የራሷ የዘመን አቆጣጠር ያላት ኢትዮጵያ፣ 2017 ዓ.ምን ተቀብላለች። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሀገሪቱና ዜጎቿ መስከረም ሲጠባ መልካሙን ተመኝተውና አልመው የነበረ ቢሆንም፣ የሰላም እጦት፣ የዜጎች አሰቃቂ ሞትና መፈናቀል፣ የሀብት ዝርፊያና ውድመት … ደጋግመው ጎብኝተዋቸዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ በሰላም እጦት በእጅጉ ተፈትናለች። ይህ የሰላም እጦት ዜጎች ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን እንዲያጡ በማድረግ ከፍተኛ ኅብረተሰባዊ ቀውስ ፈጥሯል። መንግሥት የኅብረተሰቡን ሰላም ለማስጠበቅ ልዩ ልዩ ጥረቶችን አድርጎ በጥቂት የሀገሪቱ አካባቢዎች አንፃራዊ ሰላም ቢሰፍንም፣ አሁንም አስከፊ የሕይወት መስዋዕትነት እያስከፈሉና ከፍተኛ የንብረት ውድመት እያስከተሉ ያሉ ግጭቶች አሉ። ስለሆነም በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ዐበይት ትኩረቶች ሊሆኑ ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል ዋናው ሰላምን ማስፈን ነው።
ሰላም ከሰላም ስብከት የተሻገረ ሃቀኛ ቁርጠኝነትን ይፈልጋል። ለሰላም ዋጋ መክፈል መሸነፍ አይደለም። በአሸናፊና ተሸናፊ ትርክት የተቃኘው የፖለቲካ ባህላችን ለሰላም የሚከፈልን ዋጋ እንደሽንፈት ይቆጥረዋል። ሕዝብ ሰላምን በእጅጉ ይሻል፤ ሕዝብ ለሚፈልገው ነገር ቅድሚያ መስጠት ደግሞ ሕዝብን ማክበር ሀገርንም መውደድ ነው። የሰላም በሮችን እየዘጉና የሰላም አማራጮችን እየገፉ ‹‹ሕዝብ ይወደኛል፣ የምታገለው ለሕዝብ ነው…›› ማለት ትልቅ ስላቅ ነው። ‹‹ሰላም ወዳድ›› ለመባል ብቻ ስለሰላም መስበክም ለውጥ አያመጣም። ግጭቶች በተራዘሙ ቁጥር ሥርዓት አልበኝነት እንደሚንሰራፋ፣ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት በእጅጉ እንደሚዳከም እንዲሁም ዜጎች በሀገራቸው ተስፋ እንደሚቆርጡ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ሰላምን ለማስፈን የሚከፈል ዋጋ ዘላቂ ትርፍ የሚያስገኝ ቅዱስ ተግባር ነው።
ሌላው ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ሀገራዊ አንድነትን ማስጠበቅ ነው። ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ-ፖለቲካዊ ቀጣና የዓለምን ትኩረት የሚስብ አካባቢ ነው። ይህ ቀጣና በየጊዜው በፍጥነት የሚለዋወጡ ክስተቶችን የሚያስተናግድ በመሆኑ ኢትዮጵያም ለዚሁ የቀጣናው ነባራዊ ሁኔታ ተጋላጭ ናት። ከሩቅም ከቅርብም ያሉት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን በመጉዳት ‹‹ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ›› ሲታትሩ እንደኖሩ በግልፅ የሚታወቅ ሃቅ ነው። በቅርቡ እንደታዘብነው የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች የሀገር ውስጥና የጎረቤት ፈረሶቻቸውን ተጠቅመው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ አደጋ ለመደቀን ደፋ ቀና እያሉ ነው።
ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ መቆየት የቻለችው በሕዝቧ አንድነት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በየጊዜው ከውስጥና ከውጭ የተነሱበትን ጠላቶች ድል ያደረገው አንድነቱን ጠብቆ በጋራ በመተባበሩ ነው። ታዲያ በሀገር ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያንዣበቡትን የጠላት ክንፎች ለመስበር በሀገር ውስጥ ሰላምና ፍትህን ማስፈን ይገባል። በሰላም እጦትና በኢፍትሃዊነት የተማረረ ሕዝብ ለውጭ ጠላቶች መጠቀሚያ እንዳይሆን የቤት ሥራን (ሰላምና ፍትሕ የማስፈን ሥራዎችን) ቀድሞ ማጠናቀቅ ያስፈልጋል።
የምጣኔ ሀብት ጉዳይም ትኩረት የሚፈልግ ወሳኝ ሀገራዊ አጀንዳ ሊሆን ይገባል። የእቃዎችና የአገልግሎት ዋጋ በየጊዜው ማሻቀብ እንጂ ዝቅ ማለት አልሆነለትም። ይህም የኅብረተሰቡን፣ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል፣ ኑሮ እጅግ የከበደ እንዲሆን አድርጎታል። ለዋጋ ንረቱ የተለያዩ ምክንያቶች ዛሬም ድረስ እየተጠቀሱ ቢዘልቁም፣ እነዚህ ምክንያቶች ኑሮ ናላውን ላዞረው ኅብረተሰብ ምንም አይፈይዱም። ‹‹ኑሮውን አልቻልነውም … የዋጋ ንረቱ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል …›› የሚሉና ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲደመጡ የቆዩ የኅብረተሰብ ድምፆች ዛሬም መስተጋባታቸውን ቀጥለዋል።
መንግሥት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ዘርፈ ብዙ የአጭርና የረጅም ጊዜ የመፍትሄ አማራጮችን በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። ይሁን እንጂ እነዚህ ርምጃዎች ሥር ለሰደደው ችግር አጥጋቢ መፍትሄ አስገኝተዋል ለማለት አያስደፍርም። የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እጅግ ውስብስብ በሆነ የደላሎች ወጥመድ ውስጥ በመውደቁ፣ አንዳንድ ጊዜ ችግሩ የት እንዳለ ለመለየት እንኳ ያስቸግራል። ታዲያ ችግሩን ከመለየት ጀምሮ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የአገልጋይነት መንፈስ የተላበሰ እንዲሁም የሀገር ፍቅርና ሙያ ያለው አመራርና ባለሙያ ያስፈልጋል።
የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ወደተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ያሸጋግራል የተባለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር፣ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ በከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ መሥራት ይገባል። በዚህ ረገድ የህብረተሰቡንና የባለሙያዎችን ሃሳብ ማዳመጥ፣ ማሻሻያው ስኬታማ እንዳይሆን ችግር በሚፈጥሩ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ የማያዳግም ርምጃ መውሰድ እንዲሁም ማሻሻያውን በብቃት ለመተግበር የሚያግዙ ተቋማትን ማደራጀትና ማጠናከር ያስፈልጋል።
አዲሱን ዓመት ስንቀበል ከምንሰናበተው አሮጌ ዓመት ጋር አብረው የማይሰናበቱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ። በአዲሱ ዓመት ሊከናወኑ የሚገባቸው ብዙ ሥራዎችም አሉ። ኢትዮጵያ ብዙ ሺ ዓመታትን ባስቆጠረው እድሜዋ ‹‹ረሃብንና ጦርነትን ደጋግማ የማስተናገዷ ምክንያት ምንድን ነው? ደጋግመው ካጋጠሟት ችግሮቿ መላቀቅ ያልቻለችውስ ለምን ይሆን?›› የሚለው ጥያቄ የሰከነ ውይይትና አጥጋቢ ምላሽ የሚፈልግ መሠረታዊ ጉዳይ ነው።
ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ነፃነት፣ ክብርና አንድነት ሲሉ በዓድዋና በሌሎች ሥፍራዎች ለማመን የሚከብዱ ከባድና አኩሪ ተጋድሎዎችን አድርገው ነፃ አገር ለ‹‹ተተኪው ትውልድ›› ቢያስረክቡም ‹‹ተተኪው ትውልድ›› (በተለይ ልሂቃኑ) ግን እነዚያ መስዋዕትነቶች ያስገኟቸውን በረከቶች በመመንዘር ለታላቅ ሀገር ግንባታ ግብዓትነት ሊጠቀምባቸው አልቻለም። ታዲያ ይህን የባከነ እድል በእልህና በቁጭት የመጠቀም ኃላፊነት የወደቀው በዚህ፣ በእኛ ትውልድ ላይ ነው። ይህ ትውልድ በብሔርና በሃይማኖት ተከፋፍሎ ሀገር ለማፍረስ የሚደረገውን አሳዛኝና አሳፋሪ ግብግብ የመታገልና የመመከት አደራ አለበት። የተረሳውና የባከነው የቀደምት ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ትርጉም እንዲኖረው እልህ አስጨራሽ ትግል ይጠብቀዋልና ለትግሉ ወገቡን ጠበቅ አድርጎ መነሳት ይጠበቅበታል።
ታዲያ ቅንነት፣ ትጋትና ፅናት ተላብሶ የሀገሪቱን ችግሮች ለመፍታት በቅድሚያ የምክንያታዊ አስተሳሰብ ባለቤት መሆን ያስፈልጋል። ምክንያታዊ አስተሳሰብ በሌለበት ቦታ፣ ትርጉም ያለውና ተጨባጭ የሆነ ለውጥን ማሳካት አይቻልም። ኢትዮጵያ ‹‹ለምን?›› እና ‹‹እንዴት?›› ብሎ ለመጠያየቅ፣ ለመከራከርና ለመወያየት የሚያስችል የሠለጠነ ባህል አላዳበረችም። ማሰብን፣ ማሰላሰልን፣ ሚዛናዊ ዕይታንና መመርመርን የሚጠይቀው እንዲሁም ‹‹ምን?››፣ ‹‹እንዴት?››፣ ‹‹ለምን?››፣ ‹‹መቼ?››፣ ‹‹የት?›› የሚሉትንና ሌሎች ተያያዥ መሠረታዊና አመክንዮን የተከተሉ ወሳኝ ጥያቄዎችን በማንሳት እውነትን ከሐሰት አብጠርጥሮ የማጥራት እሳቤን የያዘው ምክንያታዊነት የተባለው ጽንሰ ሃሳብ ቦታ ሊያገኝ ይገባል።
ታላቅ ሀገር ለመገንባትና የኃያል ሀገር ባለቤት ለመሆን የታላቅና በጎ አስተሳሰብ ባለቤት መሆን ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው መንገዶቿ በጥልቀት ተፈትሸው፤ችግሮቿና ስብራቶቿ በግልጽ ውይይት ተደርጎባቸው የእስካሁኑን የኋልዮሽ ጉዞዋን በማስቆም ወደፊት እንድትራመድ ማድረግ ይገባል። ለተደጋጋሚ ረሃብና ጦርነት የዳረጓትና ከተለመደና ከተሰለቸ የ ‹‹ታላቅነት›› ወሬ ተሻግራ እውነተኛ ኃያልነትን እንዳትላበስ ያደረጓት የዘመናት ሰንኮፎቿ በግልጽ ሊነገሩና ምላሽ ሊሰጣቸው ያስፈልጋል! ኢትዮጵያ ችግሮቿን በግልጽ የሚናገርላትና መፍትሄ የሚፈልግላት ልጅ/ትውልድ ትሻለች!
ምክንያታዊ አስተሳሰብን ባህሉ ያደረገ ትውልድ የመገንባት ተግባር በአንድ ጀንበር፣ በአንድ ዓመት የሚሳካ ባይሆንም ጉዞው ከአሁኑ መጀመር አለበት። ይህ ትውልድ ምክንያታዊ ትውልድ የመሆን ግዴታ ወድቆበታል። ይህን ግዴታ በብቃት አለመወጣት ግን ሀገርን የሚያሳጣ አደገኛ ዋጋ ያስከፍላል። አዲሱ ዓመት ደግሞ በአዲስ ሀገራዊ ተስፋ ስለኢትዮጵያ ችግሮች በግልጽ ተነጋግሮና ተማምኖ እውነተኛና ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች የሚደረጉበት ሊሆን ይገባል! ተደጋጋሚ መከራዎች ወገቧን ያጎበጧት እናት ኢትዮጵያም ከዚህ በላይ ለመጠበቅና ጊዜ ለማባከን ዝግጁና ብቁ አይደለችም!
ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም