ላይም ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ማሳካቷ ይታወቃል። በ1ሺ500 ሜትር ጭላንጭል የተካፈለችው አትሌቷ በተከታታይ አሸናፊ ለመሆኗ በመድረኩ ያዳበረችው ልምድ የጠቀማት መሆኑን በማንሳት መደሰቷን ትናገራለች። ‹‹በተከታታይ የፓራሊምፒክ መድረኮች የወርቅ ሜዳሊያ መመዝገቡ እንዲሁም ቁጥሩ መጨመሩ በስፖርቱ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው›› በማለትም በዚህ አቋም በተለያዩ ውድድሮች ተሳትፋ ሃገሯን ለማስጠራት ጠንክራ እንደምትሰራ ቃል ገብታለች።

በተመሳሳይ ርቀት በወንዶች ጭላንጭል ደግሞ አትሌት ይታያል ስለሺ የብር ሜዳሊያ ሊያስመዘግብ ችሏል። አትሌቱ በውድድሩ ውጤታማ ለመሆን በዝግጅት ላይ ሳለ ጉዳት ቢገጥመውም በዚህ ሳይረታ ሃገሩን ሊወክል ችሏል። እጅግ ፈታኝ በነበረው ውድድር አሸናፊ የሆነው ብራዚላዊ አትሌት ልምድ ያለው መሆኑ ክብረወሰን እስከማሻሻል ያደረሰው ሲሆን፤ በመድረኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈው ይታያል ሁለተኛ ደረጃን እንዲይዝ አድርጎታል። ይህንን ልምድ ተመርኩዞም በቀጣይ ለሚኖሩት ውድድሮች ጠንካራና በሁለት ርቀቶች የሚሳተፍ አትሌት ለመሆን ጥረት ያደርጋል። ለአካል ጉዳተኛ ስፖርተኞች የሚደረገው ድጋፍ አሁንም አነስተኛ መሆኑን የሚጠቁመው አትሌቱ በፓሪስ የተካፈሉት አሌቶች አራት ብቻ ቢሆኑም የተገኘው ውጤት ስኬታማ ሊባል የሚችል ነው።

ነገር ግን እንደ ሌላው ሃገር በርካታ አትሌቶችን ማሰለፍ ቢቻል ተጨማሪ ውጤት ማግኘት ይቻላል። ሌሎች ዓለም አቀፍ የፓራሊምፒክ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ በመሆን ልምድ ለማዳበርም አቅም የሚያስፈልግ በመሆኑ ስፖርቱ ትኩረት ያስፈልገዋል። እአአ በ2028 ለሚደረገው ፓራሊምፒክም ከአሁኑ መስራት እንደሚገባ የሚጠቁመው አትሌቱ፤ አቅመ ያላቸው ተቋማት ክለቦች ሊመሰረቱና አትሌቶችን ሊይዙ እንደሚገባም አስገንዝቧል። ይህ ከሆነም በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ በዓለም ደግሞ ተፎካካሪ ለመሆን እንደሚቻልም አክሏል።

ለቡድኑ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው ‹‹ባመጣችሁት ውጤት ኮርተናል፣ በዓለም አደባባይ ሰንደቃችን እንዲውለበለብ፣ ገጽታችን እንዲገነባ እንዲሁም ስማችን በተደጋጋሚ እንዲጠራ ስላደረጋችሁ እናመሰግናለን። በዓለም አቀፍ ከዚህ ቀደም ከነበረው የፓራሊምፒክ ደረጃ የተሻለ ውጤት የተመዘገበ በመሆኑ እንደ መንግስት አካል ጉዳተኞችን በስፖርት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የፖሊሲ አቅጣጫ አስቀምጦ በርካታ ስራ እየተከናወነ ይገኛል። ቡድኑ ሲጓዝም ድጋፍ ተደርጓል ወደፊትም በአትሌቲክስ ብቻም ሳይሆን በሌሎች ስፖርቶችም ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በልዩ ሁኔታ ድጋፍ የምናደርግ ይሆናል። በቀጣይም በድል ለተመለሰው ቡድንን የሚመጥን ዕውቅና እና ሽልማት እናዘጋጃለን›› ብለዋል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You