ኢትዮጵያ በደን ሃብቷ ከአፍሪካ ሀገራት ግንባር ቀደም እንደነበረች ይታወቃል። ይሁንና ይህ ሀብት እየጨመረ በመጣው የሕዝብ ብዛት፣ ይህን ተከትሎ በተከሰተው የእርሻና የግጦሽ መሬት እጥረትና ሰዎች መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲሉ ደኑን ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በመጨፍጨፋቸው ምክንያት ያ ግዙፍ የደን ሀብት ለመናመን ተዳርጓል።
እንደሚታወቀው ሃገሪቱ በተደጋጋሚ ለድርቅ አደጋ ስትጋለጥ ቆይታለች። ለእዚህ እና ለግብርና ምርታማነት በእጅጉ እየቀነሰ ለመጣበት ሁኔታም በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል የደን ሀብት መመናመኑ ይገኝበታል።
በእርግጥ ሀገሪቷን በተለያዩ ዘመናት የመሩ መንግስታት የወደመውን የደን ሃብት መልሶ ለመተካትና ያለውንም ለመንከባከብ ጥረቶችን ማድረጋቸው አይካድም። ሆኖም ሙከራው ያዝ ለቀቅ ያለበትና የታሰበውን ውጤት ማሳካት ያልቻለ ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የደን ሃብት ከሰብዓዊ ሕይወት ጋር ያለውን ቁርኝት ሁሉም ባይዘነጉትም የሰጡት ትኩረት የጉዳቱን መጠን ታሳቢ ያላደረገና አነስተኛ ስለመሆኑ ሌሎች መረጃዎችም ይጠቁማሉ።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዮት የማዕከላት ማስተባበሪያ ዳይሬክተርና የአፈር ሳይንስና የአግሮኖሚ ከፍተኛ ተመራማሪ እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስተባባሪ ዶክተር ገረመው ታዬ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ የመጣው ያለፉት መንግስታት መሪዎች የአረንጓዴ ልማት ስራን በባለቤትና በቁርጠኝነት መስራት ባለመቻላቸውና ሕዝቡንም በሚገባው ልክ ባለማስተባበራቸው ነው።
በዚህ ምክንያት የሃገሪቱ የደን ሃብት ከመጨመር ይልቅ ለመመናመን ተዳርጓል፤ የእርሻ ቦታ መስፋፋትንና ሕገ-ወጥ ስፍራዎችን ተከትሎ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መጥቷል። ከዚህም ባሻገር ‹‹በተለያዩ መልኩ የተከላ መርሃግብር ቢካሄድም የተተከሉትን የመንከባከብ ባህሉ ባለመኖሩ ሽፋኑን ከፍ ማድረግ አልተቻለም›› የሚሉት ዶክተር ገረመው፤ በተለይ በቀድሞ መንግስታት ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ እንደነበር ያነሳሉ። እንደሃገርም ተግባራዊ የሆነው ፖሊሲም ማዳበሪያንና ምርጥ ዘርን በስፋት በመጠቀም መሬትን ምርታማ ማድረግ፤ በጥቅሉ የእርሻ መሬትን የማስፋፋት አካሄድ መሆኑ ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት የሚጠቀስ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ይኸው የእርሻ ማስፋፋት ፖሊሲ ደግሞ ከደን ልማት ተቃራኒ በሆነ መንገድ ይፈፀም እንደነበር አስታውሰው፣ የደን ስፍራ የነበሩ መሬቶች እየተመነጠሩና እየተቃጠሉ ወደ እርሻ ቦታ በመቀየራቸው የደን መናመኑ ሂደት ተጠናክሮ የቀጠለበትን ሁኔታ እንደነበር ይገልጻሉ።
ይሁንና ባለፉት ስድስት ዓመታት ይህ ሁኔታ መቀየሩን አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ እንደ መንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መከናወን ከጀመረ ወዲህ ከፍተኛ የሚባል ለውጥ መምጣቱን ያስረዳሉ።
‹‹በተለይ ከለውጡ መንግስት ወዲህ ማለትም በ2011 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ሲጀመር በመጀመሪያው ዓመት አራት ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል፤ ይህም ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ መጥቶ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል›› ሲሉ ያብራራሉ።
የዚህ ጠቀሜታው በብዙ መልኩ እንደሚታይም ጠቅሰው፤ በአጭር ዓመታት ውስጥ እዚህ ደረጃ መድረሱ እሰየው የሚያሰኝና በዚሁ መጠንና ጥንካሬ ማስቀጠል ከተቻለ የሃገሪቱን የደን ሽፋን ሙሉ ለሙሉ መመለስ እንደሚቻል ያላቸውን እምነት አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐምሌ 2011 ዓ.ም ያስጀመሩት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአራት ዓመት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኝ መትከልን ዓላማ አድርጎ የተጀመረ ሲሆን፣ በዚህም በመጀመሪያው ዓመት ብቻ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል እቅዱን ሙሉ በሙሉ ማሳካቱ አይዘነጋም። ይኸው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነትና መሪነትና በጠንካራ ክትትል እየተፈጸመ ይገኛል። የሚተከሉ ችግኞች ብዛትም በየዓመቱ አስገራሚ በሚባል ደረጃ እየጨመረ መጥቷል። ዘንድሮም በአንድ ጀንበር ብቻ ስድስት ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ከ615 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል። ይህ እንደ ሃገር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ የሚባል ከመሆኑም ባሻገር የሃገሪቱን የደን ሽፋን በከፍተኛ መጠን ያሳድጋል ተብሎ ይታመናል።
ዶክተር ገረመው እንደሚሉት፤ ችግኝ መትከል የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር አፈርን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ይህም ሲባል በአፈር ውስጥ እየቀነሰ የመጣውን የካርቦን ክምችት ለማሳደግ፤ በአፈር ውስጥ ያለውን ብዝሃ-ሕይወት፣ ውሃና ጠቃሚ ንጥረ ነገር እንዲጨምር ለማድረግ ያስችላል። ይህ ሲሆንም የአፈር ለምነት የሚጎለብት በመሆኑ ምርታማነት በዚያው ልክ ከፍ ይላል።
‹‹በተለይ ተራራማ አካባቢዎች ላይ ዛፍ መትከል ዓመቱን ሙሉ በዘላቂነት የሚፈሱ ወንዞች እንዲኖሩ ያደርጋል›› የሚሉት ተመራማሪው፤ ይህም ሲባል ዛፎች በስሮቻቸው የሚፈሰውን ውሃ በመያዝ አፈር ውስጥ ሰርጎ እንዲገባ በማድረግ የጎርፍ መጠንና የአፈር መሸርሸርን ይቀንሳል፤ በተጓዳኝ የአፈር ጤናን ይጠብቃል ሲሉ ያስረዳሉ። ‹‹ይህ የችግኝ ተከላ በተጠና መልኩ ከቀጠለ የአፋርን ጤናና ምርታማነት ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ላይ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል›› ሲሉ ያስገነዝባሉ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዘንድሮውን የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መጠናቀቅ አስመልከተው ባስተላለፉት መልዕክትም ‹‹የዛሬ ጀምበር ወጥታ እስከምትጠልቅ 600 ሚሊዮን ችግችን ልንከተል ኢትዮጵያውያን ሁሉ አቅደን ነበር፤ ያሰብነውን ሳናሳካ ጀምበር የሚጠልቅብን አይደለንምና በአንድ ጀምበር 615 ነጥብ 7 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ችለናል›› ሲሉ በመንግስት በኩል የተሰጠውን ልዩ ትኩረት መግለፃቸው ይታወሳል።
አያይዘውም ከችግኙ ጎን ለጎን ሕፃናት ተስፋቸውን መትከላቸውን፤ ወጣቶች ፅናታቸውን ማሳየታቸውን አረጋውያን ውርስ ያኖሩበት ድንቅ ክንውን መሆኑን ተናግረዋል። በጥቅሉ ኢትዮጵያውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከቤታቸው ወጥተው የማይደበዝዝ አሻራ ማሳረፋቸውን፤ በማበራቸውና በመፅናታቸውም በዓለም ያልታየ አዲስ ስኬት ማስመዝገብ መቻላቸውን ነው ያመለከቱት።
ዶክተር ገረመው በበኩላቸው ‹‹ዘንድሮ በተለየ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶት በመሰራቱ ከታቀደውም በላይ ማሳካት ተችሏል፤ ለስኬቱ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የመንግስት ቁርጠኝነት ነው›› ሲሉ ይገልፃሉ። በተለይም መንግስት ስሩ ብሎ የመተው ሳይሆን ከላይ ሆኖ ስራውን የራሱ አድርጎ መስራቱና ድጋፍ መስጠቱ እንደሆነም ያስረዳሉ። ከላይ መንግስት ድጋፍ ሲሰጥ ደግሞ በየደረጃው ያሉት የመንግስት አመራሮች ለስራው በዚያው ልክ ትኩረት መስጠት በመቻላቸው እንደሆነ ይገልፃሉ። ከዚህ ባሻገርም ሕዝቡ በሂደት የዛፍ ችግኝ መትከልን ጥቅም እየተረዳ በመምጣቱና ተሳታፊ በመሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ።
‹‹አሁን ላይ ሕዝቡ ደን ማልማት ሃገርን ማፅናት እንደሆነ፤ አፈር መጠበቅ፤ ውሃ ማጎልበት እንደሆነ፤ ለትውልድ ምቹ ሃገርን የማስተላለፍ ሁኔታን መፍጠር እንደሆነ ተገንዝቧል›› ሲሉ ዶክተር ገረመው ያብራራሉ። አክለውም ‹‹ ከዚህ ቀደም አብዛኛው ሰው ችግኝ በገንዘቡ ገዝቶ ሊተከል ቀርቶ በነፃ ተሰጥቶት እንኳን ለመትከል ፍቃደኛ አልነበረም›› ሲሉ አስታውቀው፣ አሁን ግን በገንዘቡ ችግኝ ገዝቶ ይተክላል፤ በየቦታው የተደራጁ ወጣቶች ችግኝ እያፈሉ መሸጥን ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው አድርገውታል›› በማለትም ይናገራሉ።
በተመሳሳይ የእሳቸውን ተቋም ጨምሮ በአብዛኞቹ የምርምር ተቋማት ችግኝ አባዝቶ የመትከል ባህል እንዳልነበረ ይጠቅሳሉ። ‹‹በእኛ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም ችግኝን በየማዕከሉ አባዝቶ የመትከል ሁኔታ አልነበረም፤ አሁን ማዕከላቱ አባዝተው ለራሳቸውም ይተክላሉ፤ በአካባቢያቸው ላሉ ተቋማትና ለተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያከፋፍላሉ›› ይላሉ። ዘንድሮም ከአንድ ጀምበር መርሃ ግብሩ ቀደም ብሎ በየማዕከሉ በተለይ ለምግብ ዋስትና፤ ለመኖና መሰል ሃገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ችግኞች በማባዛትና ለሕብረተሰቡና በተቋሙ አቅራቢያ ላሉ ተቋማት በማከፋፈል የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን አስታውቀዋል።
ለዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ግን የመንግስት ቁርጠኝነት ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዝ ስለመሆኑ መስመር አለበት የሚሉት ዶክተር ገረመው፣ ‹‹መንግስት በተለይ ዘንድሮ የችግኝ ተከላን ዋነኛ የልማት ምሶሶ ወይም ቁልፍ ስራ ብሎ መስራቱን ተናግረዋል። ይህም ኢትዮጵያ የውሃ ማማ ሆና እንድትቀጥል ያየዘው አቅጣጫ ውጤታማ ስለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ‹‹ በአረንጓዴ አሻራው በጥቅሉ ችግኞችን ተከልን ማለት አፈር ጠበቅን ማለት ነው፤ አፈሩን የማይጠብቅ ሕዝብና መንግስት ደግሞ ለራሱ ለመጥፋት የተዘጋጀ ነው። ምክንያቱም ለመጪው ትውልድ የሚያበላው የሚያስረክበው የለውም›› በማለትም ያስገነዝባሉ።
እንደ ዶክተር ገረመው ማብራሪያ፤ ችግኝ መትከል ብቻውን ግብ አይደለም፤ ችግኝ ተተክሎ ካልፀደቀ፤ እንክብካቤ ካልተደረገለት ለሃገር ኪሳራ ነው። በመሆኑም መትከሉ ላይ የታየው ቁርጠኝነትና ተሳትፎ በማፅደቁና መንከባከቡ ላይም ሊደገም ይገባል። በተለይም ከተከላ በኋላ ውሃ ከስሩ እንዳይተኛና እንዳያበሰብሰው መጠንቀቅም ያስፈልጋል። ዛሬ ላይ በነቂስ ወጥቶ ዛፍ የተከለው ሰው ዓመቱን ሙሉ በተከለበት አካባቢ እየተመላለሰ ክረምቱም ውሃ እንዳይተኛበት፤ አረም እንዳይበላው፤ በበጋው ደግሞ ድርቅ እንዳይገለው መከታተልና መደገፍ ይጠበቅበታል። በተጨማሪም በተተከለባቸው አካባቢዎች የሚሞቱ ችግኞች ሊኖሩ ስለሚችሉ በአዳዲስ የመተካት ስራ መስራትም ይገባል።
አሁን ያለውን ቁርጠኝነት ማስቀጠል ከታቻለም የተሻሻለ የግብርና አሰራር ማስፈን፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የውሃ ሃብትንና የብዝሃ ሕይወት ጥበቃን በማረጋገጥ ዘላቂ ተጠቃሚነትን ያመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ተመራማሪው ተናግረዋል። ከሁሉም በላይ የተጀመረው መርሃ ግብር የጎረቤት ሀገራትን ትኩረት በመሳብ ለጋራ ተጠቃሚነት በጋራ እንዲሰሩ ከማነሳሳት ባለፈ በቀጠናው በግጦሽ መሬት፣ በውሃና በደን ሃብት እጥረት የሚፈጠረውን ግጭት በማስወገድ ስደትንና ከመኖሪያ ቀዬ መፈናቀልን ለማስቀረት ያስችላል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከሀገሪቱ የቆዳ ስፋት 40 በመቶውን ይሸፍን ነበር። ይህ የደን ሀብት በተለያዩ ምክንያቶች እየተመናመነ መጥቶ ሶስት በመቶ ደርሶም ነበር። መንግስታት ይህን አደጋ ለመቀልበስ ባደረጉት የችግኝ ተከላ የደን ሽፋኑ 17 በመቶ ደርሶ እንደነበርም መረጃዎች ያመለክታሉ።
ባለፉት አምስት ዓመታት ደግሞ የለውጡ መንግስት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በካናወነው ተግባር 32 ነጥብ አምስት ቢሊየን ማድረስ ተችሏል። በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች ብዛት እየጨመረ ይገኛል። በአንድ ጀንበር የሚተከሉ ችግኞች ብዛትም እንዲሁ እየጨመረ መጥቷል።
የደን ሽፋኑንም ከ23 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞች ብዛትም በ2016 ዓ.ም በተከናወነ ሰፊ ተግባር 40 ቢሊየን ማድረስ ተችሏል። ይህን አሀዝ 50 ቢሊየን ለማድረስም ታቅዷል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም