
አዲስ አበባ፡- አዲሱ ዓመት ከሁሉም በላይ የተሻለ የሠላም ዓመት እንዲሆን ምኞታቸው መሆኑን የተለያዩ የተቋማት ኃላፊዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) የአዲስ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በኩል ባስተላለፉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ አሮጌው ዓመት በርካታ ድብልቅ ስሜቶች ያሳለፍንበት ዓመት ነበር፤ 2017 ዓ.ም የተሻለ፣ መልካምና ከሁሉም በላይ የሰላም ዓመት ይሁንልን ብለዋል።
ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኃላፊዎች ባለፉት ሁለት ዓመት ከአምስት ወራት የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወናቸውን አስታውሰው፤ በቀጣይ እስከ አዲሱ ዓመት አጋማሽ ድረስ የተያዙ ሥራዎች የሚጠናቀቁበት ዘመን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
መሠረታዊ የሆኑና ማግባባት ያልቻሉ ምክንያቶችን ነቅሶ በማውጣት በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ የሚወያዩበትን መድረክ አመቻች እንደመሆናችን መጠን ሁሉንም ክልሎችና በተዋረድ ያሉትን ባለድርሻ አካላት በመለየት አጀንዳዎቻቸውን ሰብስበው የሚሰጡበት ሂደት ላይ እንገኛለን ሲሉ አስረድተዋል።
ዓመቱ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሠላም፣ የጤናና ከሁሉ በላይ ያለፉትን ችግሮቻችንን በሚገባ ተገንዝበን በመሰባሰብ እርስ በርሳችን ታርቀን ወደ ሀገራዊ ምክክር የምንሄድበት ጊዜ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺህ በላይ ወረዳዎች ላይ አጀንዳ እየተሰበሰበ መሆኑን አመላክተው፤ በቀጣይም የተሳካ የምክክር ሂደት እንዲፈጠር በአዲሱ ዓመት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አመላክተዋል።
የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ የሰላም እጦት ችግሮች የሚቀረፍበት ዓመት እንደሚሆን ተስፋ አኝ ሲሉ ተናግረዋል። ለሰላም እንቀፋት የሆኑ ችግሮች እንዲወገዱ ሚኒስቴሩ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
በ2017 ዓ.ም ለአዎንታዊ የሰላም ግንባታ ትኩረት ተሠጥቶ እንደሚሠራ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተለይም ከኃይማኖት ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የተሻለ ሰላም ሀገሪቷ ላይ እንዲሰፍን በርካታ ሥራዎች መጀመራቸውን አንስተዋል፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዓመቱ እንደ ሀገር የተያዙ እቅዶቻችን የሚሳኩበት፤ ወደ ብልጽግና የሚደረገው ጉዞ በተሳካ ሁኔታ የሚከናወንበት ይሆናል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ አያሌው (ኢ/ር) ናቸው፡፡ የሕዝቡ ዕድገት ጎልቶ የሚወጣበት የሰላም ዓመት እንደሆንም ተመኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው፤ አዲሱ ዓመት ለመላው ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የጤና፣ የደስታ የስኬትና እንዲሁም የዕድገትና ብልጽግና ዓመት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
ኮሚሽኑ በ2016 ዓ.ም የተሰጡትን ተልዕኮዎች በአግባቡ መፈጸም እንደቻለ ገልጸው፤ ይህንኑ በ2017ዓ.ም አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ነው ያስታወቁት፡፡
አዲሱ ገረመው