በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና 5 ነጥብ 4 በመቶ ተማሪዎች 50 በመቶና ከዚያ በላይ ውጤት አስመዘገቡ

  • አንድ ሺህ 363 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ማሳለፍ አልቻሉም

አዲስ አበባ፡– በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱ 674 ሺህ 823 ተማሪዎች ውስጥ 36 ሺህ 409 ተማሪዎች 50 በመቶና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገባቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱ 674 ሺህ 823 ተማሪዎች ውስጥ 36 ሺህ 409 ተማሪዎች የማለፊያ ነጥብ አምጥተዋል፡፡ ይህም የአጠቃላይ ተፈታኞችን 5 ነጥብ 4 በመቶ ይሸፍናል፡፡

የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ በ 9 ሺህ 114 ተማሪዎች ብልጫ እንዳለውም ገልጸዋል።

በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ 28 ሺህ 158 ወይም 9 በመቶ በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 8 ሺህ 251 ወይም 2 በመቶ የማለፊያ ውጤት ማምጣታቸውን አመላክተው፤ አንድ ሺህ 221 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል በነበረው የመሰናዶ ትምህርት በትግራይ ክልል ፈተናቸውን ከወሰዱ ተፈታኞች መካከል ከ700 በተፈጥሮ ሳይንስ ከትግራይ ቀላሚኖ ትምህርት ቤት አንድ ተማሪ 675 ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በዚህ ዓመት ፈተናቸውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ከ600 በተፈጥሮ ሳይንስ ከአዲስ አበባ አግዚሊየም ካቴድራል ትምህርት ቤት 575 (በሴት ተማሪ) የተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው፤ በማህበራዊ ሳይንስ ከአዲስ አበባ ኢትዮ ፓረንትስ 538 (በሴት ተማሪ) ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል ።

በዚህ ዓመት ሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ከአምናው በተሻለ ተማሪዎችን ማሳለፋቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ አንድ ሺህ 363 ትምህርት ቤቶች ግን ምንም ተማሪ አለማሳለፋቸውን ጠቁመዋል።

50 በመቶና ከዚያ በላይ ያመጡት በቀጥታ ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደሚገቡ የጠቆሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ የተወሰኑ ተማሪዎችም በሪሜዲያል ፕሮግራም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጨምረው ገልጸዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You