በሞቃዲሾ የተዘረጉት የካይሮ የጥፋት እጆችን ለመቁረጥ …!

ኢትዮጵያውያን በረጅም ዘመን ታሪካቸው በርካታ ጠላቶችንና ወዳጆችን አስተናግደዋል። ከጎረቤት ሆነ ከሌሎች ሀገራት እና ሕዝቦች ጋር ያላት ግንኙነት ወንድማማችነትን፣ መከባበርን እና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ እንደሆነም ታሪክ ይመሰክራል። ለጎረቤት ሀገራት ችግር ቀድሞ መድረስ፤ የሌሎችን ችግር የራስ አድርጎ መመልከት በታሪካቸው ከሚታወቁበት አንዱ መገለጫቸው ነው።

ይህ ሀገራዊ እሴት ድንበር በሚሻገረው ሀገራዊ የግንኙነት ምዕራፍም ጎልቶ የሚታይ ነው። በሌሎች ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ታሪክ የሌላቸው ከዚህ ይልቅ፣ በገለልተኝነት እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በተመሰረተ የግንኙነት መርሕ የሚታወቁ ናቸው። ይህም የታሪካችን ሌላው ገጽታ ነው።

ይህም ሆኖ ግን ይህችን ታላቅ አገር ታሪኳን ለማንኳሰስ እና ለማፍረስ ዛሬም ድረስ ሙከራዎችን ያደርጋሉ። በአንድ ወቅት ወዳጅ የሆኑ በሌላ ወቅት የታሪካዊ ጠላቶቻችን መሳሪያ በመሆን ጠላት የሚሆኑበት ክስተትም የተለመደ ነው። በጠላትነታቸውም ጥርሳቸውን ነክሰው በታሪካችን እንደ ጥላ የሚከተሉን ሀይሎች አሉ።

እነዚህ ሀይሎች ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶች አልምታ እንዳትበለጽግ ፣ እንዳታድግ ሁሌም ፈተና ናቸው። በተለይ ደግሞ ግብፅ ጊዜና ዘመን ሊሽረው በማይችል ጠላትነት፤ እንደሀገር ያለንም የመልማት ትልም ለማክሸፍ ሌት ተቀን ያለእንቅልፍ ውሎ የሚያድሩ የለም።

ግብጽ እንድትኖር ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር መጥፋት ወይም መፍረስ አለባት ብለው የሚያምኑ፤ ሁልም የሀገሪቱን የመልማት አጀንዳ የውስጥ ፖለቲካ አካል አድርገው የሚያቀርቡ ፖለቲከኞች ያሉባት ሀገር ነች፡፡ ታሪኩ ሰፊና ረጅም ቢሆንም ግብጽ በተለያዩ ዘመናት በኢትዮጵያ ላይ ያላሴረችው፤ ያልሰራችው ደባና ተንኮል የለም፡፡

በጥንቱ ዘመን ግብጽ ሠራዊትዋን ወደ ኢትዮጵያ አዝምታ የአባይን ውሃ ከምንጩ ለመቆጣጠር ባደረገችው ጦርነት በኢትዮጵያውያን ጀግኖች የውጊያ የበላይነት ጉንዳና ጉራእ ላይ አሳፍራ ስለመመለሷ የታሪክ ማህደራት ያትታሉ፡፡

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንዳትሰራ አገሪቱን አቅም በማሳጣት ትኩረቷን ለልማትና ዕድገት እንዳታደርግ፣ በሀገሪቱ ውስጥ የተረጋጋ ሰላም ልማትና ዕድገት እንዳይኖር ቀውስና ትርምስ መፍጠርን አጀንዳዋ አድርጋ ለዘመናት ስትሰራ ቆይታለች።

በሀገሪቱ ወደ ሥልጣን የሚመጡ መንግሥታት የወንዙን ውሃ ባልተፈለገ መንገድ የፖለቲካ አጀንዳ በማድረግ፤ በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ሊኖራቸው የሚችለውን ዘላቂ የጋራ ተጠቃሚነት ዕድል ትርጉም ወደሌለው የጠላትነት እና የግጭት መነሻ ለማድረግ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተንቀሳቅሰዋል። ለአብነት ያህል የቀድሞ የግብዕ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት “የአባይን የውሃ ፍሰት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውም ተግባር ግብፅን ወደ ጦርነት የሚያስገባና ጠንካራ አፀፋዊ እርምጃን የሚጠይቅ ይሆናል’’ ብለዋል ።

