አሮጌውን ዓመት ሸኝተን ዛሬ አዲሱን 2017 ዓመት ተቀብለናል። አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅርና የብልጽግና እንዲሆንልን እየተመኘን በዚህ የአዲስ ዓመት ልዩ እትማችን ኢትዮጵያ በተሰናባቹ ዓመት አቅዳ ካሳካቻቸው መካከል አንዱ በሆነው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ሙሉ ትግበራ ውስጥ መግባት ላይ ያተኮረውን ስራችንን ይዘን ቀርበናል።
ኢትዮጵያ ከአንድ ወር በፊት ወደ ተሟላ ትግበራ ያስገባችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አገሪቷ በተለያዩ መስኮች የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር በመንግስት በኩል በጽኑ ታምኖበታል። ማሻሻያው የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን ለመፍጠር፣ የዘርፎችን ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ስለመሆኑም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም ይናገራሉ።
አካታችና ዘላቂ ዕድገት ያለው ኢኮኖሚን ለመገንባት፣ የመንግሥት ገቢን ለማሳደግ እና በሃገር ውስጥ ምርት ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ የሚኖረው አበርክቶ ጉልህ እንደሆነ የተነገረለት ይህ ማሻሻያ፣ ተግባራዊ መሆን በጀመረ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ባለው ግምገማ መሰረት በታቀደለት አግባብ ተግባራዊ እየሆነ ስለመገኘቱ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የውጭ ምንዛሬ ግብይቱ ከብሔራዊ ባንክ እጅ ወጥቶ በገበያ የሚመራበት ስርዓት ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፤ ይህም በርካታ ፋይዳዎች እያስገኘ ስለመሆኑ እየተገለጸ ነው። ወደ ትግበራው ሲገባ ስጋት እንደሚሆን የተጠበቀውን የምርቶች ዋጋ መናር መንግስት ገበያውን ለማረጋጋትና አቅርቦት ላይ ለመስራት እርምጃ እንደሚወስድ በገባው ቃል መሰረት እንደ ዘይት ያሉትን ምርቶች በስፋት ወደ ገበያው በማስገባት፣ ቁጥጥርና ከትትል በማድረግ ገበያው እንዲረጋጋ እያደረገ ነው።
መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በስንዴ፣ ሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ ያከናወናቸው ተግባሮች የማሻሻያው አካል ስለመሆናቸው እየተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ወደ ሙሉ ትግበራ ገብቷል።
በማሻሻያው ትግበራ በተለይም የወጪ ምርቶችን የሚያመርቱ አርሶ አደሮች እና አምራች ኢንዱስትሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችም አስታውቀዋል። በትግበራው ኢ-መደበኛ የሆነው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወደ መደበኛ የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚገባም ይታመናል። ከዚህ ባለፈም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ከአቅም በታች እያመረቱ ያሉ ኢንዱስትሪዎች በቂ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያገኙና በዚህም ምርትና ምርታማነት እንደሚጨምርና ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ታምኖበታል።
በዋናነት የንግዱን ዘርፍ እንደሚደግፍ የተነገረለት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው፣ በተለይም የወጪ ንግድን የሚያሳልጥና የተሻለ የሚያደርግ ይሆናል። በመሆኑም በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች የሚበረታቱበትና በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጠር ይጠበቃል። የጅምላና ችርቻሮ ንግድን ለውጭ ባለሃብቶች የሚፈቅድ ሕግ እንደመውጣቱ ለእዚህ ትግበራ ማሻሻያው ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተመላክቷል።
መንግሥት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል። በዚህ ለውጦች ማስመዝገብ የተቻለ ሲሆን፣ የዚህን ለውጥ ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሁለተኛ ምእራፍ መተግበር ተጀምሯል፤ ለዚህ ትግበራ ደግሞ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ወሳኝ መሆኑ ታምኖበት ማሻሻያው ሙሉ ትግበራ ተገብቷል።
ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ እንድትገባ ካደረጓት ገፊ ምክንያቶች መካከል የዕዳ ጫና፣ የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት፣ አዝጋሚ የሆነ መዋቅራዊ ሽግግር፣ ዝቅተኛ ምርታማነት እንዲሁም ዝቅተኛ የልማት ድርጅቶች አፈጻጸም በዋናነት ይጠቀሳሉ።
እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለማቃለልና ኢኮኖሚያዊ ዝንፈትን ለማስታረቅ ወደ ሙሉ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በመንግሥት ቁርጠኝነት የተወሰደ ትልቅ ውሳኔ እንደሆነና ዘላቂ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ የሚያስችል ነው ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችም አስታውቀዋል።
‹‹በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተወሰዱ እርምጃዎች ኢትዮጵያ በ50 ዓመት ታሪክ ውስጥ ያልደፈረችውና ያልሞከረችው ትልቅ ውሳኔ ነው›› ያሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርህተስፋ (ዶክተር)፣ በተለይም ለግሉ ዘርፍ የሚኖረው አበርክቶ ዘርፈ ብዙ መሆኑን አመልክተዋል። ዘርፉ በተለይ የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ ማግኘት ባለመቻሉ የተነሳ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ሳይችል መኖሩን ተናግረዋል። የግል ባለሃብቱ እንዲፈቱለት ሲያነሳቸው የነበሩ እነዚህን መሰል በርካታ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚያስችልም አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ገበያ መር ኢኮኖሚ የሚባሉ መሰረታዊ ምሶሶዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተግባራዊ አልተደረጉም። አሁን እየተገነቡ ካሉ ምሰሶዎች መካከል አንደኛው የካፒታል ገበያ ነው። ይህ ገበያ ከ50 ዓመት በኋላ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥም ተቋቁሟል። ደርግ ከወረሳቸው ኩባንያዎች አብዛኞቹ በካፒታል ገበያ የተቋቋሙ ነበሩ።
በገበያ መር ኢኮኖሚው አንዱና ትልቁ ምሰሶ ካፒታል ገበያ ሲሆን፣ የፋይናንስ ፖሊሲው ተሻሽሎ የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ እንዲመራ መደረጉም ሌላው ለውጥ ነው። በብሔራዊ ባንክ ሲመራ የኖረው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርዓት አሁን በገበያ እንዲመራ ተደርጓል።
የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ በስፋት እንዲገቡ እና የንግዱ ስርዓት ግዙፍ ለሆኑ የውጭ ኩባንያዎችም ጭምር መፈቀዱ ለኢኮኖሚው ያለው አበርክቶ ጉልህ ነው። ግዙፍ የውጭ ኩባንያዎች አገር ውስጥ ገብተው የአገር ውስጥ ምርቶችን ኤክስፖርት እንዲያደርጉ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ሲሆን፣ እነዚህ ኩባንየዎች ከውጭ ዕቃዎችን በራሳቸው የውጭ ምንዛሬ ለማምጣት ከፍተኛ አቅምና ብዙ ተደራሽነት ያላቸው ናቸው። በዚህ ይሰማራሉ ተብለው የሚታሰቡት እያንዳንዳቸው ኩባንያዎች በ70 እና 80 አገራት ውስጥ የሚሰሩና ሰፊ ገበያ ያላቸውም ናቸው ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ተናግረዋል።
