ስፖርት ባለፈው የውድድር ዓመት

ትናንት የባተው 2016 ዓ.ም በስፖርቱ ዓለም በርካታ ጉዳዮች የታዩበትና የተስተናገዱበት ሆኖ አልፏል። የኢትዮጵያ ስፖርትም ከሃገር እስከ ዓለም አቀፍ መድረኮች በበርካታ ክስተቶች አልፏል። በውድድር ዓመቱ አንኳር የነበሩ ስፖርታዊ ጉዳዮችም እንደሚከተለው ይዳሰሳሉ።

አትሌቲክስ

ከቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ማግስት የተያዘው የ2016 ውድድር ዓመት ጅማሬውን ያደረገው በአትሌቲክስ ስፖርት በተለያዩ ርቀቶች በተሰበሩ ሦስት የዓለም ክብረወሰኖች ነበር። የአዲሱ ዓመት ገጸበረከት የተባለው የሴቶች የ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ለወራት ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች እጅ ወጥቶ ከቆየ በኋላ በአትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ዳግም ወደ ሃገሩ ሊመለስ ችሏል። ጀግናዋ አትሌት በዓለም ቻምፒዮና የ10ሺ ሜትር ድልን በተጎናጸፈች የቀናት ልዩነት በዳይመንድ ሊጉ የመጨረሻ መዳረሻ ኦሪጎን ሰዓቱን በአምስት ሰከንዶች (14:00.21) ማሻሻል ችላለች።

ከቀናት በኋላ ደግሞ የዓለም ክብረወሰን በተደጋጋሚ በሚሰበርበትና በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ በተሰጠው የበርሊን ማራቶን አትሌት ትዕግስት አሰፋ የማራቶን የዓለም ክብረወሰንን ያሻሻለች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሆናለች። አትሌቷ በርቀቱ የዓለም ቀዳሚዋ አትሌት ለመሆን የቻለችውም ባስመዘገበችው 2:11:53 የሆነ ሰዓት ሲሆን፤ ከረጅም ጊዜ የሕክምና ክትትል በኋላ ዳግም ወደ ውድድር ተመልሳ ስኬታማ መሆኗ የጽናት ተምሳሌት ያደርጋታል። ከሳምንታት በኋላ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በሪጋ በተካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሶስተኛው የዓለም ክብረወሰን በአትሌት ድርቤ ወልተጂ ሊሰበር ችሏል። በቡዳፔስቱ የዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ያጠለቀችው ወጣቷ አትሌት በ1 ማይል የጎዳና ሩጫ 4:20.98 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ ታሪክ ሰርታለች።

ዓመቱ ኢትዮጵያ ዝናን ባተረፈችበት የአትሌቲክስ ስፖርት ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የተወከለችበትም ነበር። በየዓለም የጎዳና ላይ አትሌቲክስ ቻምፒዮና የጀመረው 2016፤ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና፣ የአፍሪካ ቻምፒዮና፣ የአፍሪካ ጨዋታዎች፣ የዓለም ሃገር አቋራጭ ቻምፒዮና፣ ኦሊምፒክን እንዲሁም የዓለም ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና የተከናወኑበት ነበር። ኢትዮጵያን በነዚህ መድረኮች የወከሉ አትሌቶችም በርካታ ሜዳሊያዎች በማስመዝገብ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ አኩርተዋል።

ኦሊምፒክ

የዓመቱ ታላቁ ውድድር የ2024 ፓሪስ ኦሊምፒክ ሲሆን ባልተጠበቀ ሁኔታ ኢትዮጵያ በተቀዛቀዘ ውጤት ነበር ያጠናቀቀችው። ኢትዮጵያ 1 የወርቅ እና 3 የብር በአጠቃላይ 4 ሜዳሊያዎችን በፓሪስ ኦሊምፒክ አስመዝግባ ከዓለም 47ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 4ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀችው። ይኸውም የስፖርት ቤተሰቡን በእጅጉ ያስቆጣ ውጤት ሊሆን ችሏል። ከዚሁ ኦሊምፒክ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ እሰጣ ገባ እንዲሁም አለመግባት የተነሳው በተጠናቀቀው ዓመት ነበር። ከውጤት እጦትና የአትሌቶች ምርጫ ጋር በተያያዘ ብዙ ውዝግቦች ታይተዋል። በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሕገወጥ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ እንዲሁም አሰራሮች ቀጥሎ በሃገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራት ክስ ዓመቱ ሊጠናቀቅ ችሏል።

ታሪክ ሰሪው የፓራሊምፒክ ቡድን

በፓሪስ 2024 ፓራሊምፒክ የኢትዮጵያ ቡድን በ4 ውድድሮች ላይ ተሳትፎ 2 ወርቅ፣ አንድ የብር ሜዳሊያ እና 1 ዲፕሎማ በማስመዝገብ ትልቅ ታሪክ በመስራት ከዓለም 27ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 2ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል። ይህም በኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ተሳትፎ ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ ውጤት የተመዘገበበትና ታሪክ የተሰራበት ያደርገዋል። አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ በሴቶች 1500 ሜትር አይነስውራን ጭላንጭል የወርቅ ሜዳሊያ ስታስመዘግብ፣ በሴቶች 1500 ሜትር T11 ሙሉ በሙሉ ዐይነ ሥውራን አትሌት ያየሽ ጌቴ በራሷ የተያዘውን የዓለም ክብረወሠን በመስበር ጭምር የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፋለች። በአይነስውራን ሙሉ በሙሉ (T 11) ምድብ 1500 ሜትር ደግሞ ይታያል ስለሺ የብር ሜዳሊያ አጥልቋል። በወንዶች T46 የእጅ ጉዳት የ1500 ውድድር አትሌት ገመቹ አመኑ 7ኛ በማጠናቀቅ የዲፕሎማ ባለቤት ሆኗል።

እግር ኳስ

ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) የአሰልጣኝ ውበቱ አባተን ስንብት ተከትሎ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በድጋሚ የተሾሙበት ዓመትም ነበር 2016። የቀድሞው የዋሊያዎቹ አለቃ ስራቸውን የጀመሩትም እአአ በ2026ቱ ዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ነበር። ቡድኑ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካ ተጉዞ ከጉያና ብሄራዊ ቡድን እንዲሁም ከአትላንታ ሮቨርስ ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎችን ማድረግም ችሏል። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡናም በተመሳሳይ የሸገር ደርቢ ጨዋታቸውን ከቀናት በፊት በዋሽንግተን ዲሲ አውዲ ፊልድ ስታዲየም አከናውነዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2016 ዓ.ም የውድድር ዘመን በሁለቱም ጾታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እግር ኳስ ክለብ አሸናፊነት ተጠናቋል። ይህንንም ተከትሎ በሴቶች በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በተደረገው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች (ሴካፋ) ቻምፒዮና ንግድ ባንክ አሸንፏል። በዚህም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በሚዘጋጀው የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ምስራቅ አፍሪካን እንደሚወክል አረጋግጧል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋቿ ሎዛ አበራ ወደ ሰሜን አሜሪካ ማራውደርስ ቨርጂኒያ ክለብን መቀላቀሏ የሚታወስ ነው። የምንጊዜም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዋ አጥቂ ሎዛ ቀጣይ መዳረሻዋን ዲሲ ፖወር ክለብ ማድረጓም በዓመቱ ከተሰሙ የምስራቾች መካከል ነው።

ቦክስ

በውድድር ዓመቱ የተሻለ እንቅስቃሴ ከነበራቸው የስፖርት ማህበራት መካከል አንዱ የሆነው የቦክስ ስፖርት ነው። በዓለም አቀፍ ውድድሮች የተሻለ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን፤ በአፍሪካ የቦክስ ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ባለቤቱ ፍቅረማርያም ያደሳ፤ ምንም እንኳን ተሳታፊ ሊሆን ባይችልም እስከ ፓሪስ ኦሊምፒክ የሚዘልቅበት ዕድል ተገኝቶ ነበር።

በዓመቱ በተካሄደው የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ እያሱ ወሰን አሸንፈው አህጉር አቀፍ ፕሬዚዳንት የሆኑትም በዚሁ ዓመት ነው። ይህንንም ተከትሎ የኮንፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት መቀመጫውን አዲስ አበባ ላይ ሊያደርግ ችሏል። በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ፕሮፌሽናል የቦክስ ውድድሮችም በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂደዋል። እነሱም ኢንተርናሽናል እና ሰሚ ፕሮፌሽናል ውድድር እንዲሁም በዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር የሚመራውና በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ፕሮፌሽናል የቦክስ ቻምፒዮና ምሽት ናቸው።

ስፖርትና ቱሪዝም

ከዓለም ተወዳጅ የጎዳና ሩጫዎች መካከል አንዱ የሆነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ለ23ኛ ጊዜ 45ሺ ሯጮችን በማሳተፍ ተካሂዷል። ዓለም አቀፍ ይዘት ባለው በዚህ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ በርካታ የውጪ ሃገራት ዜጎች ተሳታፊ ናቸው። ኑሯቸውን ከኢትዮጵያ ውጪ ያደረጉ ዜጎችም ተካፋይ እንዲሆኑ በኢንተርኔት የታገዘ ‹‹Virtual Run›› ተግባራዊ ተደርጓል። በዚህም 200 የሚጠጉ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ተሳትፈዋል።

ዓመቱ ከምንጊዜውም በተሻለ በስፖርት ቱሪዝም በርካታ ስራዎች የተከናወኑበት ነበር። ከእነዚህም መካከል አንዱ በሃገር አቀፍ ደረጃ በተገነቡ የቱሪስት መስህቦች ስፖርታዊ ሁነቶችን ማዘጋጀት ሲሆን፤ በወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ እንዲሁም የብስክሌት ውድድር ተካሂዷል። የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስትር በበኩሉ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመሆን፤ የአትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው በቆጂ፣ በሃዋሳ ሃይቅ ዙርያ እንዲሁም በ40 ምንጭ ከተሞች ስፖርትና ቱሪዝምን መሰረት ያደረጉና በዘርፉ ንቅናቄ መፍጠር የሚችሉ የሩጫ ውድድሮችን አካሂዷል።

አህጉር አቀፍ የፋሽን፣ የቱሪዝም እና ስፖርት ፌስቲቫል በሆነው ሸነን አፍሪካ ፌስቲቫል ላይም ስፖርታዊ ክንውኖች ተካተዋል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) የተሳተፉበት የወዳጅነት ጨዋታ ከቀድሞ አፍሪካዊያን የእግር ኳስ ከዋክብት ጋር ተካሂዷል። በዚህም የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ኑዋንኮ ካኑ፣ ዳንኤል አሞካቺ፣ ታሪቦ ዌስት እንዲሁም በአውሮፓ ሊጎች የተጫወተው ሴኔጋላዊው ሄንሪ ካማራ መገኘታቸው የሚታወስ ነው።

የብሔራዊ ስታዲየም

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ ህልሟን ታሳካበታለች ተብለው ከሚጠበቁ ማዘውተሪያ ስፍራዎች መካከል አንዱ የሆነው ብሔራዊ ስታዲየም ምዕራፍ ሁለት ሎት አንድ ግንባታም በ2016 ዓ.ም ነው የተጀመረው። እአአ የ2029ኙን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረቧ የሚታወስ ነው።

 የስፖርት አበረታች ቅመሞች

የስፖርት አበረታች ቅመሞች በዓመቱ ለኢትዮጵያ ስፖርት አስጊ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ቢሆንም ከ2015 ዓ.ም አንጻር በ50 ከመቶ የቀነሰ ነበር። በተለይ ተጋላጭ የሆነው የአትሌቲክስ ስፖርት በመቶዎች የሚቆጠሩ አትሌቶች የደም እና የሽንት ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 6 (4ቱ በቀጥታ ተጠቃሚ መሆናቸው የተረጋገጠ) አትሌቶች የሕግ ጥሰት መፈጸማቸው ተደርሶበታል። ከዚህ ባለፈ በኢትዮጵያ ጸረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በተቋቋመው ግብረኃይል በተደረጉ 21 ኦፕሬሽኖች 7 ግለሰቦችና ተቋማት፣ 3 የሕክምና ባለሙያዎች (በቀጥታ)፣ 1 አሰልጣኝ፣ 2 የሕክምና ተቋማት እንዲሁም 1 የመድሃኒት መደብር የሕግ ጥሰቱ አካል በመሆናቸው አስተዳደራዊና ሕጋዊ ርምጃ ተወስዶባቸዋል።

የስፖርት ዓለም ሰዎች ስንብት

ዓመቱ በኢትዮጵያ ስፖርት ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ሰዎች የታጡበትም ነበር። ከእነዚህ መካከል ተወዳጁ የስፖርት ጋዜጠኛ፣ ጸሃፊ እና የቀድሞው የእግር ኳስ ተጫዋች ገነነ መኩሪያ ‹‹ሊብሮ›› አንዱ ነው። ታሪክ አዋቂው በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ለስፖርት ቤተሰቡ መረጃ ከመስጠት ባለፈ ኢሃፓና ስፖርት (ከ1እስከ3)፣ ፍትሃዊ የጠጅ ክፍፍል፣ ሊብሮ ኢትዮጵያዊ ስልጠና፣ መኩሪያ፣… የተባሉ መጽሃፍትን ለአንባቢያን አበርክቷል። በዚህም ‹‹ተንቀሳቃሽ ቤተመጽሃፍት›› የሚባል መጠሪያ ያገኘው ገነነ መኩሪያ ጥር 14/2016 የቀብር ስነ ስርዓቱ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ስፖርት ከፍተኛ ተስፋ ከተጣለባቸው ወጣት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው አሰልጣኝ አዘነ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውም ባለፈው ዓመት ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም የባህርዳር ከተማ ተጫዋቹ መጋቢት 17/2016 ዓ.ም ለስፖርት ቤተሰቡ ልብ ሰባሪ የሆነው ሕልፈቱ ተሰምቷል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You