በሕዝብ አመፅ ከስልጣናቸው በኃይል የተባረሩት ሆስኒ ሙባረክም በአባይ ተፋሰስ ላይ የሚሰራን ማንኛውንም ልማት እንደሚያወድሙት በተደጋጋሚ ሲዝት ነበር ፡፡ ይህ የጦርነት ጉሰማ ዛሬም ላይ ቀጥሏል። ግብፅን እየመራ ያለው የአልሲሲ መንግስት ያለፉትን የግብጽ መሪዎች መፈክር ከማስተጋባት አልተቆጠበም፡፡ የኢትዮጵያን በራሷ የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብት ለመገደብና በትብብርና በመተሳሳብ ማደግን ለማደናቀፍ በተለመደው መንገድ እየተንቀሳቀሰ ነው። የካይሮ መሪዎች ምኞታቸው አይሳካም እንጂ በኛ ጉዳይ መቸም ተኝተው የሚያድሩ አይደሉም ።

ኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ ያለፈችባቸው አባጣና ጎርባጣ የበዛባቸው መንገዶች ከፍተኛ ዋጋ እንድትከፍል ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ከእያንዳንዱ ፈተና በስተጀርባ በግልጽም ይሁን በስውር የሚስተዋሉ እጆች ፤ በአንድም ይሁን በሌላ ወንዙን የማልማት ጅማሮ እንዳይሳካ ከማድረግ ፍላጎት ጋር የተያያዙ ነበሩ ።

በግብፅ በኩል በባለሥልጣናት፣ በባለሙያዎችና በሚዲያዎች ትብብር የተከፈተው ዘመቻ ዓለም አቀፍ ገጽታ እንዲላበስ ተደርጎም ነበር፡፡ ይሄው ዘመቻ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መልኩን ቀይሮ አሁን ላይ አደባባ እያጣበበ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት በተፈራረመች ማግሥት ከሶማሊያ መንግሥት በተቃውሞ የታጀበ ጩኸት ተከትሎ፤ ጩኸቱን በማስተጋባት ከመጀመሪያው ረድፍ የተሰለፈጭው ግብፅ ነች፡፡

ግብፅ በዚህ ሳታበቃ የአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ሰላም አስከባሪ ተልዕኮን (አትሚስ) ተገን አድርጋ ሞቃዲሾ ደርሳለች፡፡ ሶማሊያ ግብፅ በዓባይ ተፋሰስ ላይ ማሳካት የምትሻውን የዘመናት ቅዠቷን ለማሳካት አጋጣሚውን እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ወዲህ ወዲያ ያለች ነው።

በርግጥ እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ልካ የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር እየከፈለች ለሶማሊያ ሰላም፣ አንድነትና መረጋጋት ስትሠራ መቆየቷ ይታወቃል። ሶማሊያ ዛሬ እንደ ሀገር እንድትቆም የኢትዮጵያ ወታደር ብዙ ዋጋ ከፍሏል።

የሶማሊያ ባለስልጣናት አሁን ላይ የግብጽ ጦር በሶማሊያ እንዲሰማራ ከስምምነት መድረሳቸው “የናይል ጉዳይ” ወደ ሶማሊያ የሚያመጣ እና “በአፍሪካ ቀንድ ላይ አለመረጋጋት ሊያመጣ የሚችል” እንደሆነ የተረዱት አይመስልም። ቢያውቁትም ችግሩን አሻግረው ማየት ተስኗቸዋል። ችግሩ በአልሸባብ ፍዳውን ሲበላ የቆየውን የሶማሊያ ሕዝብን ዳግም ወደ ነበረበት መከራ የሚመልስ ነው።

የችግሩን ስፋት እና አደጋ የተረዱት፤ በሶማሊያ የምክር ቤት አባል እና የፕሬዚዳንቱ ልዩ ልዑክ የነበሩት የፓርላማ አባል አብዲረሺድ ሞሃመድ ኑር ጂሌይ ጭምር “የአገሪቱ አመራር ሕዝቡን ወደ ግጭት እና ጦርነት ሊያስገባ አይገባም። የሚቃረኑ አገራት እንዲዋጉ ግዛታችን ውስጥ ማስገባት የሚመከር አይደለም” ሲሉም ተደምጠዋል። ከኢትዮጵያ ችግር ጀርባ የማትጠፋው ግብጽ ዛሬም እንደለመደችው ሶማሊያን መጠቀሚያ ለማድረግ እያደረገችው ያለው ሙከራን ጥሩ አለመሆኑን መክረዋል።

በኢትዮ- ሶማሊያ 1969 እስከ 1970 ጦርነት ጀርባ የግብጽ እጅ እንደነበረ ይታወቃል ። ለሶማሊያ ጦር ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራት የታሪክ መዛግብት የሚያመለክቱት ነው። ችግሩ በሶማሊያ የፈጠረው መንግሥት አልባነት እንደ አልሸባብ እና አይ ኤስ ኤስ የመሳሰሉ ጽንፈኝ እና አሸባሪ ኃይሎች በአካባቢው በስፋት እንዲንቀሳቀሱ አመቻችቷል ። ከአካባቢው አልፈው ለዓለም ስጋት እንዲሆኑ አድርጓል። በቀጣናው ዘላቂ ሠላም ለማምጣት የሚደረገውን አህጉራዊ ሆነ ዓለም አቀፍ ጥረት ፈትኗል ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ለሶማሊያ ሕዝብ ካለው ቅርበት /ወንድምነት/ የተነሳም ዓለም አቀፍ፤ አህጉራዊ እና አካባቢያዊ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎችን ወስዶ ሕዝቡ ከጽንፈኛ እና ሽብርተኛ ቡድኖች የሚደርስበት ፈተና ለማቅለል፤ የተሻለ የሠላም አየር እንዲተነፍስ ለማስቻል ብዙ መስዋዕትነት የጠየቁ ወታደራዊ ተልዕኮዎችን ወስዶ በስኬት ተወጥቷል ።

በአሁናዊ ጉዳይ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ፤ “ኢትዮጵያ በንጉሱ እና በደርግ የአስተዳደር ጊዜ በሶማሊያ የደረሰባትን ወረራ አትረሳም፣ ሕዝቦቿም ተላላ አይደሉም ብለዋል። አምባሳደሩ እንዳረጋገጡት ፣ የሶማሊያ ሰላም እኛን ይመለከታል፣ ሰላም እንዲመጣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መስዋዕትነት ከፍሏል ። አሁንም የሶማሊያ ሁኔታ የሚያሳስበን ድንበር ዘሎ የሚመጣ ትርምስን ስለማንፈልግ ነው።

ይህም ሆኖ ግን ግብጽ በአዲሱ የውጭ ጉዳይ እና የመስኖ ሚኒስትሩ ዶ/ር ባዳረ አብዱላቲ በኩል ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ “ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ባለችው ግድብ ምክንያት የውሃ ደኅንነቴን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ መብት አለኝ አለች “ ስትል እንደተለመደው የጦርነት ዲቤ እያሰማች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ባስመዘገበችው ታሪክ የውጭ ችግር ሲያጋጥማት ሕዝቦቿ በጋራ መመከት የተለመደ መሆኑ ይታወቃል። አሁንም በሞቃዲሾ የተዘረጉት የካይሮ የጥፋት እጆችን ለመመከት ካይሮ የአባይ ወንዝ ድብቅ አጀንዳ አንግባ በወታደራዊ ስምምነትና ከበባ፣ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በማቃቃር፣ በዓለም አቀፍ ክስና እሩጫ የሚቀየር አቋም አይኖርም። እንዲያውም በቅርቡም የግድቡ ግንባታ “ሪቫን “ መቆረጡ የሚጠበቅ ነው።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሦስተኛውና አራተኛው ተርባይኖች ሥራ መጀመራቸው አብስረዋል። የዓባይ ወንዝ ፍሰቱ ሳይስተጓጎል መቀጠሉንና የግድቡ ማስተንፈሻ በሮች ተከፍተው በሰከንድ ተጨማሪ 2 ሺህ 800 ሜትር ኪዩብ ውኃ መፍሰስ መጀመሩ የፍፃሜውን መቃረብ ይጠቁማል።

በርግጥ በሀገሩ ሉአላዊነት ላይ የማይደራደረው ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ጉዳዩን በንቃት እየተከታተለ ስለመሆኑ ብዙ ማለት አያስፈልግም። በብዙ ጩኸት መካከል ዓባይን መገደብና ሃይል ማመንጨት እንደቻልነው ሁሉ የባሕር በር ፍላጎታችንንም ብሔራዊ ጥቅማችንን ሳይጎዳ እንደምናሳካ እምነቴ ነው ። ለዚህ ደግሞ እስካሁን ያለን ሀገራዊ ዝግጁነት በቂ እና ከበቂ በላይ ነው።

ዳንኤል  ዘነበ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You