ስለዚህ እነዚህ ምሰሶዎች ማለትም የካፒታል ገበያ መቋቋም፣ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ መግባት፣ የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ መቀየር እንዲሁም የውጭ ኩባንያዎች በአገር ውስጥ ንግድ ሥራ መሰማራት መቻላቸው ኢኮኖሚው እንዲያድግ በከፍተኛ መጠን እንደሚያግዘው እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል። ሀገሪቱ የንግድ ሚዛኗን ማስተካከል የምትችልበት መንገድ እንዲፈጠር የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፣ መሰረተልማቶችን በራሷ አቅም መስራት የምትችልበትን ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ እንዲሁም የሕዝቧ ኑሮ እንዲሻሻል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ሲሉ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የውሃ ሃብት፣ የሚታረስ መሬት፣ ማዕድንና ሌሎች በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች እንዲሁም በርካታ ወጣት የሰው ኃይል አላት ያሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ አብዛኞቹ የአውሮፓ አገራትና የምስራቅ እስያ ሀገሮች /ቻይናን ጨምሮ/ ትልቁ ችግራቸው የሰራተኛ ችግር ነው ይላሉ። ምክንያቱም አብዛኛው ሕዝባቸው በጡረታ ውስጥ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ባላት የተፈጥሮ ሃብትና የሰው ኃይል ምክንያት ሰፋ ያለ ኢንቨስትመንት ወደ አገሪቱ ሊመጣ እንደሚችልም ጠቁመዋል። በዚህም ወጣቶች በኢንቨስትመንት መሰማራት የሚችሉበት ሰፊ ዕድል ሊፈጠር እንደሚችልም አመልከተዋል።
የግሉ ዘርፍ ያነሳቸው የነበሩ ችግሮችም በዚሁ ማሻሻያ አማካኝነት እንደሚቀረፉ የጠቀሱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ በተለይም የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲመራ መደረጉ በርካታ ችግሮችን ይቀርፋል ብለዋል። ‹‹የውጭ ምንዛሪ ችግር በራሳችን ያመጣነው ችግር ነው›› በማለት፣ የእስካሁኑ ችግር የፖሊሲ ችግር እንደሆነም ያስረዳሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ላለፉት 50 ዓመታት የውጭ ባንኮች በአገር ውስጥ እንዲገቡ አልተፈቀደላቸውም። እነዚህ የውጭ ባንኮች ባለመኖራቸው በተለይም የውጭ ኢንቨስተሮች የውጭ ምንዛሪ ሊያበድሯቸው የሚችል የውጭ ባንክ ባለመኖሩ የውጭ ኢንቨስትመንት ሊስፋፋ አልቻለም። በዚህ የተነሳም አጠቃላይ የገበያ ኢኮኖሚው እንዲሰራ አልተደረገም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት ምን ያህል ቀላል ነው የሚለውን አስመልክቶ የዓለም ባንክ ያወጣውን ሪፖርት ዋቢ አርገው ሲያብራሩም በዚህ በኩል ኢትዮጵያ ጥሩ ውጤት የላትም ሲሉ አስታውቀዋል። ለዚህም ዋናው ምክንያት ፈቃድ ከማውጣት ጀምሮ መሬትና የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ነገሮች ከባድ የሆኑበትን ሁኔታ በአብነት ይጠቅሳሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ለመስራት በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ሪፖርቱን ዋቢ በማድረግ ገልጸዋል። መንግሥት ይህን ችግር ለመቅረፍ ኮሚቴ በማቋቋም መስራቱንም ተናግረው፣ ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ማሻሻያን ተከትሎ በሚቀጥሉት ዓመታት የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ ማግኘት የሚቻልበት ዕድል ይፈጠራል ያሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ በተለይም በወጪ ንግድ ዘርፉ ላይ የውጭ ኩባንያዎች በሚሳፈተፉበት ጊዜ የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉና ምርትና ምርታማነትም እንደሚጨምር ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል። የአገር ውስጥ ላኪዎች የሌላቸውን ገበያ የውጭ ኩባያዎች በብዛት ሊኖራቸው እንደሚችል ተናግረዋል።
ወደ ውጭ ከሚላከው የኢትዮጵያ ምርት 78 በመቶ የሚሆነው በጥሬው የሚላክ ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ ይህ ሁኔታ ተቀይሮ እሴት ጨምሮ የመላክ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል። ለአብነትም አንድ ኪሎ ቡና በጥሬው ሲላክ ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ይልቅ እሴት ተጨምሮ ሲላክ የሚያስገኘው የውጭ ምንዛሬ እንደሚበልጥ ተናግረዋል። ስለዚህ የአገር ውስጥ ምርቶችን በኢንዱስትሪ ፓርኮችና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እሴት የመጨመር ሥራው ይዳብራል። በዚህም ልዩነቶች ጠበው አገሪቷ ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል ይፈጠራል የሚል እምነት አላቸው።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ከእሴት ጭመራው ባለፈ ከዲያስፖራው የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ መጠቀም እንዲቻል ባንኮች አሁንም በጥቁር ገበያ በሚሸጠው መጠን ልክ መሸጥ ይጠበቅባቸዋል። ይህን ማድረግ ከተቻለ አገሪቷ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ትችላለች።
ሀገሪቱ ከዲያስፖራው ብቻ በዓመት ከ12 እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ትችላለች። ያን ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ችግር ሙሉ በሙሉ ይቀረፋል። ምክንያቱም ከዳያስፖራ የሚገኘው ሃብት ትልቅ አቅም ያለው ነው። ለአብነትም የሕንድና የቻይና ዳያስፖራ ወደ አገሩ የሚልከው ካፒታል በአገሩ ዕድገት ላይ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ሲሉም ያብራራሉ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የግሉ ዘርፍ ችግሮች የሚፈቱበትና የበለጠ የሚበረታቱበት ማሻሻያ እንደሆነ ያነሱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ አቅም ያላቸው የአገሪቱ ነጋዴዎች ከአንድ በመቶ የማይበልጡ እንደሆኑ ጠቅሰው፣ እነዚህ ነጋዴዎች ሰፋ ማለት እንዲችሉ ማሻሻያው ትልቅ አቅም መሆን ይችላል። በተጨማሪም ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡ ወጣቶችም እንዲሁ በሚፈጠረው የንግድ ዘርፍ መሳተፍ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። በዚህም ኑሯቸው የሚሻሻልበትና የአገሪቷ ኢኮኖሚ የሚጎለብትበት ዕድል እንዳለ ነው ያብራሩት።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ›› በሚል መሪ ሃሳብ ባካሄደው አገር አቀፍ የንግድ ሳምንትና ኤግዚብሽን ላይ ተገኝተው ማሻሻያው ለንግዱ ማኅበረሰብ ያለውን አበርክቶ ያስረዱት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ፤ ማሻሻያው በተለይም የንግዱ ማኅበረሰብን የዘመናት ጥያቄ የመለሰ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለንግዱ ማህበረሰብ እየተፈጠሩ ካሉ ምቹ ሁኔታዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው። ማሻሻያው በተለይም የንግዱን ማኅበረሰብ ጥያቄዎች የመለሰ ሲሆን፤ የንግዱን ምህዳር ለንግድ ሥራ አመቺ እያደረገም ይገኛል። ስለሆነም የንግዱ ማኅበረሰብ ይህንን አመቺ ሁኔታ በመጠቀም አገሩንና ራሱን ለመለወጥ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በመስራት ተጠቃሚ እንደሚሆን አመላክተዋል።
ማሻሻያውን ተገን በማድረግ ሕገወጥ ተግባራትን በሚፈጽሙ ላይ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀው፣ በተመሳሳይ አቅርቦትን የማሳደግና የገበያ ትስስሩን የማስፋቱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለንግዱ ማኅበረሰብ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ስለመሆኑ በስፋት ተነግሮታል። በተለያዩ መድረኮች ሲነሳ የኖረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ የአምራቾችን የዘመናት ጥያቄ መመለስ የቻለ ስለመሆኑም መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ የውጭ ባለሃብቶች ሲያነሷቸው ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንደነበር ይታመናል። በአሁኑ ወቅት የውጭ ምንዛሪ በገበያው እንዲመራ በመደረጉ በተለይም አምራች ኢንደስትሪዎች ጥሬ ዕቃ ወደ አገር ውስጥ በማስመጣት ኩባንያቸውን ማስፋትና ምርታማነትን መጨመር እንደሚያስችላቸው ታምኖበታል። ማሻሻያው ወደ ሙሉ ትግበራ መግባቱን ተከትሎ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ስራቸውን ለማስፋትና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸው እንደሆነ ሲያነሱ ተደምጠዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም